ክፍል1

Chapter 1 of 1
"ቲጂ" ጓደኞቿ እንደሚጠሯት በዴስኳ ላይ ተቀምጣ የላፕቶፗን 'ኪቦርዶች' በቀጫጭን ረጃጅም ጣቶቿ ወዲህና ወዲያ እያለች ትጫናቸዋለች ። ጥፍሮቿ ደብዘዝ ባለ ቀይ ቅብ ደምቀዋል ፣ ሁለት ወርቃማና የሚያብለጨልጩ ቀለበቶች በቀኝ እጇ ፣ አንዱን ማርያም ጣቷ ላይ ሌላውን ቀለበት ጣቷ ላይ ሰክታለች ፣ እንደሃብል ያለ ረዘም ያለና የሚያንጸባርቅ 'ብራስሌት' ግራ እጇ ላይ ጠምጥማለች ፣ ሰፋ ያለው የሸሚዟ እጅጌ እንዳይሸፍንባት ወደ ላይ በትንሹ አጥፋዋለች ።

እንደጣቶቿ ፊቷንም ማሳመር ትወዳለች ። ስስ ከንፈሯን እንደጣቶቿ ጥፍሮች ያለ ቀለም ቀብታቸዋለች ፣ ቅንድቧን ተኩላ ፣ ከአፍንጫዋም ላይ ጌጥ በስታ ፣ ረጅም ጸጉሯን እንደሚሆን አድርጋው ፣ ተሽቀርቅራ . . . ስልኳ ይጠራል ። እጇን ከኪቦርዱ ላይ አርቃ ስልኳን ወደ ጆሮዋ አስደግፋ "ሄሎ ሚሚዬ . . . " አለች ፊቷ ካለው ግድግዳ ላይ የተሰቀለውን ሰዓት እያየች ። '6 ፡ 45 ' ይላል።
"ቀረሽ እንዴ? . . . " እንደሷው ያለ ቀጭናን የሚጎተት የሴት ድምጽ። "እረ መጣሁ . . . ተነስቻለው . . . ጀምሩ ችግር የለውም . . . እየመጣሁ ነው።" ላፕቶፗን ከድና ቦርሳዋን ወምበሩ ላይ እንዳንጠለጠለች ከተቀመጠችበት እየተነሳች ።
"እሺ እሺ ውዴ " የሚለውን ካደመጠች በኋላ ስልኩ ተቋረጠ ። ወደ ሱሪ ኪሷ ስልኳን ከታ ከቢሮው ወጣች።
መስሪያ ቤታቸው የነበረበት ህንጻ አዲስ ቢሆንም ግንባታው ገና ጨርሶ አልተጠናቀቀም ስለሆነም ወለሉ መጨረሻ ላይ የሚታየው አሳንሱር 'ከአገልግሎት ውጭ' የሚል ወረቀት ተለጥፎበታል። ሳታነበው በደረጃው አድርጋ ወደታች ወረደች ። ሰሞኑን ስታደምጠው የነበረው ዘፈን በሃሳቧ ይመላለሳል ። 'ፍላት' ጫማዋ ደረጃውን ሲመታ የዘፈኑ ግጥም ቤት ሲመታ ፣ እግሯን እያነሳች ስትጥል የዘፋኙም ድምጽ ሲወጣና ሲወርድ ፣ በርግጥ ዘፈኑን እየሰማችው እንዳለ ሁሉ ጌጦች ያጣበቡትን ጆሮዋን እያለፈ የዘፋኙ ድምጽ የሚገባ ይመስላታል ።"ምህ . . . ምህ . . . " ከህንጻው ስትወጣ በራሷ ድምጽ ማንጎራጎር ጀመረች ። አስፓልቱን ተሻግራ ፊትለፊት ከነበረው ምግብ ቤት ገብታ በአይኗ ወዲህና ወዲያ አማትራ ከነ ሚሚ አጠገብ እስክትቀመጥ ድረስ ዘፈኑን አላቆመችም ነበር።
አንድ ጊዜ እንዲሁ ምሳቸውን እየበሉ 'ምግብ እየተበላ በተቻለ ፍጥነት አለማውራት ነውር ነው' ብለው ህግ አውጥተው ነበር ። ከሰላምታና የመጀምሪያው ጉርሻ ከተጨበጠ ወዲያ ይህ ህጋቸውን ሊተገብሩ አላረፈዱም ። የባጡንም የቆጡንም እንደመጣላቸው ያወሩ ጀመር።
"ስሚማ ?" አለች ሚሚ ለህያብ ። "ከህሩይ ጋ እንዴት ሆናቹ?"
