FEATURE • SCREENPLAY
ታሪክ እንደ ተረት
by ተክለወልድ ተክለአልፋ
Paginating script...
EXT.ሰፈር ውስጥ - ቀን
ሰፈሩ ከዚ በፊት በተለያዩ ፊልሞች ላይ የምናውቀው የ'ሎው ክላስ' ሰፈር ነው። የዛጉ ቆርቆሮዎችና የወየቡ የስልክ እንጨቶች ከአይን የማይጠፉ ነገሮች ናቸው ። እናም ከአንድ ከዛገ ቆርቆሮ ጀርባ ተቀምጠው የሰፈሩ ጎረምሶች ድዳቸውን እያሰጡ ነበር ። ምን አይነት እንደሆኑ መናገር አይጠበቅብንም ፣ ድድ የሚያሰጡ አይነቶች ስለሆኑ። ከነሱ ብዙም ሳይርቁ ህጻናቱ ያለቀ ልብሳቸውን መሬቱን ከሸፈነው ቀይ አፈር ላይ እያንፏቀቁ ፣ ያለቀ ሲልፐራቸውን አየደፈጠጡ ፣ ጣቶቻቸው ሊያፈተልኩ እያሉ ብይ ይጫወታሉ ። የተሰጣውን ልብስ እንዳይነኩ በተነሱና በተቀመጡ ቁጥር አጎንብሰው ነው ። ጸሃዩዋ ትሞቃለች ፣ ከቆርቆሮው ስር የተቀመጡት ጎረምሶችን እንዳታቃጥላቸው ቆርቆሮ ከሸፈነው ግቢ የተመዘዘው የዛፍ ቅርንጫፍ ይሸፍናቸዋል ፣ ህጻናቱ ደሞ ንዳዱን አያስተውሉትም ። እንዲህ ባለ ሁኔታ ተቀምጠው እያለ ድዳቸውን ከሚያሰጡት ጎረምሶች መሃከል ስልክ እንጨቱን ቆሞ የተደገፈው አንዱ
ጎረምሳ 1
እረ መጣች መጣች . . .
ጎረምሳ 2
ማ?ማ?
ሁሉም የመጀመሪያውን ጎረምሳ በአይን ይከተሉትና ከሩቁ እግሩ በጨርቅ ተጠቅልሎ ከዘራውን ተደግፎ እየመጣ የነበረውን ቀጠን ያለ መካከለኛ ቁመት ያለው ወጣት ይመለከታሉ ። ጉልበቱን የሚሸፍን ሰፋፊ ኪስ ያሉት ቁምጣ አድርጓል ፣ ከላይ አነስ ያለ ትሸርት ። ሉጫ ጸጉሩ አድጎ ወደፊቱ ተደፍቷል ተንጨባሮ ።
ጎረምሳ 3
አው አው . . . ኤባ ጀምሪ . . .ጀምሪ ዝፈን
በድንገት ከጎኑ የተቀመጠው (ኤባ) ጭኖቹን በእጆቹ እየመታ መወዛወዝ ይጀምራል። በዙሪያው ያሉት ራሳቸውን በመረቅነቅና አንዳንድ ጩሀቶችን በማውጣት ይተባበሩታል ። የሚዘፍኑት የቦብ ማሌን could you be loved የሚል ሙዝቃ ቢሆንም ግጥሙ ግን ከራሳቸው ነው።
ኤባ(በዜማ)
በቆንጆ ቢላ . . . በቢላ (2)
ጎረምቹ
ፓራም ፓ ፓራም ፓ ፓ ፓራራ . . .
(በየመሃሉ)
ኤባ(በዜማ)
ኮቴውን አጥፍቶ . . .
EXT. ሰፈራቸው ውስጥ - ማታ
ጨራቃ ሙሉ ሆኗ ትትያለች ፣ ሰፈሩ ግን ጨለማ ነግሶበታል ፣ በጠባቡ የሰፈራቸው መንገድ ቀደም ሲል እግሩን ተጠቅልሎ ያየነው ወጣት ሲራመድ እናያል
ኤባ(V.O.)
ሁሉም ሰው አንቀላፍቶ . . .
የኛ ሰፈር ወጣት ሚገባበት ጠፍቶ
መሽቶ . . . አይ?
(አዝማች ይቀጥላል-በቆንጆ ቢላ)
ወጣቱ ፈጠን እየለ ዙርያውን እየገላመጠ ይሄዳል ። በጠባቡ መንገድ
EXT.ሰፈር ውስጥ - ቀን ፣ የቀጠለ
ወጣቱ እያነከሰ ሲቀርባቸው ወደሱ እያዩ የነበሩት ጎረምሶች እይናቸውን እዛና እዚህ አድርገው ምዝፈናቸውን ቀጠሉ
ኤባ
በቆንጆ ቢ ቆንጆ ቢ ቆንጆ ቢላ ቆንጆ ቢ ቆንጆ ቢላ(2)
EXT. ሰፈራቸው ውስጥ - ማታ የቀጣለ
ኤባ(V.O.)
የራሱን ጥላ ፈርቶ . . . በመንገድ ላይ ሰው አቶ
ቀን ጠብቆ መጮህ ሽለላ ቀረርቶ . . . ላይጠቅም ከቶ
(አዝማች ይቀጥላል - በቆንጆ ቢላ)
በፍርሃትና በመደናገጥ የሚራመደው ወጣት በድንገት ይቆማል ከፊቱ ከነበረው ጨለማ ግዙፍ ጥላ ብቅ ይላል ። ጥላው በጁ የያዘው ቢላ ከወጣቱ አይን ያንጸባርቃል ። ወጣቱ በመፍራት ወደኋላው ሊመለስ ይላል
ኤባ(V.O.)
ጀግና ነኝ ምን እያለ ሲጎርር ሲደነፋ
ወደኋላው እንዳይመለስ ከኋላውም እንዲሁ ሌላ ግዙፍ ጥላ ብቅ አለና ቢላውን አንጸባረቀበት
ኤባ(V.O.)
ከመሸ ከጨለመ የታለ ልቡ ጠፋ
ሚገባበት ጠፍቶት ሊሮጥ ቢልም ጥላው ይይዘዋል ። ይጥለዋል ። ሌላኛው ጥላ ከመምጣቱ በፊት ወጣቱ የያዘውን ጥላ በግሩ መቶ ሊያመልጥ ሲንፏቀቅ የተመታው ጥላ በንዴት እግሩን በያዘው ቢላ ይወጋዋል
ኤባ(V.O.)
በቆንጆ ቆንጆ ቢላ አግሩን ማታ ሲነፋ . . . አይ
በቆንጆ ቢ ቆንጆ ቢ ቆንጆ ቢላ ቆንጆ ቢ ቆንጆ ቢላ
EXT.ሰፈር ውስጥ - ቀን ፣ የቀጠለ
ወጣቱ ለአፍታ አየት ካረጋቸው በኋላ እያነከሰ መንገዱን ቀጠለ ። ጎረምሶቹም እያጨበጨቡና እየሳቁ ካሳለፉት በኋላ የሚጠብቁትን አይነት ግብረ መልስ ስላላገኙ ብዙም ሳይደሰቱ ምናልባትም አፍረው ወደነበሩበት ዝምታ ይመለሳሉ ።
እየተፈጠረ የነበረውን ነገር በግርምት ሲመለከቱ ከነበሩት ህጻናት ውስጥ አንደኛዋ ከሚውለበለቡት ልብሶች መሃል ቆማ ወደ ጎረምሶቹና ጀርባውን ሰጥቷቸው ወደሚጓዘው ወጣት ትመለከታለች ። ጸጉሯ ተንጨባሯል ፊቷም ወዝ የለውም እንደሌሎቹ ህጻናት ሁሉ። ትላልቅ አይኖቿን ወደስጥ ሰግስጋ ትመለከታለች ፣ በአትኩሮት ።
ሃና(V.O.)
ያደኩበት ሰፈር ሁሉ ሰው ቅጽል ስም ነበረው ።
ታዲያ አንድ ሰው ሌላውን ሰው ከጠላው ከተቀየመው ወይም ካኮረፈው በቅጽል ስሙ መጥራቱን ያቆምና በሙሉ ስሙ ይጠራዋል . . . እያነከሰ ሲገባ የነበረው ሰው ስሙ ስንታየሁ ደስታዬ ይባላል ። የሰፈራችን የሙዚቃ ባንድ ስለሱ የተናገሩትን ከቁም አትቁጠሩት። እንደዛ ያለ ነገር አልተፈጠረም ። የተፈጠረው . . .
ሲጫወቱ ከነበሩት ህጻናት ከሁሉም በእድሜ የሚያንስ የሚመስለው ፣ ቁጢጥ ብሎ ከተቀመጠበት ማውራት ሲጀምር ህጻኗ ሃና ወደሱ ትዞራለች።
ህጻኑ
እኔ እውቃለው! እናቴ ነግራኛለች ።
INT. ፖሊስ ጣቢያ - ቀን
ወጣቱ ከፖሊሱ ፊት ለፊት ቆሟል ። ፖሊሱ ደሞ እጁን እያውለበለበ እየተቆጣው ነው ።
ህጻኑ
እ? . . . ጸጉሩን ስላልተቆረጠ ፖሊሱ ወሰደውና ፖሊስ ጣቢያ እ?. . .
ፖሊሱ ወጣቱ እግሩን ጠረጴዛው ላይ እንዲሰቅል ያዘዋል በምልክት ። ወጣቱ እግሩን ይሰቅላል። ፖሊሱ ልብሱን እንዲሰበስብ ያዘዋል ፣ ወጣቱ በመሰላቸውት ያረገዋል ። ፖሊሱ በርከክ ይልና ከወገቡ የታጠቀውን ሽጉጥ አውቶ እግሩ ላይ እያነጣጠረ ቀና ብሎ ወጣቱን የሆነ ነገር ይለዋል ወጣቱ ምንቸገረኝ በሚመስል መልኩ ትከሻውን ይነቀንቅበታል ፖሊሱ ፊቱን ይመልሳል
ህጻኑ(V.O.)
ጸጉሩን አልቆረጥ ስላለ . . . ፖሊሱ ተኮሰበት
ፖሊሱ ይተኩሳል
ህጻኑ(V.O.)
ከዛ እያለቀሰ . . .
ወጣቱ እንደተቆነጠጠ ሁሉ ህመሙን ዋጥ አድርጎ ፣ እምባው ከአንዲቷ አይን ፍስስ ስትል
EXT.ሰፈር ውስጥ - ቀን ፣ የቀጠለ
ሌላ ህጻን
እረ እረ ስሚማ ምን እንዳለ
ወደ ሌላኛዋ ከጎኑ ተቀምጣ ወደነበረች ልጅ እየተጥራ እየሳቀ
ሌላ ህጻን
ቦቸራ እግሩን ያመመው ጸጉሩን ስላልተቆረጠ ፖሊስ ተኩሶበት ነው . . .
(ይስቁበታል)
ሃና(V.O.)
ህ! ይሄንንም ከቁም አትቁጠሩት
መልሳ ወደልጆቹ ትመለከታለች ። አገር ሰላም ብለው በተቀመጡበት ከቆርቆሮው ጀርባ የእጣቢ ውሃ በባልዲ ቁልቁል ወደ አናታቸው ሊወርድ ሲልና ሚገቡበት ሲጠፋቸው 'freeze frame' በጥቁርና ነጭ ፎቶ ።
ሃና(V.O.)
እግሩን ምን እንደሆነ ለማወቅ ወደኋላ እንመለስ ከ4 ዓመት በፊት
የፊልሙ ኢንትሮ ሃበሻ ልብስ ለምሰው በሚጨፍሩ ጥቋቁር የሰዎች ስዕል እየተመላለሰ ፣ "eyeye" በሚለው የ'either orchestra' የመድረክ ስራ ታጅቦ ይጀምራል።
ext. የካፌው በረንዳ ላይ - ወደ 10 ሰዓት አካባቢ
ኢንትሮው ካለቀ ወዲያ ስናያቸው የነበሩት ከካፌው ግድግዳ ላይ የነበሩ ስዕሎች እንደሆኑ እናያለን ። ሙዚቃው ይደበዝዛል። ካፌውም ደጅ ላይ ወጣቱና አንዲት ሴት ሆነው ይቀመጣሉ። ሴቲቱ ቀይና እጅጉን የምትማርክ ነበረች ። ወጣቱ ፊቱን ቁዋጥሮ ሲመለከታት ቆየና
ቦቸራ(ስንታየው)
አልገባኝም?
ሩት
ምኑ?
ቦቸራ
አልገባኝም? ድንገት ተነስተሽ እንዴት?ያረኩሽ ነገር አለ?
ሩት
ምንም አላረከኝም
ቦቸራ
ታዲያ ለምን እንደዚ ትያለሽ? ሩት?ስንት ዓመት ነው አብረን የቆየነው?
ሩት
በድንገት ተነስቼ ያረኩት ነገር አደለም ቦቸራ! በሃሳቤ የነበረ ነገር ነው ። እስከዛሬ ልነግርህ ድፍረቱን ስላጣሁ ነው ያልነገርኩህ ? እባክህ ቀለል አርገህ እየው?
ቦቸራ
እንዴት ነው ቀለል አርጌ የማየው !!! ትናንትና ልጆች ወልደን ቤት ገዝተን ምናምን ስትይ ቆይተሽ . . .
ሩት
ድምጽህን ቀንስ . . . ትናንትና ነዋ . . . ሰው እያየን ነው አትጩህ
ቦቸራ
ለምንድን ነው ማልጮኸው ?!እስከለተ ሞቴ ድረስ ያለውን ህይወቴን ካንቺ ጋር ነው የሳልኩት ? ለምንድን ነው ማልጮኸው ?!!
ሩት
ተነስቼ እሄዳለው . . . አትጩህ
ቦቸራ
እሺ እሺ ፣ አልጮህም። ተቀመጭ?
ሩት
አትጩህ
ቦቸራ
እሺ
ሩት
አየህ አደል? አንደኛው ምክንያቴ ይሄ ነው። ከራስህ ውጪ የምታስብለት ሰው የለም
ቦቸራ
ምንድን ነው ምትይው ፣ አፈቅርሻለው ።
ሩት አይኗ እምባ ያቀራል።
ቦቸራ
ትናትና ያልሽኝን ታስታውሻለሽ? 3 ልጆች ነው ምፈልገው? አንድ ሴት አንቺን ምትመስል ? 2 ወንዶች እኔን የሚመስሉ? ባንድ ሌሊት ሃሳብሽን ምን ቀየረው?
ሩት
በምን ታኖራቸዋለህ?
ቦቸራ
ምን?
ሩት
ከሰማይ መና ይወርድልሃል?
ቦቸራ
ስራ እየፈለኩ ነው። ቤቱ ደሞ የቀበሌ ነው። ገንዘቡ ከሆነ ያሳሰበሽ በዚም ብዬ በዛ ማምጣቴ አይቀርም።
ሩት እምባ ያቀረሩትን አይኖቿን በያዘችው ሶፍት ጠረግ ጠረግ አረገችውና ፣ ትክ ብላ ስትመለከተው ቆየች ። ቦቸራ ፈገግ ማለት እንደጀመረ ።
ሩት
ራስህን ጠብቅ ስንታየው . . .
ብላ ተነስታ ትሄዳለች ። ቦቸራ በተራው እምባ ባቀረሩት አይኖቹ ደረጃውን ወርዳ እየሄደች ያለችውን ፣ መለስ ብላ ምታየውን ሩትን ትክ ብሎ ተመለከታት ። ዘፈኑ ጡዘቱ ላይ ሆኖ ይቀጥላል ።
ሃና(V.O.)
እንዲሁ እንደዋዛ የግሯ ጎኔ የሚላት ሴት በስሙ ጠርታው ተሰናበተችው ፣ ተለየችው ። ምክንያቷን እንኳን በቅጡ ሳታረዳው ።
INT. መጠጥ ቤት - አመሻሽ
ጠበብ ያለው መጠጥ ቤት ጸሃይ ከጠለቀች ወዲያ እንደሚሆነው አልተጨናነቀም ፣ አዝጋሚ ክላሲካል በትንሹ ተከፍቶ ደምበኞቹን በመጠባበቅ ላይ ነው ። ከመሃከል የተሰቀለው መብራት የሚለቀው ነጭ ብርሃን ወደጠባቡ ክፍል ጥጋ ጥግ ሳይደስ ይመለሳል ፣ ከጥጋ ጥጎቹ አንዳንድ ሰዎች ቆዝመዋል ፣ በጭስ እንፋሎት ተደብቀዋል ። የተቀመጡትን ሰዎች የምትቃኘው እመቤት ለተደረደሩት መጠጦች ጀርባዋን ሰጥታ ባልኮኒውን ተደግፋ ከእኛ እይታ ውጭ ወዳለው ነገር ትክ ብላ ታያለች። ጠባቧ መጠጥ ቤት አምሽተው በሚመጡ ደምበኞቿ እንድትጣበብ እየተመኘች ፣ የቆዩት ነጭናጥቁር እምነበረዶች በአዲስ ጠጪዎች ኮቴ እንዲራኮት እየናፈቀች። ከአንዱ ጥግ ድራፍቱን አቅፎ የተቀመጠው ስንታየው እንዲሁ የሚናፍቀውን ሰው በአይነ ህሊናው እያየ ወደምንም አፍጧል ። የግደጋው ሰዓት ይነጉዳል ። ጠባቧም መጠጥ ቤት የጽሃይን መጥለቅ ተከትሎ ተጣበባለች ፣ አዝጋሚው ሙዚቃ ቀርቶ በሰዎች ጩኸትና ሳቅ ተተክቷል። ሞቅ ያለው አንዱ ድራፍት ያረገዘ ሆዱን ወደየሰዉ እየጠቆመ ከተቀመጠበት ተነስቶ ከተከፈተው 'ዥዋዥዌ' የተነኘው የአብዱ ኪያር ሙዚቃ ጋር ይዘፍናል በዙሪያው የተቀመጡትም መሰሎቹ በጭብጨባ ይደግፉታል ፣ በ40ዎቹ ውስጥ ያሉ የወንዶችና የሴቶች ስብጥር ። አንዳንዶቹ ወደሱ እያዩ ስለነበር የሚያጨበጭቡትና የሚስቁት የሚያሾፉበት ይመስል ፣ ስንታየው ወደነሱ ከማየትና በደስታቸው ከመቅናት አልተቆጠበም ። የጨበጠውን ድራፍት ይበልጥ ጨበጠው በንዴት። ከሚጨፍሩት ሰዎች አጠገብ የምሽቱን መንገድ ከመንገዱም ወዲያ ጉራንጉር ሰፈራቸውን የሚያሳየው አነስ ያለ በር ወለል ብሎ ተከፍቷል። የሚገባው ቀዝቃዛ አየር በሰዎች ትንፋሽና ላብ እየተረታ የክፍሉን ሙቀት በበሩ ሊያወጣው አልቻለም ። ዘረጦው ከተቀመጠ ወዲያ ከጎኑ የነበረች ሌላ ዘረጦ ተነሳችና ወፍራም ሰውነቷን አጥወለወለችው ። ከስንታየው በቀር ሌላው ሰው በድርጊታቸው እየተዝናና ነበር ። የጨበጠውን መጠጥ በጉሮሮው አንደቀደቀው። ይህን ሲያደርግ ያያው ከመጨፍሩት መሃከል የተቀመጠ ከሌሎቹ በአንጻሩ ሸንቀጥ ያለ ጉረኛ ቢጤ ፈገግ በማለት ከጎኑ ለነበረችው ልጅ በጆሮዋ የሆነ ነገር ይላታል ። ሲነግራት ቀና ብላ ወደ ስንታየው ትመለከትና ፈገግ ትላለች ለመደበበቅ ሳትሞክር። እያየችው ይበልጥ ፈገግ ትላለች ። ስንታየው ግምባሩን ቋጥሮ እየተመለከታቸው ፣ አስተናጋጁ መጥቶ ሌላ ቢራ ያመጣለታል ።
ይህ እየሆነ እያለ አነስ ባለችው በር በኩል አንድ ሰው ገብቶ ይቆማል ። ረዘምና ደንደን ያለ ሰውነቱ ኮስተር ካለው ፊቱ ጋር ይሄ ነው የማይባል ግርማ ሰጥተውት ከበሩ ስር ተቀምጠው የነበሩት ሴቶች ቀና ብለው ማየታቸው አልቀረም ። ዙሪያ ገባውን ከቃኘ በኋላ ስንታየውን ሲያየው ፈገግ ብሎ ወደሱ አቀና ሴቶቹ በአይናቸው ሸኙት ።
ማራኪው ወጣት በአይኑ ከባልኮኒው የነበረችውን እመቤት ጠቀስ አረገና ከስንታየው ፊት ለፊት ሄዶ ተቀመጠ። መሽኮርመሟንና መደሰቷን ሳያይ ሲሄድ የነበረውን አስትናጋጅ ክንዱን ይዞ
ባርች
እንዴት ነህ አምበሳው? . . . አንድ ቢራ
አስተናጋጁንም ሊጠቅሰው ምንም አልቀረው ።
ሃና(V.O.)
ቅጽል ስም የሚወጣባቸው መንገዶች የተለያዩ ናቸው። አንዳንዴ የነገሮችን ተቃራኒ ለነገሮች እንሰይማለን ። ቀጭኑን ሰው ደቦጭ ማለት ባይለመድም ወፍራሙን ሰው ግን ቀጮ እንላለን ። አሁን ቆመው ከሚጨፍሩት ቀጮዎች በኩል አቋጦ የገባው እንደበረዶ የቀላው የሰፈራችን ነዋሪ ባርች ይባላል ፣ በተቃራኒው።
ባርች
ስልክህን ለምንድን ነው ማታነሳው?
ስንታየው
ጥላኝ ሄደች
ባርች
ማ? ሩት?
(በራሱ ቀልድ ይስቃል)
ስንታየው ራሱን ይነቀንቃል ።
ባርች
አትመለስም?
(ድጋሜ ይስቃል)
ስንታየው
በሙሉ ስሜ ጠርታኝ ስንታየው ብላኝ ሄደች ።
ባርች
የምርህን ነው እንዴ?
(ቢራው ሲመጣለት ራሱን በመነቅነቅ አስተናጋጁን እያመሰገነ)
ስንታየው
ሰው ባንድ ሌሊት እንዴት ይለወጣል ?
ባርች
ቆ ቆ ቆ ቆ ቆይ? አልገባኝም? ከትንሿ ጋር ተለያየን ነው ምትለኝ?
ሃና(V.O.)
አንዳንዴ ደሞ ሁለት አንድ አይነት ስም ያላቸው ሰዎች ካሉ ትንሿ ትልቋ የሚል ቅጽል ስም ይወጣላቸዋል
ባርች
መቼ? ለምን?
ስንታየው
ከ5 ደቂቃ በፊት . . . 'ስንታየው ራስህን ጠብቅ' ብላኝ ሄደች
በድንገት የሁለቱንም ትከሻ መታ መታ አድርጎ ከአጠገባቸው ይቆማል ፣ ሁለቱም ቀና ብለው ያዩታል። ተሰድረው የተደረደሩት ጥርሶቹን ብልጭ እይደረገ እያሳያቸው ፣ ወዝ ያጠመቀውን ጥቁጥ ፊቱን እያብለጨለጨባቸው ቁልቁል ያያቸዋል ፣ ነጭ ብርሃን የሚተፋውን አምፖል እየጋረዳቸው።
ከጎኑ የነበረውን ወምበር ሊስብ በእጁ ሲጨብጠው ጣቱ ላይ ካለው ቀለበት ጋር ሲጋጭ እናስተውላለን። ከተቀመጠ በኋላ
ባርች
ከሩት ጋር ተለያዩ?
ጃምቦ
እኔ ደሞ 5 ሚሊዬን ብር መሬት ላይ ወድቆ አገኙሁ ዛሬ?
(መልስ አልነበረም)
የምርህን ነው እንዴ?!
ሃና(V.O.)
አሁን የመጣው ሸበላ ጃምቦ ይባላል ። አባቴ ነው ።
ጃምቦ(O.S.)
ለምን?
ስንታየው
አላውቅም? ምንም ነገር አላቸኝም?
ባርች
ምንም?! ምንም?!