"ምንም አዲስ ነገር የለም . . . ከምታውቁት ውጪ" አለች እንደመከፋት እያለች ።
"ማለት ? ራት የጋበዘሽ ለምንም ነው? እንደዛ ስትቻኮይ" አለች ቲጂ። "ምንም ዝም ብለን አውርተን ነው የተለያየነው . . . የሆነ ነገር ሊነግረኝ ግን ፈልጎ ነበር መሰለኝ አስተያየቱ ላይ ያስብቅበታል . . . አላቅም? ምናልባት ገምቼ ይሆናል ? ግን ስንለያይ በጣም ደብሮት ነበር ።" እንጀራውን እያተራመሰች ።
"እንደ እቅዱ ስትይ?" ሚሚ ተቀብላ።
"እንዴት ልበልሽ . . . መጀመሪያ አካባቢ በጣም አሪፍ እየሄደ ነበር ። እየቀለደ እየሳቅን ነበር። ከዛ በመሃል ስልኩ ጠራ አላነሳውም ነበር ። ከዛ ግን በየጨዋታው መሃል እየደወለ ሲያስቸግረው ወይ እንዲያነሳው ወይ ደሞ ሳይለንት እንዲያረገው ነገርኩት ። ስልክ ቁጥሩን እንደማያውቀውና እንዲህ ባለ ሰዓት ማንሳት እንደማይፈልግ ነግሮኝ ሳይለንት አደረገው . . . ከዛ ጨዋታችንን ቀጠልን . . . ስራ ሊለቅ እያሰበ እንደሆነና የራሱን ስራ ሊጀምር እንደፈለገ ነገረኝና ምን እንደማስብ ጠየቀኝ . . . ሃሳቤን ሳልነግረው ስልኩ ላይ መልክት ገባ። አው ሳይለንት አርጎት ነበር መልክቱም ሲገባ አይሰማም ግን እንኳን ለሱ ቀርቶ ለኔም መልክት ያለማቋረጥ ሲገባለት እየታየኝ ነበር ። ሳያስበው ነው እሱም ያየው . . . ግን ወዲያው ሲረበሽ አስታወቀኝ ። ብዙም ሳይቆይ መሄድ እንዳለበት እና እንደሚክሰኝ ነገረኝና ከሆቴሉ ወጣን ከዛ በላዳ አሳፍሮኝ ሄደ።" አለችና የምጸቷን ፈገግ አለች። ሚሚ "ወዴት?" አለች ተቀብላ። አሁንም የምጸቷን ስቃ "አልነገረንኝም 'አስቸኳይ ነገር ገጥሞኛል' ብቻ ነው ያለኝ ።" በነገሩ መብገኗን ለመደበቅ እየሞከረች ። "እና ዛሬ ስራ አልመጣም እንዴ?" አለች ቲጂ። "አልመጣም . . . ጥዋትም ስደውልለት ስልኩ ዝግ ነበር ።" አሁን ደሞ መጨነቋን ለመደበቅ እያለች ። ሚሚ መረበሿን በመረዳት "ከባድ ነገር ቢሆን ኖሮ መደወሉ አይቀርም ነበር ። ባይሆን ነው ያልነገረሽ " በማለት ልታረጋጋት ሞክረች ። ህያብ ትከሻዋን ነቀነቀችላት ፣ ቀጥላ የወሬያቸውን ርዕስ ለመቀየር "መላኩ እንዴት ነው?" አለች። ጥያቄው የተሰነዘረው ለቲጂ ነበር ። ሚሚ በቅርቡ ትዳር የመሰረተችና ሁሉ ነገር መልክ መልኩን እየያዘላች እንደሆን ቀደም ሲል ተጨዋውተዋል ። ጥያቄውን አድምጣ ቲጂ ፈገግ አለችና ". . . ደህና ነው ። ያሳዝናል ሞኝነቱ ምናምን ።" ብላ መልሳ ሳቀች ። የሚለውንና አኳሃኑን እየነገረቻቸው አብረው መሳቅ ጀመሩ። ምግቡ ካለቀ ቢቆይም ቡና ሳይጠጡ አይወጡምና ቡናውም እስኪደርስላቸው ጨዋታቸውን ቀጠለ ። ስለ መላኩ 'ሞኝነት' ፣ 'ኣሳዛኝነት ' . . . ወ.ዘ.ተ።
በርግጥ መላኩ ሞኝም አሳዛኝም የሚባል አልነበረም። ነገር ግን ለቁም ነገር ትግስትን ይፈልጋታል የተቀረውን ህይወቱን ከሷ ጋር ማሳለፍ በመፈለጉ በየትኛውም አይነት መልኩ በሷ ፊት የተበላሸ ገጽታ እንዳይኖረው ይፈልጋል ለዛም የሚናገረውንና የሚያረገውን በጣም በመጠንቀቅ ነው የሚያረገው ። ለምትጠይቀው ጥያቄ የሚሰጣት ምላሽ የተብላላና የተቆጠበ ነው ፣ የሚቀልድላትም ቀልድ እንደ ሂሳብ ቀመር የተጠና ነው ።
ለሷ እንዲህ ያለ ወንድ ሲገጥማት የመጀመሪያዋ አይደለም ። ብዙዎች በውበቷ ተረተውና ክብራቸውን ጥለው ከስሯ ሲከተሏት ፣ ስታስከትላቸው የደስታን ተራራ ስታወጣቸው በሚቃጠል የስሜት ባህር ውስጥ ስታስዋኛቸው ትከርምና ወድ ጥልቁ ገደል ወደ ቀዝቃዛ ብቸኝነት ትጥላቸዋልች ። ስሜታቸውን ማቃለልና እንደውሻ ማድረግ ለምን እንደምትወድ ለራሷም አይገባትም . . . አሳዳጊ አልያም ወላጅ ብቻ የሰውን ልጅ የሚቀርጽ ቢሆን ኖሮ እሷ እንደ እናት አባቷ ደግና ሰው አክባሪ ትሆን ነበር ። ነገር ግን ሰው እንዲያድግ ሁሌም ትንሽ ይሆናል ፣ ከሱ የሚተልቁት ሁሉ ደሞ ወላጆቹ ፣ አሳዳጊዎቹ ይሆናሉ ። ማን ያጠባው ወተት እንደጣፈጠው ሳያውቅ ሰው ያድጋል ። መልኩንም ከማያውቃቸው ሁሉ ይዋሳል ። እንዳንዶች ራሳቸውን በመስታወት ሲያዩት ደስ ይላቸዋል ሌሎች ደሞ ያዝናሉ ። እሷ ግን ራሷን በመስታወት ባየችው ቁጥር ኩራት ቢጤ ልቧን ይነፋዋል ። 'ማን አለብኝ' ትላለች ። የወደዷት ወንዶች ከጥፍሯ የማይደርሱ በመሆናቸው እንዳሻት ታረጋቸዋለች።'ማን አለባት?'