ስንታየው
ትናንት ማታ ልጆች ወልደን ምናምን ስትለኝ ነበር ትናንት እንደዛ ብለሽ ዛሬ እንዴት እንደዚ ትያለሽ ስላት ምን ታበላቸዋልህ አለችኝ? ምንድን ነው ያለችው መና ከሰማይ ይመጣልሃል ነው ምናምን እንደዛ ነገር አላቅም
ለተወሰነ ደቂቃ በዝምታ ይቆያሉ ። ስንታየው የቅድሞቹን ሰዎች ይመለከታቸዋል ። አሁን ላይ ከዘፈኑ ይልቅ በራሳቸው ጨዋታ እየተዝናኑ ነው ፣ እየተሳሳቁ ።
ባርች
ከኔ ምክር አይጠበቅም ምከረኝ ካልከኝ ግን ፣ ቀለል አርገህ እየው ፣ ሴቶች አህ . . . ምን ያህል ጊዜ አብራቹ እንደቆያቹ ምናምን እርሳው እና ወደፊት ልታገኛቸው ስለምትችላቸው ሴቶች አስብ ፣ የጸሃዬን ዘፈን ታስታውሰዋለህ? ግጥሙን? 'ሸምበቆ ቢረዝም ፍሬ አያንጠለጥል የዚችና የዛች ጥዕማቸው ለየቅል' እ?
ጃምቦ
ፍሬ የሌለው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ?ያንተ ንግግር
ባርች
ቁም ነገር እያውራሁ አደል እንዴ ለምንድን ነው ምትቀልደው ?
ጃምቦ
ካንተ ቁምነገር የኔ ቀልድ ብዙ ቁም ነገር አለው ።
ዛሬ መንገድ ላይ እየሄድኩ ብርቅዬን አገኘኋቸውና የተሸከሙትን ተቀብዬ እየሸኘኋቸው
ባርች
ብርቅዬ የቷ?
ጃምቦ
የሚረሱት ብርቅዬ? . . . ከሳቸው ጋር እየሄድን? 'ባለፈው ባርችን ከናቱ ጋር አየሁት' አሉኝ። ረስተው ነው ሚሆነው ብዬ እኔ 'ነፍሳቸውን ይማር እናቱ አርፈዋል ' ስላቸው ምን አሉ? 'ታዲያ ያቺ አሮጊት ማን ናት?' . . . 'አሮጊት?'
ባርች
ቀልዱ ቢቀርብህስ?
ጃምቦ
ቢያንስ ቁምነገር አለው?. . . የኸውልህ ከሷ ጋር ጎጆ መስርታቹ ልጆች ወልዳቹ ምናምን አስበኸው ሊሆን ይችላል? ጨለምተኛ አትበለኝና? ጎጆ እንደወጣና ልጅ እንደወለደ ሰው ልምከርህ?
ባርች
ደስተኛ ነህ በህይወትህ? ሳትዋሽ ተናገር?
ጃምቦ
እግዜብሄር ይመስገን በጣም ደስተኛ ነኝ!
(ባርች በአባባሉ ይስቃል)
ምን እያልኩህ ነበር? ቦቼ? አው ፣ እኔም እንደዛ ሳስብ ደስተኛ ነበርኩ ? አሁን ግን ብትጠይቀኝ ደስተኛ ነህ ወይ ብትለኝ? አደለሁም ነው ምልህ
(ባርች ሳያስበው አሁንም ይስቃል)
በገባሁ በወጣሁ ቁጥር ይሄ የለም ይሄን አምጣ ነው? በትንሽ በትልቁ መጨቃጨቅ ነው? ገንዘብ! ገንዘብ! ገንዘብ!
ጃምቦ በጁ አስተናጋጁን ይጠራዋል ።
ስንታየው
ምን ልታረግ ነው?
ጃምቦ
ልጠጣ ?!
ስንታየው
ጥ! ተው ባክህ?
ጃምቦ
አንድ ብቻ ነው !
ሃና(V.O.)
በተሰያሚውና በስሙ መካከል ምንም አየነት ተፈጥሯዊ ግንኙነት የለም ትል ነበር አይን አለም የምትባል መነጽር ምታረግ የአማርኛ መምህራችን ። የመንደራችን ሰው ግን ለአባቴ ጃምቦ የሚለውን ስም ሲያወጡ መጠጥ በቀመሰ ቁጥር ራሱን የሚዘነጋ እንደዛም ሆኖ መጠጥን የሚናፍቅ ተፈጥሮውን አስበው ነው 'ጃምቦ!' እያሉ የሚጠሩት . . .እውነት ከሆነ ስድብ አደለም መሰለኝ።
ባርች
አንድ ወር አለፈህ አደል ከጠጣህ? ቻል አድርገው ፣ ታገሰው እ?
ስንታየው
ያልኳቹ ነገር ሲጀመር የገባቹ አልመሰለኝም? ትናንትና ስል ትናንትና ማለቴ ነው። ትናንትና? ትናንትና። ትናትና አገባሃለው ስትለኝ የነበረችው ለስንት ዓመት አብራኝ የቆየችው ልጅ ጥላኝ ሄደች እኮ ነው የምላቹ ?!!
ይህን እንዳለ ቅድም በአትኩሮት ሲያያቸው የነበሩት ሰዎች ከት ብለው ይስቃሉ ፣ በተናገረው ነገር ይመስል ። ሶስቱም ዞረው ይመለከቷቸዋል ። ሰዎቹ ወደነሱ እያዩ ነበር ።
ስንታየው
ምንድን ነው ችግራቸው? ከቅድም ጀምሮ ሲያፈጡ ነበር?
አስተናጋጁ ሲመጣ ጎንበስ ሲል 3ቱም አይናቸውን ወደ አስትናጋጁ ይመልሳሉ ።
ጃምቦ
የተለመደውን
ስንታየው
እንዳታመጣ ፣ እንዲሁም ሚስትህ አይኔን ማየት አትፈልግም እንኳን-እንኳን ምክንያት ሰጥተሃት
ጃምቦ
አንድ ብቻ ነው . . . አንድ ይዘህ ና?
አስተናጋጁ የሚጠብቀው ነገር ያለ ይመስል ትንሽ ቆሞ ካያቸው በኋላ ወደኋላ አፈገፈገ ።
ጃምቦ
ኬት ነው ያመጡት?!
ጃምቦና ስንታየው አፍ ለአፍ ገጥመው መነጋገር ሲጀምሩ ባርች በአይኑ አስትናጋጁን ሸኝቶ ከባልኮኒው የነበረችው በ40ዎቹ ውስጥ ያለች የልጅነት መልኳ ያልተለያት ጠይም እመቤት ወደሱ እያየች ይይዛታል። ፈገግታ ካሳያት በኋላ ስትሽኮረመምና ስትደሰት እያያት ቢራውን ይጎነጫል ። በመሃል አስተናጋጁ ጀርባውን ለኛ ሰጥቶን ወደነስንታየው ሲያመራ እይታችን ይገታል። በትሪ አድርጎ የያዘውን ቀዝቀዝ ያለ መጠጥ ፣ አረፋው ኩልል ብሎ ከላይ ተንሳፎ ጥቃቅን አረፋዎች ከጠርሙሱ ስር ወደላይ እየተንደቀደቁ ሲወጡ በ'CLOSE UP' እንከተላለን ። ከጃምቦ ጠረጴዛ ፊት ለፊት እንቀመጣለን ፣ ሽቅብ እየተመለከትነው ፣ ከረጅም አፍንጫው ስር ያሉትን ሁለት ዋሻዎች ፣ ቁልቁል የሚያዩትን አይኖች እያየን ፣ የሰዎቹ ጭብጨባና ወሬ ትርጉም በማይሰጥ መልኩ ወደጆሯችን እየገባ ። ጃምቦ በ'SLOW MOTION' ዋንጫውን አንስቶ ወደአፉ አስጠግቶ አስጠግቶ አስጠግቶ ሲያንቆረቁረው ከጉሮሮው ሲወርድ ፣ ዋንጫው ሲጎድል ሲጎድል ሲጎድል ባዶ ሆኖ ወደ ጠረጴዛው ሲመለስ።
EXT. የሰፈራቸው መንገድ - ማታ የቀጠለ
ጨለማ በነገሰበት መንደራቸው ያሉት ያልተበላሹ አንዳንድ የመንገድ መብራቶች ተደጋግፈው እንደቆሙት ቤቶች ተደጋግፈው የሚሄዱትን እነ ጃምቦን ያሳየናል ። ጃምቦ እንዳለው 1 ብቻ እንዳልጠጣ መገመታችን አይቀርም ። ጠባብ በሆነው ዳርና ዳሩን የሚሰፍጥ ግማት ያለው ቱቦ እንደገደል ከሚያዋስነው መንገድ ላይ ራሱን ጠብቆ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ባርችና ስንታየው ዳርና ዳር ቆመው አንዴ ወዲህ አንዴ ወዲያ እየገፉ ከገደሉ ይጠብቁታል ። በስንታየው በኩል ብዙውን ጊዜ ስለማይገፋ ባርች የመግፋቱንም የመጎተቱንም ስራ ደርቦ እየሰራ ነው ።
ባርች
ደግፈው እንጂ አንተ
ስንታየው አልሰማውም ፣ የጃምቦን እጅ አንገቱ ላይ ጠምጥሞ እንዳቀረቀረ እምባ ያቀረሩ አይኖቹን ከመሬቱ ተክሎ በራሱ ሃሳብ ይነጉዳል።
ስንታየው
ጥላኝ ሄደች ?!
ጃምቦ ግምባሩን የስንታየው ጉንጭ ላይ አስደግፎ
ጃምቦ
እኔ የስንዱ ልጅ አለሁልህ አደለም እንዴ?!
እንደ ጎራዴ በሚያርደው ድምጹ እየጮኸ ፣ ስንታየው አልሰማውም
ጃምቦ
እኔ አለሁልህ አደለም እንዴ?!
በግምባሩ እየገፋው
ስንታየው(ለራሱ)
ጥላኝ ሄደች
ጃምቦ
እና ለምንድን ነው ምታለቅሰው?!
አሁንም በግምባሩ እየገፋው
ጃምቦ
ለምንድን ነው ምታለቅሰው?!
ባርች ወንድም አደለም አደለም?!
ንገረኛ?!
ባርች ብቻውን እየታገለ
ባርች
አንተንም ተሸክሜ -(ያልጎመጉማል)- ደግፈው እንጂ?
በስንታየው ጥግ ሲንደረደሩ ስንታየው ከሃሳቡ እየነቃ ወደመሃል ይገፋዋል ።
ጃምቦ
መልስልኛ?!
ወደ ጨለማው ይጠልቃሉ ።
INT. የጃምቦ ቤት - የቀጠለ
ባርች ጃምቦን ደግፎ ይዞ ባረጀው የእንጨት በር በኩል ሲገባ በሩ እስከመጨረሻ በመበርገዱ ትልቅ ጩኸት አሰማ ። በሶፋው ላይ ተቀምጣ የነበረችው ባለቤቱ ቆመችና እጇን አጣምራ መመልከት ጀመረች ። አዋዜ የመሰለ ላይነን የሌሊት ልብሷ ከጉልበቱ ጋር ሲደርስ አልቆ የተቆላ ቡና የሚመስለው ቆዳዋ ከቀጭን እግሮቿ ላይ መታየት ይጀምራሉ ። አነስ ካለው ፊቷ ላይ ዙሪያውን ጥቁር መስመር ተለድፎ የሚታየው አይኗን ጃምቦዋ ላይ ሰክታ ቅንድቦቿን አኮሳትራ ያልራሱ ከንፈሮቿን እየመጠጠች የተመሳቀለውና በቋፍ ያለውን የድሃ ጎጇቸውን እንዳናስተውል ታደርገናለች ።
ጃምቦ
ጣይቱ ?! እቴግዬ ?! ተሸንፌ መጣሁ አደል ?! እናቴ? እማ?
ሃና ወደቆጡ ከሚወስደው ደረጃ ላይ ተደብቃ እየተመለከተች ነው ።
ሃና(V.O.)
እስከማስታውሰው ድረስ አባቴ ሰክሮ እናቴን መቷት አያውቅም። በተቃራኒው ሳይሰክር የማይናገራቸውን የፍቅር ቃላት እንደ ውሃ ያፈስላት ነበር ። ጣይቱ? እማ? እቴግዬ? ምናልባት ለምን ጠጣህ ብላ እንዳትናገረው ሊሆን ይችላል ነገር ግን 'ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል' አደል ሚባለው?
ባርች ስንታየውን ሶፋው ላይ አደላድሎ እንዳስቀመጠው ከጀርባው ቆማ የነበረችው 'ጣይቱ' ሻሿን በቀጭን ጣቷ ፋቅ ፋቅ አድርጋ መናገር ጀመረች ።
ጣይቱ
ወዴት ልሂድ አሁንስ?
ከጎኗ ከነበረው ሌላኛው ሶፋ ላይ ተቀምጣ ራሷን በሁለት እጆቿ ይዛ። እምባዋ እንደበጋ ዝናብ ዱብ ዱብ እያለ
ጣይቱ
ምን ልሁን ? የት ቤተክርስቲያን ሄጄ ልሳል?
ቶሎ ብሎ ሊወጣ የነበረው ባርች ንግግሯ እግሩን ያዘው ፣ ፊቷን ወደሷ አዙሮ በመቆም ወቀሳውን መስማቱን ተያያዘው
ጣይቱ
ምነው እግዜር ቢሰማኝ? ምናለ ብትተዉት ? ምናለ ሌላ ቦታ ብትገናኙ
ሃና(V.O.)
ለምንድን ነው ምታለቅሰው?
ህጻን ሃና አይኗን አጥባ ትጠይቃለች ።
ጣይቱ
ልጆቹን አርፎ እንዳያሳድግ . . .
EXT.ሰፈራቸው ውስጥ - የቀጠለ
ስንታየው መንገዱ ዳር ከነበረው ቱቦ ሽንቱን እያንዶቀዶቀው ያለቅሳል ። ያልጎመጉማል ። እንደቆሰለ ውሻ ። ጨረቃዋን ለማየት ቀና ብሎ ሲፈልግ የለችም ። ወደሁላው ሊመለከት ቢሞክር ሽንቱን ጫማው ላይ ያንጠባጥባል ። በሱ እየተበሳጨ ሸንቶ እንደጨረሰ ከአጠገቡ ከነበረ ስልክ እንጨት በሁለት አዝጋሚ እርምጃዎች ይሄድና ስልክ እንጨቱን ተደግፎ የተኛ ቆሻሻ የነበረበትን ማዳበሪያ ከመሬት ተነስቶ ሽንት ባረጠበው ጫማው እየደጋገመ ይወቃዋል ። እያለቃቃሰ እየጠለዘ ስልኩ ይጠራል። ራሱን ካረጋጋ በኋላ ስልኩን አይቶ የማያውቀው በመሆኑ ፊቱን እየቋጠረ አነሳውና ወደጆሮው ደገነው ።
ስንታየው
አቤት?
ሳሚ
እ ቦቼ? . . . ቦቼ?
ስንታየው
ማን ልበል
ሳሚ
ሳሚ ነኝ ደላላው ። ስራ ፈልግልኝ ብለኸኝ ነበር እ?
ስንታየው
ስልክ ቀይረህ ነው
ሳሚ
አዲስ ሆነብሻ
ስንታየው
እ?! . . . ከስንት ጊዜ በኋላ ነው የደወልክ ? ሁለት ወር አለፈህ?
ጫማውን ከማዳበሪያው እያከከ ።
ሳሚ
አንተ ሁለት ወር ትላለህ? ሰው እስኪሸብት ከወላጆቹ ጋር ተጣብቆ እየኖረ አደል እንዴ ?
(መልስ አልነበረም)
የድምበሯን ልጅ አወከው ?
ስንታየው ሲፈልጋት የነበረቸውን ጨረቃ እያየ እምባውን እየታገለ
ስንታየው
አ አው? ራሱን ያጠፋው?
ሳሚ
46 ዓመቱ ነበር ፣
ስንታየው
አው።
ሳሚ
ሰው አሁን እዳ ገብቶ ነው የሞተው ምናምን ይላል ። ድምበሯ እንደዛ ነው ያሉት . . . ደሞ አንቱ እላለው እንዴ ። የሰው ነገር እኮ አሁን እሳቸው እድሜያቸውን ጨርሰዋል . . .
ስንታየው ሁለት እጆቹን ሲጨብጥ ስልኩንም አብሮ ጨብጦ ድምጽ ሳያወጣ እየጮኸ ። ተኮራምቶ ይቀመጣል ። ከስልኩ የሚወጣውን ድምጽ ባይሰማውም ሳሚ ደላላው ማውራቱን አላቅቆመም
ሳሚ
በዛ እድሜያቸው አሁን እንደዚ ይደረጋል ። ተንኮለኛ አሮጊት! ነጠላ ለብሰው ሲሳለሙ እኮ ነው የሚገርመኝ እንደደና ሰው ? እንግዲህ እግዜር ያሳይህ ልጃቸው አብሯቸው ነው ያለው ስራ የለው ትዳር የለው ። ድምቡሎ እንደሌለው እያወቁ ምን ያረጋሉ? ቤቱንና ንብረታቸውን ለቤተክርስቲያን ውርስ ያስገባሉ 'ለነፍሴ' ብለው ። አሁን እሳቸው እውነት ለነፍሳቸው አስበው ?
እ?
ስንታየው ሲለው የነበረውን ነገር ከልቡ ባያደምጠውም ስልኩን ወደጆሮው በጥድፊያ እየላከ
ስንታየው
ይገርማል በጣም
ሳሚ
በዚ ምክንያት ነው ራሱን ያጠፋው ባይገርምህ? ራሱን እንዲጠላ አድርገውት?
ስንታየው
ይገርማል
(ዝምታ ነገሰ)
ስንታየው ቁጢጥ ካለበት እየተነሳ
ሳሚ
ለምን ነበር የደወልኩት ? . . . አው ስራውን አግኝቼልህ ነበር ?
ስንታየው
ጥ(እምባው እያነቀው) . . . ጥሩ ?
ሳሚ
ግን ውድድር አለው? እ? እንዳታስብ ግን ?
ስንታየው
እሺ
ሳሚ
ዛሬ ሃሙስ ነዋ ፣ ሁለት ቀን ቅዳሜ ነው መሰለኝ አው ቅዳሜ ነው ? እ? ፏ ፈሽ ብለሽ ትከሰችላቸዋለሽ። እ?
ስንታየው
እ (እየተናነቀው ) እሺ?
ሳሚ
በይ ደና ደሪ አባቴ እ?
ስናታየው
እሽ እሽ ደና ደር?
ስንኩን ወዲያው እየጠረቀመ ፣ አንጋጦ ወደ ጨረቃ እያየ እንደ ውሻ እንደ ጅብ ጮኽ ። ይኼኔ ባርች ወቀሳውን አዳምጦ እየተመለሰ ነበር ፣ ከጨለማው ወጥቶ የሚጮኸውን ስንታየውን አፉን ይይዘዋል ።
ባርች
ሽቤ አማረሽ እንዴ?
ዝም ካለ በኋላ አቅፎት ወደ ሌላኛው ጨለማ እየጠለቁ
ስንታየው(o.s)
ምን አለች?
ባርች(O.S)
አ . . . ምን ትላለች ?
ስንታየው(O.S)
ተናገረችህ አደል?
ድምጻቸውም ከጨላማው እንደገቡ እየደበዘዘ ይመጣል።
ባርች(O.S)
አረ ደስ ብሏት ነበር ። በርታ እያለችው ነበር ።
ስንታየው(O.S)
ቲስ ቀልድ ! እሷ እኔን ካልሰደበች አይሆንላትም
ሃና(V.O.)
እናቴ ስንታየውን አብዝታ ትጠላው ነበር ። አባቴ የሚጠጣው በሱ ምክንያት ነው ትል ነበር ለምን እንደሆነ ባላውቅም ።
INT. የጃምቦ ቤት - የቀጠለ
ሃና(V.O.)
ጠጥቶ በገባ ቁጥር ስንታየውን እየረገመች ታመሻለች ።
አባቷ ሶፋው ላይ ተንጋሎ በተኛበት ትልቋ(ጣይቱ ፣ እናቷ)ራሷን በጣቶቿ ደግፋ እያየችው ትበሳጫለች ፣ ትንቀዋለች ። ሶፋዎቹ ሳሎኑን አጣበውታል። ስንታየው ከተኛበት ሶፋ አጠገብ በጠርዞቹ ሁሉ ግድግዳዎቹን የሚዳስስ አልጋ ተቀምጧል ። እምባዋን እይጠረገችና አፍንጫዋን እያጸዳች ወደቆጡ ቀና ብላ ስትመለከት ሃና ደረጃው ላይ ተደብቃ እያየች አይናቸው ይጋጫል ።
ጣይቱ
ግቢና ተኚ! ሾካካ!
ሃና እየሮጠች ወደቆጡ ትወጣለች ። እንከተላለን ። ወለሉን በባዶ እግሯ በረገጠችው ቁጥር ወደውስጥ በጥቂቱ ትሰጥማለች ። ከጥጉ ከነበረው መደብ ላይ ገብታ በፍጥነት ብርድ ልብሷን ተጠቀለለችና አይኖቿን ጨፈነች ።
የእናቷን ንግግር ከታች እየሰማች
ጣይቱ(O.S.)
ህ! . . . የተረገመ!
በታፈነ መልኩ የጣይቱ ምሬት ይቀጥላል ትንሽ ቆይቶ ሳናስተውለው ይጠፋል። የሃናም ትረካ ይቀጥላል ።
ከመደቧ በላይ ከነበረው ፒንክ ወጣ ገባና ሳርና ጭቃ ከበዛበት ግድግዳ ላይ እይታችን ተተክሎ ይቆይና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የጥዋቷ ጸሃይ በገባ ወጣው ግድግዳ ላይ መንጠላጠል ስትጀምር ያኔ ከተኛችበት ጸጉሯ ተንጨባሮና ፊቷ አብጦ ትነሳለች ። ወደኛ ትመለከታለች ። ምላሷን እያጣጣመች ፊቷን ጸጉሯን አከክ አከክ ታደርግና ብርድልብሷን ወዲያ ብላ ትነሳለች ።
እናቷ ከታች ሁና ብርድልብሷን እያጠበች አልጋው ላይ ሁና አልጋዋን እያነጠፈች ሃና ዱብ ዱብ ብላ ከቆጡ ትወርዳለች ደረጃዎቹን እየደለቀች ። ድለቃው ግን ፊቱን ሸፍኖ የተኛውን ጃምቦን አልቀሰቀሰውም ።
ጣይቱ
እንቅልፎ? ነጋልሽ?
ሃና አሁን ደሞ ቀጭን ክንዷን በቀጭን ጣቷ አከክ አከክ እያደረገች ፈገግ አለች ።
ጣይቱ
ፊትሽን ታጠቢ? ልብስሽን ቀይሪ? - ጸጉርሽን ደሞ አበጥሪው ? - አትቁሚ ቶሎ በይ ?
የናቷን ጥያቄ ተቀብላ ወደ ደጅ ወጣች ። እናቷ ያጠፈቻቸውን ብርድ ልብሶች እንደያዘች ወደቆጡ ወጣች።
ext. በራቸው ላይ - የቀጠለ
ከቤታቸው በር ላይ የሰፈራቸው ገጽታ ከሞላ ጎደል ግልጽ ሆኖ ይታያል ። ምን ያለ እንደሆነ ደግመን ማስረዳት አይጠበቅብንም ። ተደጋግፈው ያሉና ያረጁ ቤቶች ስለሆኑ ። የነሱም ቤቱ እንዲሁ ከሁለት ሌሎች ግድግዳዎች ላይ የተደገፈ ነው ። በዚህች መንደራቸው ውስጥ በምትገኝ ትንሽ መንደር ውስጥ የነበሩት ቤቶች መሃላቸው ባለ ቀጭን መተላለፊያ ተወስነው ሁለት ወገን ይዘው ተፋጠዋል ። ይህን መተላለፊያ ይዘው ቀጥታ ቢሄዱ ፣ ከየበሩ ስር የነበሩ የሳፋ የወምበር ጎgማዎች ወ.ዘ.ተ ኮተቶችን አልፈው ወደጥጉ ሲደርሱ ወደጎን ሲታጠፉ በሩ የዛገና የወየበ ጠባብ የመንደራቸው ሽንት ቤት ነበር ።
ሃና ከሽንት ቤቱ ወጥታ ቆልፋው ከወ.ዘ.ተ ኮተቶች አልፋ በራቸው ላይ ከነበረው ኮተት ስትደርስ የያዘችውን የላርጎ እቃ አስቀምጣ እጇን ልትጣጠብ ጆጉን ስታፈላልግ ከፊቷ ከነበርው ቤት ውስጥ እኩያዋ ይወጣል ። እሱም እንደሷ ዱካኩ አለቀቀውም ። ጆጉን ከአንዱ ጥግ ስታገኘው ውሃ ሞላችና ከፊቷ ለነበረው ልጅ እያቀበለችው
ህጻን ሃና
ጨምርልኝ እስቲ?