ቡናቸው ተቀድቶ እየጠጡ በመሃል የህያብ ስልክ ጠራ ። ህሩይ መሆኑን ስታይ ተነሳችና ወደ ደጅ ወጣች ። ከባድ ጩኸት እያሰማ የሚጎተተው የጭነት መኪና እስኪያልፍ ድረስ ጠበቀችና "ሄሎ . . . " አለች ስልኩን አንስታ።
"ሄሎ ህያቤ . . . " አለ ወፈር ባል ድምጽ።
"ትደውላለህ ብዬ እኮ እየጠበቁህ ነበር ምነው ሳትደውል? በሰላም ነው?"
"ላስጨንቅሽ ብዬ አደለም ይቅርታ አድርጊልኝ . . . ?" አለ ድካም ባዘለ ወፍራም ድምጽ።
"አይ በሰላም ከሆነስ ጥሩ . . . እንደዛ ተቻኩለህ የወጣኸው ምን ሆነህ ነው?" አሁን ከጭንቋ ሁሉ ተገላገለች። ". . . ላታምኚኝ ትችያለሽ ግን . . . "
ሲያመነታ ታወቃትና "ምን? . . . ንገረኝ ችግር የለም?" አለች።
"ማታ እንደዛ ሲደወል የነበረው ስልክ ታስታውሻል አደል ? . . . ሳይለንት ካረኩት በኋላ መልክት ይላክ ጀመር ። መልክቱ ምን እንደሚል ታውቂያለሽ? . . . እናትህ ታማለችና ሆስፒታል ቶሎ ድረስ ክፍሉ 323 ነው ብለው ነው የላኩልኝ ። በጣም ነበር የተደናገጥኩት ግን አንቺንም መረበሽ አልፈለኩም ነበር ለዛ ነው ምንም ሳልልሽ ወደ ሆስፒታል የሄድኩት . . . "
"ምን ገጠማቸው . . . እንዴት ናቸው ?" አለች በመደናገጥ።
" . . . እረ እሷ በጣም ደና ነች እግዛቤር ይመስገን . . . የሆነውን ልነግርሽ አደል እንዴ . . . እየተጣደፍኩ ወደተባለው ሆስፒታል ሄድኩ . . . ወደ ተባለው ክፍል ገባሁ . . . ክፍሉ ውስጥ ግን ሌሎች ሰዎች ተኝተው አገኘሁ . . . መልሼ ልደውልልሽ ስል ስልኬ ዘግቶ ነበር ። ታምኚኛለሽ?"
"ምን?" ሳቋ ሊያፈተልክ እያለ "እና ምንም አልተፈጠረም ነው ምትለኝ?" አለች።
"ያ ሁሉ ወከባ ለምንም ነበር" አለ ምንም መጥፎ ነገር ባለመፈጠሩ ያዘነ ይመስል ።
ከልቧ ከት ብላ ስትስቅ ቆየችና "ግን ለምን ቀረህ ዛሬ ታዲያ?"
"እኔንጃ ለምን እንደሆነ? ጥዋት ስነሳ የሆነ ነገር ቅር ቅር ኣለኝ። የምሰራውን ስራ ከዚሁ ለመስራት ወሰንኩ "
"እንደዛ ከሆነ እሽ . . . "
"እሽ። " ትንሽ ቆየና "ወደ በኋላ ግን ልወጥ እችላለው . . . ከዛ እግሬ ወደመራኝ ልሄድ እችላለው "አለ።
ፈገግ እያለች "ከዛስ?"
"ከዛማ ትንሽ እራመዳለ ።"
"ከዛስ?" ፈገግታዋ እየጨመረ።
"ከዛ? ከዛማ እናንተ ሰፈር አጠገብ ያለውን ካፌ አወቅሽው ? . . . እዛ ትንሽ እቀመጣለው ። ከ10 ፡40 እስከ 12፡20 ማለት ነው።"
አሁንም እንደፈገገች "ትንሽ አይቆዩም የተከበሩ " አለች ።
"አይ እዛው አካባቢ አንድ የምሄድበት ቤት ስላለ የምቆይ አይመስለኝም . . ."
አውርታ ስትጨርስ ወደነሚሚ ተመልሳ ያወሩትን ሁሉ ነገረቻቸው። በተፈጠረው አስቂኝ አጋጣሚ ተገርመው ቡናቸውን ጨልጠው ወደ መስራቤታቸው አቀኑና ሁሉም ወደስራቸው ተመለሱ። ቲጂ ላፕቶፗን ከፍታ ከመነካካቷ በፊት 'ኢርፎኗን' ጆሮዋ ላይ ሰክታ ሰሞኑን ልትጠግበው ያቃታትን ዘፈን መስማት ጀመረች ። አንድ ሁለት ጊዜ መላኩ በፊቷ ሲያልፍ ያሳያትን ፈገግታ በፈገግታ ለመመለስ ቀና ከማለት ውጪ ሃሳቧን ምንም አልሰረቀውም ዘፈኑንም በአዙሪት ማድመጥ አላቆመችም።
ማታ ወደ 11 ሰዓት አካባቢ
ሚሚና ህያብ በጊዜ ከመስራቤታቸው ኮብልለዋል ። የሚሚ የተለመደ ቢሆንም የህያብ ግን በጊዜ መውጣት ባህሪዋ አልነበረም ። ለትግስት ስራዋን ብትጨርስም ጊዜው ከተቀመጠችበት ሳትነሳ እየሄደ ነው ። እየጠብቀችው ያለ ነገር ቢኖር የመላኩን መነሳትና ቀድሟት ከስራ መውጣትን ነው ። ያን ካላደረገ ስትነሳ ጠብቆ አብሯት እንደሚነሳ ገምታለች ። ልሸኝሽ ይላታል። ቤቷ እስክትደርስ ድረስ አሰልቺ ወሬ ሲያወራት ይቆያል። ያን አትፈልግም ። ቢሆንም ግን ማምለጫ ያላት አትመስልም ። ከሁለት ጊዜ በላይ ወደሷ ሲያይ ይዛዋለች . . . ሲፋጠጡ ማደራቸው ነው።
ወደ 10 ጉዳይ
መላኩ ከተቀመጠበት ተናሳ ። እንደማታየው ለመሆን ሞከረች ።ቀድሟት ሊወጣ እንደሆነ አስባ ተደስታ ሳትጨርስ ወደሷ እየመጣ እንደሆነ አወቀች ። ስራዋን ያልጨረሰች እንደሆነ ለመምሰል ሞከረች ፣ አንገቷን ወደቀፎዋ እንደምትሰገስግ ኤሊ አቀረቀረች ።
ብዙም ሳይቆይ "ትቆያለሽ?" አለ ከፊቷ የቆመው ጠይም ፣ ረጅም ፣ ወጣት ።
'አው እቆያለው ' ልትለው ብትወድም 'እጠብቅሻለው' ማለቱ እንደማይቀር አስባ "አይ . . . ለወጣ ነው" አለችው ቀና ብላ እየየችው ። በትንሹ ፈገግ አለና "ውጭ . . . እጠብቅሻለው " ብሏት ቀድሟት ወጣ።
ምንም ያልያዘችበት የሚመስለውን ቦርሳዋን በእጇ በመሰላቸት አንጠልጥላ ከህንጻው ወጣች ። መላኩ ወደ ላይ አንጋጦ ሰማዩን እያየ ነበር ። ከአጠገቡ መጥታ ቆማ "እንሂድ?" አለች ጉሮሮዋን ካጸዳች በኋላ። መንገድ ጀመሩ እያዘገሙ ። ከሁለቱም ምንም ቃል ሳይወጣ . . .
አልፎ አልፎ ቀና እያለች ታየዋለች ። የጠለቁና አቅም ያጡ ትላልቅ አይኖቹን እዚም እዚያም ያሳርፋቸዋል ፣ አልፎ አልፎም እሷ ላይ። ዝቅ ብላ አለባበሱን ትቃኛለች ። የቆዳ ሻራ ጫማ ፣ ጥቁር የጨርቅ ሱሪ ፣ ሱሪው ውስጥ ያልተወሸቀ ነጭ ሸሚዝ ፣ በላዩ ላይ ካኪ ጃኬት . . .