ልጁ አሰብ ካደረገ በኋላ ተቀበላትና ሳሙና የያዘችባቸውን እጆቿን አረጠበላት ።
ህጻኑ
ቶሎ በይ
መተላለፊያውን እየቃኘ የሆነ ነገር በመጠባበቅ ላይ ነው ።
ህጻን ሃና
እሺ
እጇን ታጥባ ስትጨርስ ሳሙናውን ድጋሜ አንስታ እጆቿን ትቀባቸው ጀመር
ህጻኑ
በሁለት እጅሽ ነው እንዴ ፊትሽን ምትጣጠቢው?
ህጻን ሃና
አው
ሳሙናውን አስቀምጣ ፊቷን እየዳበሰች ። ከአንዱ ቤት ገዘፍ ያለ ሰው ወጥቶ ኮተቱን በአይኑ መመልከት ጀመረ የሆነ ነገር እንደሚያስስ ሁሉ።
ህጻኑ
ቶሎ በይ?! ቶሎ በይ?!
ወደ ሰውየው እያየ ። ሰውየው ጎምበስ ብሎ ከኮተቶቹ መሃል የላርጎ እቃ አንስቶ በውሃ መሙላት ጀመረ ።
ህጻኑ
ቶሎ በይ ?! እንኪ ይዢው ራስሽ ቅጂ!
ሰውየው ቲሸርትና ቁምጣውን እያውለበለበ ወድ ጥጉ መራመድ ይጀምራል
ህጻን ሃና
ዝምብለህ ጨምር ልጨርስ ነው
ህጻኑ ወደሰውየው እያየ እግሩን ከፍ ዝቅ እያረገ ይቀዳላትና . . . ጆጉን መሬቱ ላይ ትቶላት ሽው ብሎ ይሮጣል ሰውየው መታጠፉን ሲያይ ። መንገድ ላይ የነበረው ኮተት ታዲያ ጠልፎ ይጥለዋል ። አንዳንድ ነዋሪዋች ይወጡና በሩ ላይ ሆነው ይመለከታሉ ። የሃናም እናት ልብሷን ቀይራ ጸጉሯን እያስተካከለች ብቅ ትልና ።
ጣይቱ
ምንድን ነው ?
ሃና ሳሙና በሌለው አይኗ በኩል አጮልቃ እያየች ሳትመልስላት ቀረች ።
የኮተቱ ባለቤት ከቤታቸው ብቅ አሉና
ሴትየዋ
አንተ?! በል ልቅም አርጋት እንደነበረች ? ገና በጥዋቱ?
ህጻን ሃና
አቢቲ ወድቆ ነው ።
ፊቷን መልሳ እያጠበች አቢቲ የወደቀውን አፍሶ ሲጨርስ ወደ ሃና መጥቶ
አቢቲ(ህጻኑ)
አየሻ አስመለጥሺኝ - አሁን ከገባ አይወጣም
ጣይቱ
አንተ?!
ከጀርባ እንደነበረች ስላላየ ያፍራል
ህጻን ሃና
አይ አቢቲ ፈረጥሻ? ፖፖ ላይ ተቀመጥ
ጣይቱ
አንቺ?! በይ ግቢ! ቶሎ በይ ልብስሽን ቀይሪ!ከመቼው ነው እንዲ ያደጋጁት?
ሃና ወደውስጥ ትገባለች
ጣይቱ
ቆይ ለእማሹ ካልተናገርኩልህ!(ወደ አቢቲ እያየች)
int.የነጃሞ ቤት - የቀጠለ
ሃናና እናቷ ቁጭ ብለው ቁርሳቸውን በአንድ ሰሃን ይቋደሳሉ ። ሃና ዩኒፎርሟን አድርጋ ጸጉሯችንም ወደኋላ አስይዛዋለች ። አይናቸው የሚያርፍበት ነገር በማጥትቸው ፣ ቴሌቭዥንም ሆነ ራድዮ ባለመኖሩ ፣ በጎረሱ ቁጥር ወደምንም እያዩ ያስባሉ ። ሃና ወደ ውጭ እያየች ስታስብ ምግቡን ረስታዋለች።
ጣይቱ
ለምንድን ነው ማትበይው
ህጻን ሃና
እየበላሁ ነው
ጣይቱ
በደምብ ብይ
በጀርባው ለጥ ያለው ጃምቦ ንግግራቸው የሚቀሰቅሰው አይመስልም ።
ጣይቱ
እሱን ሳትጨርሽ እንዳትነሽ
እናቷ ወደ ደጅ ትወጣለች ። ሃና ይህን ስታይ ከተቀመጥችበት ተነስታ የተንጋለለውን አባቷን በጣቷ ትወጋዋለች ። ስትወጋው ስትወጋው አይኑን በሰመመን በትንሹ ይገልጣል ።
እናቷ እንደገባች ልጅቱ ምታረገውን ነገር በማየቷ በሩ ጋር እንደቆመች
ጣይቱ
እንዲነሳ ብለሽ ነው?እሱ ምን አለበት እቴ ለጥ ይበል እንጂ - የዛሬ ዓመትም በተነሳልሽ? ያ ከይሲ እያለ እምህ!
(የምታነሳውን እያነሳች - የምታስቀምጠውን እያስቀመጠች)
ዝም ብለሽ ምግብሽን ብይ !
ሃና(V.O.)
ምንም እንኳን እናቴ ስንታየውን አብዝታ ብትጠላውም የአባቴ የስንታየውና የባርች ወዳጅነት ዘመን ያስቆጠረና በቀላሉ ሊቋረጥ የማይችል ነው ።
እናቷ ወዲህ ወዲያ ስትል ካሜራውን ትሸፍነውና ሲገለጥ
EXT. የሰፍራቸው መንገድ - የቀጠለ
የሰፈሩ ህጻናት 3 - 4 እየሆኑ ተከታትለው ይሄዳሉ ። ሃናና አቢቲ እንዲሁም ሁለት ተጨማሪ የሰፈራቸው ልጆች ከነዛ ልጆች መሃከል ነበር ። ከነሱ ፊት 3 ወንዶች ተቃቅፈው ይሄዳሉ እንደነሱ ያለ የመንግስት ት/ቤት ዩኒፎርም ያረጉ ። ሃና የጓደኞቿ ጨዋታ ብዙም ትኩረቷን አልሳበውም ። ከፊት የሚሆዱትን 3 ልጆች እያየች
ሃና(V.O.)
ከልጅነት አብረው የመጡ ፣ ሊነጣጠሉ የማይወዱ ነፍሳት ነበሩ ። ከአንድ መንደር አድገው ከአንድ ትምህርት ቤት የተማሩ አብሮ አደጎች ። ለዛ እናቴ አብዝታ ጓደኝነታቸውን እንዲያቆም አባቴን ብትወተውተውም የሚሆን ነገር አልነበረም ።
int. ት/ቤታቸው - ቀን
ሃናና ቢጤዎቿ እየተጫወቱ ተማሪው እየተተራመሰ ደረጃውን ወጥተን ወደ አንዱ ክፍል ስንገባ ጎረምሶቹ ተማሪዎች ሌላ እኩያቸው የሆነ ተማሪ እያስቸገሩት ቢሆንም በክፍሉ ውስጥ የነበሩት ሌሎች ተማሪዎች በራሳቸው ስራ ተጠምደው ነበር ።
ሃና(V.O.)
አባቴ እንደነገረኝ ከሆነ ስንታየውን የሚያስቸግሩት ተማሪዎች አይጠፉም ነበር ግማሾቹ ጎበዝ ተማሪ በመሆኑ ሌሎቹ ደሞ ያለምክንያት ያስቸግሩት ነበር ። ያ በሚሆን ጊዜ ባርችና አባቴ ፈጥኖ የማዳን ስራቸውን ከመስራት ተቆጥበው አያውቁም ነበር ።
ሲያስቸግሩት ከነበሩት ተማሪዎች ጀርባ ሁለት ሌሎች ጎረምሶች ተንደርድረው ይመጡና በረጅም ቡጢና የጫማ ጥፊ ተማሪዎቹን(ጉልቤዎቹን) ይጠልዟቸዋል ። ይሄኔ የልጁ መጎሳቆል ጉዳያቸው ያልነበር ተማሪዎች ክፍሉን በጩኸት ማናጋት ይጀምራሉ ። ሁለቱ ልጆች ከሌሎቹ ተማሪዎች ጋር ግብ ግብ ይገባሉ ፣ ተማሪው በዙሪያቸው ቆሞ
ተማሪዎቹ(በዜማ)
በለው በለው በለው . . . በለው በለው በለው
ትርምስ ።
ሃና(V.O.)
በልጅነት አእምሮዬ ምናልባት እናቴ ስንታየውን የምትጠላው አንድ ትምህርት ቤት ይማሩ ስለነበርና ባርችና አባቴ በሱ ምክንያት ፊታቸው ሲደማና ሲያብጥ ማስተዋል ስለነበረባት ይሆናል እል ነበር? ነገር ግን ጓደኛ ለመች ነው?
ከሴቶቹ መሃል አንዷ በንዴት ስታያቸው የተጣሉት ልጆች ደምተውና አብጠው ከጓደኛቸው ጋር ከክፍሉ ፈገግ እያሉ ሲውጡ ተከትለን ወደነሃና ክፍል እንጠልቃለን ።
ሃና በመስኮቱ ወደውጭ ትክ ብላ እያየች ፣ መምህሩ የሚለውን ነገር ስትሰማ ፊቷን ወደክፍሉ ትመልሳለች ። ክፍሉ ውስጥ የነበሩት አንዳንድ ህጻናት መምህሩ እንዲመርጣቸው ያወጡትን እጃቸውን እያውለበለቡ ።
ሃና(V.O.)
ስንታየው የሰፈራችን 'ቅጣው እጅጉ' ማለት ነበር ። በትምህርት ቤታቸው ከነበረ ሌላ ስንታየው ሲለዩ አንዳንዶች ስንታየው 'ቀለሜው' ይሉት ነበር ቦቸራ ብለው ካልጠሩት ። ባርችና አባቴ ከጉልበተኞች ሲያስጥሉት እሱ ደግሞ ከከባድ ፈተና 'እያስኮረጀ' ያወጣቸው ነበር ።
በገባንበት መስኮት ወጥተን ወደሌላኛው ክፍል ስንሄድ መምህሩ ወዲህና ወዲያ እየተንጎራደደ ተማሪው አንገቱን ቀብሮ ወረቀቱ ላይ እያፈጠጠ ሁለት(ሌሎች ተማሪዎች) እዛና እዚ ተቀምጠው ከመሃል ከነበረው መደዳ አንድ ልጅ ፈተናውን ጨርሶ መምህሩን ቀና እይለ እያየ ትንሽ ወረቀት ይቀዳል ፣ ሲጨርስ ከራሱ መልስ እያየ 'a b c d . . . true false ' እያለ ይገልብጣል ። ያንንም ሲጨርስ መምህሩን ቀና ብሎ ለ1ሺኛ ጊዜ አየና ጀርባውን እንደሰጠው ሲመለከት ከአንደኛው ጥግ ወደነበረው ተማሪ ይወረውረዋል። ተማሪው ከወረቀቷ ጋር አይናቸው ይወረወራል ። አልደረሰችም መሬት ላይ ነበር ያረፈችው ፣ እንዳያነሳው ደግሞ መምህሩ ፊቱን አዙሮ እየተመለሰ ነው ። መምህሩ እስኪያልፍ ይጠባበቃል ፣ መምህሩ እንደዞረ በዛኛው ጥግ የነበረው ተማሪ እጁን ያወጣና ወደሱ እንዲመጣ ያረገዋል በመንገዱ ላይ የነበረችውን ወረቀት ረግጧት ያልፋል ። እንዳለፈ ይህኛው ተማሪ እጁን ሰዶ ያነሳታል ተማሪውም በአይኑ ያግዘዋል ። መምህሩ እየተጓዘ ፊቱን መለስ ቢያረግበትም ረፍዶ ነበር ፣ ወደ ጠራው ተማሪ ዝቅ ብሎ ማውራት ሲጀምር ወረቀቱን የወረወረውና የተቀበለው ይተያዩና ምልክት ይሰጣጣሉ ። ይሄኔ አስኮራጁ ከተቀመጠበት ይነሳና ወረቀቱን ከሚቀመጥበት አድርጎ ይወጣል መምህሩ ይሄኔ ወረቀቱን የያዘው ልጅ መልሱን መገልበጥ ይጀምራል ። አስኮራጁ ይወጣል . . . ወደነ ሃና ክፍል ስንመለስ ሃና እንደለመደችው በመስኮት በኩል እያየች ነበር ፣ አስኮራጁ ያልፋል ።
ሃና(V.O.)