"እ . . . ዛሬ ጓደኞችሽ የሉም።" አለ ጉሮሮውን እየሞረደ።
"አው ባክህ ። " አለች።
"ጥሩ . . ." አለ ትንሽ ፈገግ እያለ ።
በተናገረው ነገር ግራ በመጋባት ቀና ብላ እያየችው "ለምን?" አለችው።
"እኔ ሆንኩ የምሸኝሽ ብዬ ነው . . . " አለና አይኑን ወዲያና ወዲያ መልሶ ማማተር ጀመረ። "እህ. . ." አለችና እሷም አቀርቅራ መገዷን መራመድ ቀጠለች። አሁንም በዝምታ ተውጠው መንገዳቸውን ቀጠሉ ። ቤቷ የምትገባበትን ሰዓት ብትናፍቀውም እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ ጥሩ ወሬ ፣ የቡና ቁርስ እንደሚወጣው ስታስብ ትንሽ ልታወራው ሞከረች ። "እ . . . ቤትህ ግን ወዴት ነው? እንዳላደክምህ?" አለች።
"ባለፍነው መታጠፊያ በኩል ነው።"
"ታዲያ ለምን ትለፋለህ . . . አላድክምህ?" አለች ። የሚለውን ለመስማት ።
መላኩ ራቱን የሚበላበት ካፌ ከፊት እንደሆነ አሳይቷት ራት አብራው ትበላ እንደሆን ጠየቃት ። ልትስማማ አልፈለገችም ነበር ነገር ግን ቤቷ የነበረው ብረት ድስት ሁሉ ባዶ እንደነበር አስታውሰች ። ከዛም በላይ የሚሆነውን ነገር ሁሉ ለመናገር ቸኩላለች ። ለዛም ተስማማች ።
ማታ 3:40 አካባቢ
ወደ ቤቷ እንደገባች ልብሷን ቀይራ እንቅልፏን ለመተኛት እየተዘጋጀች ባለበት ስልኳን ከቦርሳዋ አውጥታ ለናቷ ደወለች ። ስላለው ነገር ሁሉ ካወሩ በኋላ በቅርቡ መጥታ እንደምትጠይቃቸው ነግራቸው ተሰነባበቱ ።
ብቻዋን ፣ ባዶ ቤት ፣ የራሷ ሃሳቦች ብቻ ጮቅ ብለው ይሰሟታል ። ጭር ሲል የማትወድ አይንት ናት ። ለዛም ቀኑን ሙሉ ስትሰማው የነበረውን ዘፈን አሁንም ከፍታው አልጋዋ ውስጥ ገብታ መስማት ጀመረች ። ትንሽ ስትቆይ እየሰለቻት በመምጣቱ ጥፍሮቿን የቀባቻቸውን ቀለሞች ልታጠፋ ቦርሳዋን ስትበረብር ከተከፈተ የካኪ ወረቀት ውስጥ ያለ ደብዳቤ አገኘች ። ከማሸጊያው ጀርባ ለይ 'ላንቺ' በትልቁ ተጽፏል ።
ከፍታ ለማንበብ አልዘገየችም።
ከአንድ ቀን በፊት
"ወይ አንሳውና ምን እንደሚፈልጉ ጠይቃቸው" አለች የህሩይ ስልክ ያለማቋረጥ እየጠራ ስላስቸገራቸው ።
"ተይው ሳይለንት አደርገዋለው . . . ይህን የመሰለ ቀን እንዲያበላሹብን መፍቀድ የለብንም " ስልኩን ሳይለንት አርጎ ከጎኑ አስቀመጠው ።
ያዘዙት ምግብ ቀርቦላቸው እየተመገቡ ወይኑ ተቀድቶ እየጠጡ እያወሩ በጨዋታቸው መሃል ስራ ሊያቆም እንደሆነ ነገራት ምን እንደምታስብ አብሮ ጠየቃት ። ይሄኔ ስልኩ ላይ የገባውን መልዕክት ይመለከታል . . .
እሷን በላዳ ከሸኘ በኋላ ያረጀች ኮሮላው ውስጥ ገብቶ ወደተባለው አድራሻ ይሄዳል እየተጣደፈ ፣ እየከነፈ ። ከሆስፒታሉ ስር መኪናውን አቁሞ ወደ ውስጥ ገባ ፣ ከሚመጣው ታካሚ ኣካሚ ፣ ዘመድ ቤተሰብ ፣ ከሰዉ እየተጋጨ እየተቻኮለ 'ሪሰፕሽኖቹ' ጋር አቀና። እያለከለከ የተባለውን ክፍልና የእናቱን ስም ተናገረ
"ያልከው ክፍል የተያዘው በሌላ ታካሚ ነው . . . በነገርከኝ ስም የገባ ድንገተኛ ታካሚ የለም" አለች በርጋታ በችኮላ ለጠየቃት ጥያቄ ። የናቱ ስልክ አለማንሳት ያልተመለሰለት ጥያቄ ሆኖ እያለ ምላሿ በትንሹም ቢሆን አረጋጋው ። ከሆስፒታሉ በርጋት ወቶ ወደ መኪናው አቀና ።
ከመኪናው ገብቶ ራሱን ወደኋላው ደገፍ አርጎ ፣ አይኑን ጨፍኖ ፣ የተጣደፈው የልብ ምቱን ቀስ እያለ ሲረጋጋ እያደመጠ ፣ እናቱ ስልኩን አጮሁበትና አባነኑት።
"ደህና ነሽ እማ? . . . ደህና ነኝ እኔ . . . አንቺ ደህና ነሽ ? . . . አይ ስልክ አላነሳ ስትይ ነው . . . ች . . . ችግር የለም . . . እሽ . . . እሽ . . . ደህና እደሪ . . . እሽ ላንቺም" ደህንነታቸውን በዚህ መልኩ ካለጋገጠ በኋላ ለህያብ ሊደውልላት ፈለገ ፣ ተጨንቃ እንደሚሆን በማሰብ። አሁን የደወለ እንደሆን ግን ንግግራቸው አጭርና ምንም ስሜት የሌለው ይሆናል መኪናውን ቀደም ሲል አስነስቶት እንደመቆየቱ ። ስለሆነም አሁን ይስነሳትን መኪና ማንቀሳቀስን በኋላ ቤቱ ሲገባ ደሞ ከህያብ ጋር መነጋገርን መረጠ። እጆቹን መሪው ላይ ሰቀለና ። ከመውጣቱ በፊት ግን ፣ ካይኑ አንድ ነገር ይገባል። መስታወቱ ስር በውሃ ጠራጊው የተያዘ ወረቀት በቀዝቃዛው ንፋስ እየተውለበለበች ይመለከታል ።
በመጀመሪያ ያልሆነ ቦታ ቆሞ ትራፊክ ቀቶት እንደሆነ ነበር የገመተው በድጋሜ ሲያየው ግን እንደ ደብዳቤ ያል ነገር መሰለው ። የመኪናውን በር ከፍቶ በመውረድ ከተወሸቀበት መንጭቆ አውጣና ይዞት ወደመኪናው ተመለሰ ። በሩን ከዘጋ በኋላ ፣ ተደላድሎ ተቀምጦ ደብዳቤውን አገላብጦ ተመለከተው 'ላንት' የሚል ጽሁፍ ከጀርባው በኩል በደማቁ ፣ በትልቁ ተሞነጫጭሮበታል። ከፍቶ ማንበብ ጀመረ።
ይድረስ ላንተ
በልጅነት አእምሮዬ ይተራመሱ ከነበሩ ሃሳቦች ውስጥ አንዳቸው እንኳን እውን ቢሆኑ ኖሮ ትልቅ አደጋ ነበር የሚሆነው ። ለምሳሌ ያክል ራሴን ስፓይደር ማን አርጌ አስብና ጉልበተኞች እጅ የወደቀች አንዲት ምስኪንና የምታምር ልጅ አድናለው ያዳንኳት ልጅ ደሞ በኔ ትማለላለች። ምንም እንኳን ያለምክኒያት የሚጠልዙኝ ባይጠፉም ራሴን እንደጀብደኛ መቁጠር እወድ ነበር ። አቅሜን ገትቼ እንጂ ብፈልግ አፍንጫቸውን የማወልቅላቸው ይመስለኝ ነበር።ትምህርት ቤቱ በእሳት እየጋየ ከሆነ ደሞ እኔ ከመሃል ጭረት ሳይነካኝ የምወጣ ። ያስቃል አደል ? ትንሽ ከፍ እያልኩ ስመጣ ግን እነዚህ ጣሪያ የዘለሉ ሃሳቦቼን መሬት የረገጡ ለማረግ አብዝቼ መጣር ጀመርኩ ። እርግጥ ህይወት ባዘጋቸችው መድረክ ላይ የዋና ገጸባህርዩን ቦታ ወስጄ መጫወት መፈለጌን አላቆምኩም የተቀየረው ነገር ቢኖር የምጮተው ገጸ ባህሪ ያለበት የድራማ አይነት ብቻ ነው ። ቅድም አክሽን ነበር ከዛ የቀጠለው ደሞ ትራጄዲ ነው ። በዓለም ላይ ጀግና የሚባሉ ሰዎች ሃዘናቸውን ተሸክመው የሚኖሩ እንደሆኑ ተሰማኝ ። ለዛ ደሞ አሳዛኝ ነገር እንደሚገጥመኝ እያረኩ ራሴን አስብ ጀመር። በቅርቤ ካሉት ሰዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ሲሞቱ ያለውን አሳዛኝ ኑሮ ቀድሜ ለመኖር ቋመጠኝ ። አስቂኝ የሆነው ነገር ምንድን ነው በዛ ጊዜ የሚገጥመኝ አሳዛኝ የህይወቴ አጋጣሚዎች ሳይታዩኝ ነው ያለፉት ። ለምን? የጠበቋቸውን አይነት መልክና ቅርጽ ይዘው አልነበረም የመጡት ። ስጠብቀው የነበረው በቅርቡ ያለ ሰው እንደሚለየኝ አድርጌ ነበር መለየት ግን ብዙ ትርጉም ነው ያለው። ዩኒቨርስቲ ከገባሁ በኋላ ደሞ ህይወቴ የሮማንስ ድራማ የሆነ መሰለኝ ። የመጀመሪያ ቀን እንዳየኋት ነበር የወደድኳት ያም ማለት የመጀመሪያ ዓመት ላይ ማለት ነው ። አንድ ክላስ አልነበረም ያኔ ፣ ቢሆንም ግን እሷን ለማየት እያልኩ ወደነሱ ክፍል እየሄድኩ አንዳንድ ክላስ እማር ጀመር ። ልቀርባትም ሞክሬ ነበር ትልቅ ድንጋይ መሸከም ከዛ ይቀላል ብልህ ልታምነኝ ይገባል ። ቀጣይ ዓመት ላይ አንድ ዲፓርትመት ነበርና የመረጥነው አንድ ክፍል ተመደብን ።