አንዳንዴ ላለመድፈን ብለው አንዳንድ መልስ አውቀው ይሳሳቱ ነበር ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ሶስቱም እኩል ያመጡ ነበር ። የክፍሉ ተማሪ መቅናቱ አልቀረም ።
ወረቀቱን ያነሳው ልጅ ፈገግ ብሎ ደረቱን ነፍቶ በመስኮቱ ያልፋል ።
ሃና(V.O.)
ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል ስለሚባል እነሱም ለአንድ ሁለት ሰው መልሱን ማካፈል ነበረባቸው ።
ወደዛኛው ክፍል ስንመለስ
መምህሩን የጠራው ተማሪ ከወረቀቱ መልሱን ከገለበጠ ወዲያ አንዳንድ መልሶችን ከወረቀቱ ላይ ሰርዞ ወረቆቱን እጁ ወዳመራው ሲወርውር ትልቅ እቃ የወደቀ ይመስል ተማሪዎቹ ወደመሬቱ አፈጠጡ ።
ሃና በመስኮቱ በኩል በኩራት ፈገግ ብሎ የሚያልፈውን ሶስተኛውን ልጅ ትመለከተዋለች።
ሃና(V.O.)
እንዲህ ባለ ሁኔታ እስከ 10 ዘለቁ
INT.የነሃና ቤት - ቀን የቀጠለ
ከተኛበት በሰመመን ሲነቃ ፊቱ ተጨማዶና አይኑ ቀልቶ ነበር ። አይኑን ብቻ ገልጦ ቤቱን ከቃኘ በኋላ ብቻውን መሆኑን ሲያውቅ ራሱን ከሶፋው ላይ ደጋግፎ በማንሳት በረጅም እየተነፈሰ ይቀመጣል ። የደረቱን መሃል አከክ አከክ ባረገ ቁጥር ፊቱንም አብሮ ያጨማድድ ነበር ። ራሱን ደጋግሞ ካበሰ ወዲያ ፊቱንም በእጆቹ እየለጠጠ ከመለሳቸው በኋላ ፣ የቀሉት አይኖቹ እምባ አቀረሩ ፣ ደም ስሩ ተገታተረና ፊቱ በወዝ ተጠመቀ ። ዙሪያ ገባውን ከፈለገ በኋላ ከጠባቧ ሳሎን ወለል ላይ ወደአንድ ጥግ የተቀመጠ አነስ ያል ሃይላንድ አገኘ ፣ ይዟት ከቤቱ ወጣ ።
ሃና(V.O.)
ሁሌ ፋሲካ የለም እንዲሉ 10 ከደረሱ ወዲያ ትልቅ ችግር ገጠማቸው ። ፈተናውን የሚፈተኑበት ክላስ ምድቡ በአልፋቤት በመሆኑ ስማቸው ትልቅ እንቅፋት ሆነባቸው ።
ባልቀየመውም አባቴን በሙሉ ስሙ ስጠራው ፍቅሬ እለዋለው ። ባርችን ደሞ ዮሴፍ ። ስንታየው ደሞ ስንታየው . . . በዛ ምክንያት ጎን ለጎን መቀመጥ ቀርቶ አንድ ክፍል እንኳን የመሆን እድሉ አልነበራቸውም ።
EXT.ሰፈራቸው - የቀጠለ
ሃይላንዱን ይዞ በሰፈራቸው መንገድ በጠራራ ጸሃይ ይራመዳል ፣ ሰፈሩ ዳርና ዳር ያሉት ማታ እንደገደል የሚፈራቸውን ትቦዎች ያልፋል ፣ ቀስ እያለ እያዘገመ ተጉዞ ወደ መጠጥ ቤቱ ይደርሳል።
INT.መጠጥ ቤቱ - የቀጠለ
ወደ ውስጥ ገብቶ እንደምሽቱ ያልደመቀውን ቀዝቀዝ ያለ ሙዚቃ የሚዋልልበትን መጠጥ ቤት በአይኑ እዛና እዚ ገርመም እያረገ ከገባ በኋላ ከባልኮኒው ሄዴ ሰው እስኪመጣ ትንሽ ጠበቀና የምናውቃት እመቤት ከወደኋላው መጥታ በርጋታ ታስተናግደዋለች ። ቀለም የሌለው መጠጥ ወደሃይላንዱ ታፈስለታለች ።
ሃና(V.O.)
ስንታየው በሰፈራችን ምናልባትም በት/ቤታችን ተሰምቶ የማይታወቅ ውጤት በማምጣት አለፈ ። ባርችም ከፊቱ የነበረችውን ልጅ ፈተና በደምብ በማጥናቱ ተንጠልጥሎ አለፈ ። ምስኪኑ አባቴ ግን ሳያልፍ ቀረ ።
የቀዳውን ሃይላንድ ጠርቆሞ እየዘጋ ከመጠጥ ቤቱ ይወጣል ።
EXT.ከተ/ቤቱ ውጭ - የቀጠለ
ተማሪዎች እየተንጋጉ ይወጣሉ ፣ መኪናዎች ቆመው ተማሪዎቹን ሲያሻግሯቸው እንመለከታለን ። ከሚሻገሩትም መካከል ሃናና ጥዋት አብረዋት የነበሩት እነ አቢት እንደለመዱት አብረው እየሄዱ ነበር ። ከተሻገሩ በኋላ ተማሪው ሁሉ በየፊናው ተበትኖ ስለሚጓዝ መንገድ ላይ ዩኒፎርም ለብሶ የሚታየው ጥቂት ነበር ።
አቢቲ
እረ አይቻልም! አሮፕላን ታክሲ መሰለህ እንዴ?
ህጻን 2
ይቻላል ፣ እኔ ስላየሁ ነው
አቢቲ
(ወደ ሃና ይዞርና)
አንቺ አሮፕላን ውስጥ መስኮት መክፈት ይቻላል ?
ህጻን ሃና
አው
ህጻን 2
ይቻላል?
ህጻን ሃና
አላውቅም . . . ንፋስ ከፈለጉስ
ይህን እያሉ በአንድ አነስ ያለች ቆርቆሮ ቤት በኩል ያልፋሉ እኛ ግን እዛው እንቀራለን ። ከቤቷ ፊት ለፊት ብዙ ማዳበሪያዎች እህል የጫነ ተሳቢ ይመጣና ይቆማል ። ሽፌሩ እንደወረደ ከውስጥ አንድ ጎረምሳ ወጣት ሊሆን ያለ ይወጣል ።
ሃና(V.O.)
ለዛ አረብ አገር ያለችው አክስቴ በላከችለት ገንዘብ ጎረምሳው አባቴ አነስ ያለ የንግድ ስራ ጀመረ ።
ጎረምሳው
ባሪያው ?!
ጎረምሳው መንገዱ ላይ ቆሞ ወደነሃና በኩል እያየ ከተጣራ በኋላ ከመንገዱ ዳር ከነበረ ሻይ-ቡና ቤት ውስጥ እጅጉን የጠቆረና ፈርጠም ያለ ሰው ይወጣል
ባርያው
(በጎጃም አማርኛ)
እ!!!
ጎረምሳው
የት ሂደህ ነው?
ባርያው
15 ብር በማዳበሪያ ?!
ጎረምሳው የሚለውን እንዳልሰማ ሁሉ ወደሹፌሩ ሄዶ ሰላምታ ይለዋወጣሉ ፣ ሹፌሩ ቁልቁል እያየው ጎረምሳው ከኪሱ አውቶ መቁጠር ይጀምራል። 'ባሪያው' ወደ ተሳቢው ሄዶ እያወረደ
ባሪያው
ሰምተሃል?
ጎረምሳው ቆጥሮ ከሰጠው በኋላ ሹፌሩ መቁጠር ሲጀምር ተሳቢው ላይ ወጥቶ ማዳበሪያውን ለማውረድ የተቸገረውን ባሪያውን ያግዘዋል ። ጀርባው ላይ ከጫነለት ወዲያ ባሪያው ተሸክሞ ወደ ትንሿ ቆርቆሮ ቤት ይገባል። እንከተለዋለን ።
INT. ቆርቆሮ ቤቱ ውስጥ - የቀጠለ
ውስጥ የውጭዋ ጸሃይ ቤቱን ከጨለማው ልትገፍ ትታገላለች ፣ ባትችልም ። ዙሪያውን ሙሉ ቆርቆሮ የሆነው ቤት በየጥጋ ጥጉ የገለባ ተራራ የማዳበሪያ ክምር ይታይበታል ። ቆርቆሮ ሲሸከክ እንሰማለን ፣ ሽክክ! ሽክክ! ሴቶችም ጮክ ባለ ዶርዜኛ ሲነጋገሩ እናደምጣለን።እሳት ሲነድ ።
እንደገባ ደፍ ደፍ እያለ ማዳበሪያውን ከአንዱ የክፍሉ ጥግ ዘፍ አደረገጎ ተመልሶ ይወጣል።
ሴቶቹ ይስቃሉ ። ከወጣበት በድያሜ ማዳበሪያ ተሸክሞ ያስገባል ፣ አሁን ግን ቅድም ካስቀመጠበት ቦታ ሳይሆን ከጀርባ ከነበረ ሌላ ክፍል ለማስቀመጥ ይገባል ። እንደገባ በዚህኛው በኩልም ሌላ በር እንዳለና ከውስጥ አንዲት ቀጭን ንቅሳት ያለባት ሴት ሴት በወስፊት ቆሎውን እያበጠረች ሽው ሽው እያረገች እንመለከታለን ። ከበሩ ፊት ለፊት ከነበረው ሌላ ቆርቆሮ ደሞ በዶርዝኛ ምታወራዋን አንዲቷ ቆሎውን እየቆላች ሸከክ ሸከክ እያረገች እንመለካታለ ።
ባሪያው
መንገድ ! መንገድ!
ሴትየዋ
(በጎንደር ቅላጼ)
ወዲህ ለምን መጣህ ?
ማዳበሪያዋን ዘፍ ያረገዋል
ባርያው
ታዲያ የት ላርግልሽ ሴትዮ! . . . ዎኦ?!
ከቁብም ሳይቆጥራት ተመልሶ ይወጣል።
ፊቷ በላብ ርሶ ቆሎውን ምትቆላው ሴት ፣
ቆዪዋ
(በደቡብ ቅላጼ)
ባራያው! . . . አንተ ?!
ሴትየዋ
ይመለሳል!
ሸክክ ሸክክ . . . ሽው ሽው . . . እሳቱ ይነዳል . . . ዶርዝኛው ይቀጥላል . . . ባርያው ተመልሶ ሸክሙን ይዞ ይገባል
ቆዪዋ
ባርያው?! . . . እንጨት አልቋል በለው ? በዛው ስትወጣ?
ዘፍ አድርጎ እየወጣ
ባርያው(O.S.)
እንጨት የለም ትላለች ?! . . .አንድ! ሁለት! . . . በርታ!
ተሸክሞ ድጋሜ ዘፍ ። አንፋሿ ቆሎውን ወደላይ ወርውራ ቆሎው ሲመለስ ከረጅም ትሩ ላይ ሆኖ እየተለቀመ ነበር ።
ext. በአንፋሿና በቆዪዋ መሃከል የነበረው መንገድ - የቀጠለ
መንገዱ ላይ ሁነው ሁካታውን እና ጩኸቱን እየሰሙ ብዙ ሴቶች ክብ ሰርተው ተቀምጠው የሚለቅሙት ይለቅማል ፣ ቆሎውን በዘይት የሚያሹት ደሞ በዘይት ያሹታል ፣ ለውዝና ዱቤ ይጨምሩበታል ፣ የሚያሽጉት ያሽጉታል ያሸጉትን ከማዳበሪያ ይጨምሩታል ።
EXT. መንገዱ ዳር - የቀጠለ
የመጨረሻውን ማዳበሪያ ካሸከመው በኋላ ጎረምሳው ከመኪናው ይወርዳል ። ሽፌሩ ውስጥ ገብቶ መኪናውን እያሞቀ በመቆየቱ ጎረምሳው እንደወረደ ቦታውን ይለቃል ። ጎረምሳውም እጁን ያውለበልባል ። እዛው ቆሞ እንዳለ ባሪያው ይወጣል ።
ባሪያው
5 ማዳበሪያ 15 ብር ስንት ይመጣል?