አሁን እሷን ፍለጋ ሩቅ መሄዱ ቀረ ከባዱ ስራ ግን በትንሹም ቢሆን አልቀለለም ፣ መቀራረቡ ማለቴ ነው። በአይይን መተያየት ብቻ ነበር ፣ ያው እሷ አታየኝም እኔ ሳፈጥባት እውላለው ። ሶስተኛ ዓመት ላይ ሰላም እንባባል ጀመር በመጠኑም ተቀራረብን ። አራተኛ ዓመት ላይ ፍቅረኛ እንዳላት አወኩ ። ከዛ ወዲህ ትልቅ ድባቴ ውስጥ ገባሁ ። ከብዙ ልፋት በኋላ የተገነባው መጠነኛ ቅርርብ ገደል ገባ። ባየኋት ቁጥር ያልነበረ ትዳራችንን አፍርሳ የሄደች ፣ ልጆቻችንን የትም የበተነች ነበር የሚመስለኝ የማገጠችብኝ ያክል ። ብዙም ሳይቆይ የምስራች ሰማሁ ፣ ከፍቅረኛዋ ጋር እንደተለያዩ አውኩ የፈረሰው ጎጆዬን ለመጠገን አሪፍ እድል እንደሆነ ተሰማኝና ተመልሼ ልቀርባት ሞከርኩ ። ይህን ሳረግ ያየው የቀድሞ ፣ የጥንት የጥዋቱ ፍቅረኛዋ ያደረሰብኝ ከባድ ድብደባ ይበልጥ እንድንቀራረብ አርጎን ነበር ። ዛቻና ማስፈራሪያውን ግን ስላላቆመ ራሷ እየራቀችኝ መጣች ። አንድ ሌሊት ከላይብረሪ ስንመለስ ተገናኘንና ትንሽ ተቀምጠን እንድንጫወት ጠየቋት ። ወሬ ጠፍቶ እየተፋጠጥን ብርዱ ከብዷት ስትንቀጠቀጥ አየኋት እና ደርቤው የነበረውን ጃኬት አውልቄ ልደርብላት ብሞክር ባለማማት ከተቀመጠችበት ተነስታ መርዶውን ነገረችኝ ። ለሷ የነበረኝን ስሜት ከጥንስሱ ታውቅ እንደነበር ነገር ግን መቺውም ቢሆን ምርጫዋ ልሆን እንደማልችል አረዳችኝ ። እንደምታዝን ነግራኝ ውደ ዶርሟ ተመለሰች። ሰማንያችንን በይፋ ቀደደች ። ልደግፋት የነበረችው ጎጇችንም መናዷ አልቀረም። ደግነቱ በሰዓቱ የቀድሞፍቅረኛዋ ዶርሜ ጋር እየጠበቀኝ ነበር ደና አርጎ ቀጠቀጠኝና እልሄን አበረደልኝ ። ከዛ ጊዜ ወዲያ አይኗን ደፍሬ ላይ አቃተኝ ። ፍቅር እስከመቃብር ሳይሆን ፍቅር ያስብላል ቅር የሚል ስም ሰጥቸዋለው ። አክሽን ፣ ትራጄዲ ፣ ሮማንስ ቀጣይ ደሞ ኮሜዲ ነው ። ተመርቄ ከወጣኡ በኋላ ሁሉም ነገር ትርጉም እንደሌለው ፣ የህይወትን ትርጉም ማወቅ እንዳለብኝ ደነገኩ። መርሁ በራሱ አስቂኝ ነበር አሁን ትርጉም የለም አሁን ደሞ ትርጉሙን ማወቅ እና ጥዋት ከእንቅልፌ ስነሳ ሞቼ በተገኘሁ እልና ምታ ልተኛ ስጋደም ደሞ ትንሽ ቆይቼ ሁሉን ነገር ባወኩ እላለው። የፍልስፍና መጻህፍትን ማንበብ እውነት ፣ ፍቅር ፣ ደግነት ምንድን ነው እያሉ መጠየቅና ፈላስፋዎቹ በሄዱበት ዱካ መከተል አስቂኝ ነበር ። የዚህች አለም እውነታ ጠባብ በሆነው የሰው አእምሮ ሊጠቀጠቅ አይችልም ። ወይ አእምሮው ፈንድቶ ያብዳል ወይ ደሞ እውነታው ይጠባል ። ማንም እውነቱን በሙሉ ያወቀ የለም አእምሮው በቻለው መጠን ጥሯል ጥረቱ ግን መቼም ቢሆን በቂ ሁኖ አያውቅም ። የሚታይ ነገር እንዳለ ሁሉ መንገድ ዳር እቀመጥና ሃላፊ አግዳሚውን እመለከተዋለው ከነሱ የተሻለ እንደማውቅ ሁኜ ወይ ደሞ እነሱ ምንም የማያውቁ እንደሆኑ ሆነው ወይ ለማወቅ መጣሩ ያለውን ፈተና በመረዳት እጃቸውን ሰጥተው እንደሆኑ እኔ ግን ጀብደኛ እንደሆንኩ ከባዱን እውነታ መሸከም እንደምችል