ጎረምሳው 50 ብር አውቶ ይሰጠዋል
ባሪያው
ቆይ 50 ብር አይደለም . . . ስ - ሰባ አምስት ነው ሚሆነው
ጎረምሳው
50 ብር ይበቃሃል !
ባሪያው
ቀልድ አደልም እኮ የያዝኩት እንጀራ አደል እንዴ
ጎረምሳው
አወቀም ሃገሩ ገብቷላ ቆሎውን የሚያሽ የለም ከነገ ጀምሮ ታሸዋለህ በቃ
ባሪያው
አህ?!አይመለሰም እንዴ?!
ጎረምሳው
የለም - አይመጣም - አንተ ብቻነህ የቀረኸው! እ?!
እንዲ እያሉ ሌላ መኪና ከፊታቸው ይቆማል ።
ጎረምሳው
ይኽው ትጭናለህ አሁን?!
ወርዶ ወደሚመጣው ሹፌው እየተራመደ ።
ባሪያው
15 ይኸው ተናግሪያለው
ባሪያው ወደቆርቆሮው እየተመለሰ ፣ ጎረምሳው ከሹፌሩ ጋር ሲጨባበጥና መነጋገር ሲጀምር ጥለውን የሄዱትን እነሃናን ተከትለን እንደርስባቸዋለን ። ወንዶቹ መሬት ላይ የነበር ኮዳ እየልጉ ነበር እሷ ደም እየያቻቸው እየተራመደች
ሃና(V.O.)
ስራው ከሰፈራችን ባያወጣውም ፣ ትልቅ ቤት ባያሰራውም በቂ ነበር ።
INT. የነጃምቦ ቤት - የቀጠለ
ሃና እንደገባች አባቷ ሶፋው ላይ ተዘርሮ ባዶው ሃይላንድ ከሶፋው ላይ ከተንጠለጠልው እጁ ስር ከነበረው ወለል ላይ እየተንከባለለ አቧቷን ታገኘዋለች። ብዙም ሳትደናገጥ ወደ ቆጡ ትወጣለች። ልብሷን 'በቅጽበት' ቀይራ ተመልሳ በደረጃው ትወርዳለች ። ትወጣለች ። 'በቅጽበት' መሽቶ እናቷ ትመጣለች። በሩ ላይ ሆና የተኛውን ባሏን ስታይ እሷም ምንም ሳትል ወደውስጥ ትዘልቃለች ። እሷም ልብሷን ቀይራ ወደስራዋ ትገባለች ፣ ሽንኩር ትከትፋለች ፣ የተዘረረውን ባሏን አየት እያረገች ።
ካሜራችን ጃምቦን ቁልቁል እሱን ብቻ እየቀረጸ ይቆያል ፣ ሲገለበጥ ፣ እጁን ከፍ ዝቅ ሲያረግ እናያለን ጥላዎች ወዲህና ወዲያ ሲሊ ፣ ጸሃይ ጠልዋ ስትወጣ ፣ ደረጃው ሲጮኽ ጊዜው እንደሄደ ይገባና ። ከዛ ተንከባሎ ሊወድቅ ሲልና ሲነሳ ።
ሃና(V.O.)
ለሁለት ቀን ሙሉ ከተኛ በኋላ አባቴ በመጨረሻም ሲነቃ ሁልጊዜም እንደሚሆነው የጥፋተኝነት ስሜት እረፍት ነሳው።
ሰዓትን ያያል ረፋድ ላይ ነበር ። በቤቱ ውስጥ ሰው አልነበረም ። ፊቱን በሁለት እጅቹ ሸፍኖ በረጅሙ ይተነፍሳል ።
INT.የስንታየው ቤት - የቀጠለ
ሃና(V.O.)
ልክ እንደአባቴ ሁሉ ስንታየው በሩት ሃሳብ ሰክሮ ለሁለት ቀን ከቤት አልወጣም ነበር ።
ቁልቁል ሶፋው ላይ የተኛውን ስንታየውን ወደኛ እያየ እንመለከተዋልን ፣ ሲገላበጥ ሲቀመጥ መልሶ ሲተኛ ። እንዲህ ባለ ሁኔታ እያለ ስልኩ ይጠራል ። ቁጥሩን ያያውና ፊቱን ይቋጥራል ። ፊቱን እንደቋጠረ ወደጆሮው ያስጠጋዋል። አንስቶ ።
ሳሚ ደላላው
ሄሎ . . . ?
ሃና(V.O.)
ስለ ስራው እስኪረሳ ድረስ በሷ ሃሳብ ተወስዶ ነበር
ስንታየው ድምጹን ሲሰማ ከተኛበት ስሱን በርድልብስ ገፎ ተስፈንጥሮ ይነሳል። ሱሪውን በችኮላ ሊለብስ ሲል ይወድቃል ።
int. መስራቤቱ - የቀጠለ
ሃና(V.O.)
እንደ 'እድል' ሆኖ ፈተናው ከመጀመሩ በፊት ደረሰ ።
ከተባለው መስራቤት ብዙ ወጣቶች ወንዶችና ሴቶች ተኮልኩለው የሚያሰናዳቸውን ሰው ይጠባበቃሉ ስንታየውም እየተሯሯጠ ደረጃውን ከወጣ በኋላ (ሊፍቱ ስላመለጠው)ሰው ሁሉ ከተኮለኮለበት ቦታ ደረሰና ትንፋሹን መሰብሰብ ጀመረ ።
ሃና(V.O.)
በጊዜው ስለመጣ አልነበረም ፣ ነገር ግን በሃገሪቷ ካሉት ታዋቂ ባንኮች ውስጥ አንደኛው የስራ እድል ሲያወጣ ለመፈተን የሚመጣው ስራአጥ ወጣት ተቆጥሮ የማያልቅ በመሆኑ ፣ ያን ሁሉ ሰው ማስተናገድ ትልቅ ስራ ስለነበር ነው ።
ከመጡትም ወጣቶች ውስጥ ስማቸው እየተጠራ ለመፈትን ብቁ ሆነው የተገኙት 648ቶቹ ብቻ ነበሩ ።
ስንታየው መቀመጫ ባለመኖሩ እንደቆሞ እንደሰዉ መጠባበቅ ጀመረ ። ቀደም ሲል የመመዝገቡንና ፊሉን የማስገባቱን ስራ እታች ጨርሶ በመምጣቱ።
ትንሽ ቆይቶ አንዱ የቀበሌ ሰራተኛ ጩኸትና ያለውና የባንክ ቤት ሰራተኛ ልብስ ያረገ መላጣ ሰው ከአንድ ጥግ ቆሞ የሰዎችን ስም ይጠራል ሰዉ ወዲያው ዙሪያውን ከቦ ያደምጣል ። የተጠሩት ሰውየውን አልፈው ከኋላው ይቆማሉ ።
ሰውየው
ስንታየው አባተ!?
ሃና(V.O.)
ከነዛም ውስጥ ስንታየው አንደኛው ነበር ምንም እንኳን የስራውንም ሆነ የፈተናውን ይዘት ባያውቀውም።
ስንታየው ሰዉን ሰርስሮ አልፎ ከተጠሩት ጋር ተቀላቅሎ የስም መጥራት ፕሮግራሙ ካለቀ ወዲያ ሁሉም በዚሁ ሰውየ እየተመሩ በኮሪደሩ ላይ ይራመዳሉ።
ሰውየው
ስልካቹን አጥፉት እ? እንደ ሕጻናት እናንተን መቆጣጠር የለብንም ! ሰዓቱ ስለሄደ ፈጠን ፈጠን አርጋቹ ስሩ እ?
ወጣቱ ይከተለዋል ከዛ አንድ በር ሲከፍትላቸው ሁሉም ወደ በረቱ እንደሚገባ መንጋ ተጣበው ይገባሉ ። ቦታ ቦታቸውን ከያዙ በኋላ ፈተናው ይጀምራል ።
ጊዜው ከሄደ በኋላ ምናልባትም ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ ተፈታኞች ፈተናቸውን የሙጥኝ እንዳሉ ነበር ስንታየው ግን ፈተናውን ከጨረሰ ቢቆይም ራሱን በሁለት እጆች ይዞ ስለሩት ያብሰለስላል ። እስኪብርቶውን አንስቶ አንዳንድ ቃላት ላይ ያሰምራል መልሳቸው ላይ ካከበበ ቢቆይም ። ወዲያና ወዲህ ያያል አሁንም ጊዜው ሲሄድ ሰዉየው ከሌሎች ሴቶችና ውንዶች ስብጥር ጋር መንገዋለሉን ያቆምና
ሰውየው
5 ደቂቃ ይቀራችኋል!
5 ደቂቃ ይቀራችኋል!
ስንታየው ለመጨረሻ ጊዜ ፈተናውን እየገለጠ መልሶቹን ሲያረጋግጥ ከአንድ ገጽ ወደ ሌላ ገጽ ሲሄድ የነበረው ቁጥር የተለያየ እንደሆነ ያስተውላል ። ያም ገጽ ፊትና ጀርባ የሆነው ከሌሎቹ አንጻር ወፈር ያለ ነው ፣ ሲያብተለትለው ሁለት ገጽ ይሆናል ። ሁለት ገጽ ዘሏል ። ሌላ ጣጣ!
በ5 ደቂቃ ውስጥ የቀሩትን ጥያቄዎች መስራት ተያያዘ ፣ ግማሹ እንጊሊዘኛ ግምሹ ደሞ ሒሳብ በመሆኑ ግምት በሚመስል ፍጥነት እንግሊዘኛውን እየተወናበደ ከሞላው በኋላ ሒሳቡን ለመስራት ማውጣት ማውረዱን መቀነስ መደመሩን ጀመረ ።
ሰውየው በስሩ ሲያልፍ ባዶ መልሶችን አይቶ በስንታየው ፈገግ ይላል ስንታየው ቀና ሳይል ይቸከችካል ። ሰውየው ወደፊት አምርቶ ከሁሉም ረድፎች መሃል ይቆምና
ሰውየው
እሺ አቁሙ ? ፈተናውን በየመደዳቹ እንቀበላለን ? መስራታቹን አቁሙ
ፈታኞቹ ከመጀመሪያው ጀምሮች በየረድፉ ፈተናውን መቀበል ይጀምራሉ ። ስናትየው ይሞነጫጭራል ሌሎች ተፈታኞች አይተው እስኪታዘቡት ድረስ ።
ፈታኟ
ልቀበልህ?
ሴትየዋ መጥታ ስትቀበለው 3 ጥያቄዎችን በግምት አከበበና አስረከባት ። በባከነ ሃሳብ ተውጦ ተቀመጦ ወደምንም ያያል
INT. የነአቢቲ ቤት - ማታ
'ጣይቱ' ከራሳቸው ከቀለምና ከነገሮች አቀማመጥ ብዙም በማይለው በነአቢቲ ቤት ተቀምጣ በባከነ ሃባስ ተውጣ ውደ ቦርጫሙ ቲቪ ታያለች ።እማሹ ቡናው ስር ተጥዳ እንዲሁ ሽቅብ ወደ ቴቪው ታያለች ። እሳቱ እቶን መስሏል ፣ የቡናውም ጀበና ይንሰረሰራል ። ቴቪው የቱርክ ፊልም እያሳየ ተዋናዩ የፍቅሩን መጠን ከፊቱ ለነበረችው ሴት ይሸልልላታል ።
ተዋናዩ
መላ ኢስታንቡልን አቃጥልልሻለው
እና የመሳሰሉትን ይለፍፋል ።
አቢቲና ሃና ከአንድ ሶፋ ተጣብቀው ተቀምጠው ቴቪውን እያዩ እናቶቻቸው ወደነሱ ዞር ሲሉ ደብተራቸው ላይ መጻፍ ይቀጥላሉ ።
ሃና(V.O.)
ለረጅም ጊዜ በቤታችን ቴሌቭዥን ባለመኖሩ እናቴ የነአቢቲ ቤት ቡና ለመጠጣት በሄደች ቁጥር ተከትያት እሄድ ነበር። ከራዲዬው ወሬ ብዙ እጥፍ ይሻላል!!