ሁሉ ሆኜ ። ፍልስፍናዎቹ በአብዛኛውን ወደ አሳዛኝ መጨረሻ የሚያመሩ እኔ ደሞ ከዚ ቀደም ተሻግሬው የመጣሁትን ትራጄዲ ለማምለጥ ስፍጨረጨር ሳላስበው በራሴ ውስጥ ሌላ ሰው ፈጥሬ ከሱ ጋር ነበር ማወራው የነበረው ። አንዳችን እንጠይቃለን አንዳችን እንመልሳለን ብዙ ጊዜ የሚጠይቀው አዲሱ ነበር የኔ ስራ መልስ ማምጣት ነው መልስ ያላመጣሁ እንደሆነ ሙልጭ አድርጎ ይሰድበኛል ። እየቆየ ሲመጣ በሆነ ባልሆነው ይሰድበኝ ጀመር ። እኔን ብቻ ሳይሆን መንገድ ላይ የሚያየውን ማንኛውም ሰው መዘርጠጥ ያዘ። እሱ በሚያሳያቸው አኳኋኖች እኔ ትልቅ ችግር ውስጥ እገባ ነበር ። እሱ በገላመጠው እኔ እሰደብ ነበር። እሱ በኮራው እኔ እናቅ ነበር። እሱ በተዳፈረው እኔ እገፋ ነበር ። እንዲህ ባለ ሁኔታ እንኳን የህይወት አጋር ፍለጋ ቀርቶ ለራስም በቅጡ መሆን አይቻልም ግን እግሬ አላረፈም አንዲት መንደራችን ውስጥ በቅርቡ የገባች ወጣት ወደድኩና ከሷ ጋር ራት ልንበላ ወደ አንድ ካፌ ሄድን አዲሱ ያለወትሮ ተረጋግቷል ። አኳኋናንም ሆነ የምታረገውን ነገር እየገመገመ አልነበረም ለኔም ፋታ ሰጠኝ ። ይህ የሰጠኝ እረፍት ግን ረጅም ሰዓት አልቆየም ። ራታችንን በልተን ወይን ቀድተን እየጠጣን እያለ ስለወደፊቱ ምን እንደማስብ ጠየቀችኝ ። ስለወደፊቱ ምንም እንደማላስብና ምንም ባስብ ጥቅም እንደሌለው ነገርኳት ። አሁን ላይ የተረዳሁት ጥያቄዋን መመለስ የነበረብኝ ተጋብተን ልጆች ወልደን ገለመሌ ብዬ እንደነበር ነው። በዛ ጥያቄ የተነሳ ክርክር ገባን ። ተስፋ የቆረጥኩኝ እንደሆነና ግድ እንደሌለኝ ነገረቺኝ እኔ ደሞ በምላሹ የምናስበውና የምናረገው ማንኛውም ነገር ከኛ ቁጥጥር ውጭ እንደሆነ ላስረዳት ሞከርኩ ነገ ሚባል ነገር እንደሌለና ስለነገ የሚጨነቁ ሰዎች ሞትን ፈርተው ራሳቸውን ከእውነታ በራቀ ተስፋ የሚያጠረቁ ፈሪዎች እንደሆኑ ፣ ዛሬ ብሞት የማልጠላ መሆኔን ነገርኳት። ሰው ያለተስፋ እንዴት ሊኖር እንደሚችል ስትጠይቀኝ ራሱን በመቀበል እንደሆነ ነገርኳት ተስፋ የሚያረግ ሰው ማድያቷን በሜካፕ ደብቃ ውበቷን ያጎላች እንደሚመስላት ሴት እንደሆነ ስነግራት ስትጠጣው የነበረውን ወይን ፊቴ ላይ ረጭታው ወጣች። ምን እንዳበሳጫት በርግጥ አልገባኝም ነበር ኋላ ላይ ከናቷ ጋር ሁና መንገድ ላይ ተያየንና ነገሩ ተገለጠልኝ ። አዲሱ ብዙ ችግር እየፈጠረብኝ እንደሆነ ስረዳ ልገለው ተነሳሁ ። እንዴት? የኔ ያልመሰለኝ ድምጽ ከአእምሮዬ በመጣ ቁጥር ድብን አርጌ እሰድበዋለው። አንተ መሃይም ፣ ቀፎ ፣ ደሞ አንት ምን አውቀህ ነው ? ፣ ደሞ አንተም ሰው ልትመክር ሆነ ፣ ማፈር አልፈጠረብህም መሰለኝ እያልኩ አሽማቅቀው ያዝኩ። በጊዜ ሂደት ግን ሳሸማቅቀው የነበረው ራሴውኑ እንደ ነበር አወኩ ። በጭላንጭል የቀረችው በራስ መተማመኔ ተሟጣ አለቀች ። አስቂኙን ዘውግ እንዲህ አርጌ ተሰናበትኩት ምን ቀረ ? ልብ አንጠልጣይ ወይም ትሪል ! ! ! ሸገር ሆቴል ክፍል 344 ኮመዲኖው ስር ያለውን ደብዳቤ ፎቶው ላይ ላለችው ልጅ በ24 ሰዓት ውስጥ አድርስላት ። አንተ መሆንህን ማወቅ የለባትም ። ላንተ ከሚለው ደብዳቤ በቀር ማንበብ አትችልም።
ያንተው














You've reached the end of the current published chapters.