FLASHBACK
እናቷ ሞቅ ያለ ስልክ እያወራች ነው ። ጮክ ብላ ። ከፊቷ የነበረውን ክሰል ከእግሮቿ አስጠግታ ትሞቃለች። ከት ብላ ትስቃለች ።
ሃና አባቷ ተንጋሎበት ከነበረው ሶፋ ግርጌ ወደነበረው ራዲያ ተጠግታ ምንም ከማያሳየው ቦርጫሙ ቴሌቪዥንን እያየች ተቀምጥ ስትቀያይር ብትቆይም ደና ነገር አልነበረም። ሲሰለቻት መቀያየሩን ትተውና ዝም ብላ ትቀመጣለች
ጋዜጠኛው(V.O.)
ጠቅላዩም አክለው እም የተደረገው ነገር ሃገሪቷን ብቻ ሳይሆን መላው ዓለምን አደጋ ውስጥ የሚከት ስለመሆኑ ተናግረዋል የሰሜን ኮሪያ ባላስቲክ ሚሳዬሎች ሙከራ ከፍጻሜ ሊደርስ እጅጉን የራቀ ይመስላል ተያይዞም ደቡብ ኮሪያ ይህ ቀጠናዊ እንቅስቃሴ የከፋ መዘዝ ይዞ እንደሚመጣና ተጎጂ ሊሆኑ የሚችሉት አካላት ቁጥራቸው ያቅ ያለ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቃለች . . .
በጋዜጠኛው ጆሮ የሚያደነቁር አነጋገርና በእናቷ ጮክ ያለ ወሬ መሃል ሁና በመሰላቸት ወደ ግድግዳው እያየች ጆሮዋን ትይዛለች።
INT. የነአቢቲ ቤት - የቀጠለ
ስንመልሰ ሃና ቀና ብላ እያየች እናያታለን ። እማሹ የቀዳችውን ሶስተኛ ቡና ለአቢቲ ትሰጠዋለች
እማሹ
እንዳትደፋት!? ነግሬሃለው ?!
አቢቲ በሁለት እጆቹ ይዞ ፊቷላይ ደስታም ሆነ ሃዘን ወደማይታየው 'ጣይቱ' ያቀናል ቀስ እያለ። እየፈራና እየተባ ። ቀስ ብሎ ከ'ጣይቱ' ፊት ሲኒውን ሲያስቀምጥ
እማሹ
ኡ . . . ኡ?! ደፍተኽ ጨረስከው እኮ! ምን ያለኸው ከረፈፍ ልጅ ነህ?
ጣይቱ ግን ከውጪ የሰማችው እኛም የሰማነው ነገር በመኖሩ አይኗ ወደበሩ ነበር ። ከበሩ ስር የተቀመጠችውም እማሹ አይኗን ተከትላ ወደበሩ አየች
ጣይቱ
ምንድን ነው? ድመት ነው?
እማሹ
(በሩን ገርበብ አድርጋ ካየች በኋላ)
ነው መሰለኝ?
ጣይቱ
ሂጂ አስወጪው ያራል ? ቶሎ በይ?
ሃና ጫማዋን እየጎተተች ከመፍጠኗ የተነሳ በሩን ከፍታ ትወጣለች ፣ እነ ጣይቱ ወደ ቦርጫሙ ቲቪ አይናቸውን እንደመለሱ
ህጻን ሃና(O.S.)
ፍላት ስክሪን!!!!!!!!!!!!!!
ሰፈሩን በጩኸት ታናጋዋለች ። ጣይቱና እማቹ ከቤቱ እየሮጡ ይወጣሉ ። አቢቲም ይከተላቸዋል።
የሰፈሩ ሰው ሁሉ ከቤቱ ብቅ ብቅ እያለ ይወጣል ጩኸቱ ባለመብረዱ
ህጻን ሃና(O.S.)
ፍላት ስክሪን !! ፍላት ስክሪን!!
ፍላት ስክሪን ተገዛ!!
int. የነጃምቦ ቤት - የቀጠለ
ጣይቱና እማሹ ወደቤቱ ሲገቡ ጃምቦ እየጮኸች የነበረውን ልጁን ሊያረጋጋ ሲጥር እሷ ደሞ እሱ ይዞት የመጣውን የቴሌቭዢን ካርቶን ልትከፍት ስትሞክር ያገኛሉ ። ጃምቦ ቆሞ ጣይቶን በተማጽኖ አይን ይመለከታትል
እማሹ
ምንድን ነው ሚያስጮህሽ አንቺ!
በጣይቱ ስር አልፋ በእምብርክኳ ወደነበረችው ሃና ስታቀና ጣይቱና ጃምቦ በአይን እየተነጋገሩ ነበር ። አንዴ የሱ ፊት በተማጽኖ አንዴ የሷ ፊት በጥያቄ አንዴ እሱ በይቅርታ አንዴ እሷ በመራራት አንዴ እሱ በደስታ አንዴ እሷ በደስታ ፈገግ ፈገግ ሲሉ ሲተያዩ አንዴ እሱ አንዴ እሷ በእይታችን ይገባሉ።
የሰፈሩ ሰው በሩ ላይ ተኮልኩሎ ወደውስጥ አንድ አንድ እያለ ይገባል ።
ጣይቱ
አይ የልጅ ነገር ፣ አስደነገጠቻቹ አደል !
አንዲት አሮጊት
ምን መጣ ብለን እኛማ
ከዚህ ወዲያ ያለው ነገር በስሎ ሞሽንና እንደሰመመን(በመቆራርጥ) ሆኖ የሚቀረጽ ነው
ሃና ካርቶኑን ከአቢቲ ጋር ሁነው እየቀደዱት ጠባቧ ቤት በሰው ተሞልታ መሳሳቅ ሲጀምሩ ጣይቱ ወድባሏ ስታየ
CUT TO:
INT. የነጃምቦ ቤት - ለሊት ሊጠጋ
ሃና(V.O.)
ያን እለት ማታ ከደስታ ብዛ መተኛት አልቻልኩም
እግሮቿን አቅፋ ይዛ መሃል ከነበረው ሶፋ ላይ ተቀምጣ ቦግ ወዳለው ቴሌቪዥን እያየች ። በግራና በቅኝ ትይዩ ተቀምጠው ሲተፋፈሩ ሲተፋፈሩና አይን ለአይን መተያየት ሲያቅታቸው ይቆያሉ።
ጃምቦ ወደወምበሩ ጠጋ ብሎ ክንዶቹን ላስቲክ ከተሸፈነው ጠረጴዛ ላይ አስደግፎ ሲጠጋ የሃና እይታ ውስጥ ይገባል።
ጃምቦ
ከዚ ወዲ አንድ መጠጥ ብቀምስ ሰው አትበይኝ
ቃል እገባልሽላው ።
ጣይቱ
እናያለን
EXT. ሰፈራቸው ውስጥ - የቀጠለ
ባርች ከመጠጥ ቤቱ ፊት ለፊት ከነበረው መንገድ ቆሞ ወዲህና ወዲያ ሲመላለስ ይቆያል ሰዓቱን ሲመለከተው እኩለ ለሊት ሊሆን ትንሽ ነው የቀረው ። በጨለማው ውስጥ ወደምትንቦገቦገው መጠጥ ቤት ያቀናል ፈጠን ፈጠን እያለ ።
ሲደርስ ወደውስጥ ሊጠልቅ ሲል እየጮሁና እየዘፈኑ ከሚወጡ ሰካራሞች ጋር ይጋጠማል።እነሱን በርጋታ ካሳለፈ በኋላ ወደውስጥ ይገባል ።
INT. መጠጥ ቤቱ ውስጥ - የቀጠለ
ወደውስጥ ሲገባ እመቤቷ አንዳንድ ወምበሮችን እየገለበጠች የተቀሩት ደምበኞቿ የመጨረሻውን ብርጭቋቸውን እየጨለጡ ነበር ። እንደዚ አምሽቶ የሚመጣውን ባርችን ቀና ብላ ስታየው ሰልከክና ሞላ ያለው ጠይም ፊቷ ይፈካል።
ባርች
ልትዘጊ ነው እንዴ ?
እመቤት
ተቀመጥ ችግር የለም
ባርች
እንዳላስቸግርሽ
እመቤት
አረ ተቀመጥ ግድ የለህም ?!
አንዱ ሰካራም
ተቀመጥ!!! ጋሽዬ!!!!
ጃምቦ ፈገግ እያለ ውደውስጥ ወደ ባልኮኒው ሄዶ ይቀመጣል። እመቤቷ ከባልኮኒው ጀርባ ሄዳ ትቆማለች ።
እመቤት
እሺ ምን ልታዘዝ?
ባርች
ያን
እመቤት
ጓደኛህም ትናንት መጥቶ በሃይላንድ ይዞ ነው የሄደው ባይገርምህ
ባርች
ስንት ዓመት አብሯት የቆየችው ጓደኛው አልፈልግህም ብላው ሄዳ ነው ።
እመቤት
ማ?
ባርች
በሃይላንድ የወሰደው ?
እመቤት
ባለትዳሩን ነው እኔ ያልኩህ
ባርች
ጥ! ነው እንዴ ?! እኔ ደሞ ቦቸራ ነበር ያሳሰበኝ
ባርች
ይህኛውም ለካ . . . እህ?!
እመቤት
ስለጓደኞችህ ብዙ ታስባለህ ?
ምን ሆንኩኝ አለች ልጅቷ?
ባርች
ምን ይታወቃል የናንተ ነገር? የሰው ልብ መስበር ብቻ ነው ምታቁት?
እመቤት
ተው እንጂ ?! ይሄኔ ጓደኛህ ይሆናል ልቧን የሰበረው
አንዱ ሰካራም
ጋሽዬ ?! . . . ሙዚቃ የለም እንዴ!?
እመቤት
ልንዘጋ ነው ጋሼ?!
ከበሩ ስር የተቀመጠውን ፋዛዛ አስተናጋጅ በአይኗ ስታመለክተው ልብሱን(የታጠቀውን ሂሳብ መቀበያ) ያወልቅና ወደሽማግሌው ሄዶ ሊያስነሳቸው ይጥራል በትህትና ሌሎቹ ከተቀመጡበት ሂሳባቸውን ቁጭ ቁጭ አድርገው በመውጣት ላይ ነበሩ ።
ባርችና እመቤቷ አይናቸውን ሲመልሱ አይናቸው ይጋጭና እንደለመደችው ምትገባበት ይጠፋታል ። ማፈሯን ኮራ ባለው አተያየቷ ለመደበቅ ሞከረች ። ባርች እንዳዘነና በአኳኋና እንደተዛናና ሆኖ እያቀረቀረ ፈገግ ይላል መጠጡን እያወዛወዘ ።
ሰካራሙ
ምንድን ነው ይሄ ሙዚቃ!!!
ማ ሞቶ ነው?!
በቤቱ የተከፈተውን ለስለስ ያለውን ሙዚቃ ሲያጥላሉ
አስተናጋጁ
ይነሱ ጋሼ ይነሱ?
እመቤቷ ወደ ኋላ በሚወስደው በር በኩል ትሄዳለች። ባርች ሰዓቱን ይመለከታል የሚጠባበቀው ነገር እንዳለ ሁሉ ።
ሰካራሙ
ልቀቀኝ ወዲያ?!
የደገፋቸውን አስተናገጅ እየገፉ ራሳቸው ሊደፉ እያሉ ። ከቤቱ ይወጣሉ ። ጭር ይላል ቤቱ ባርች ኩባያውን በፍጥነት ጎንጨት ጎንጨት ይለዋል ። እመቤቷ ጊዜ ካለፈ በኋላ ከሃላ ትወጣለች።
እመቤት
ሄዱ እንዴ ሰዎቹ?
ባርች
ትንሽ ቆዩ ?
እመቤት
አይ . . . ወምበሩን ሳያስተካክለው ሄደ?
ከባርች ጀርባ ሄዳ ወምበሮቹን መገልበጥና ከመሃል የነበሩትን ወምበሮች ዳርና ዳር ማስያዝ ጀመረች ። ባርች ትንሽ ጠብቋት ለመነጋገር የማያመች ሁኔታ ውስጥ መሆኑ ስለገባው መጠጡን ጨለጠውና ከመቀመጫ እየተነሳ
ባርች
ከመሸ መጣሁ መሰለኝ?
ስንት ልቀጣ?
እመቤት
ለአንድ ብርጭቆ አናስከፍልም። ባይሆን ስራ ብታግዘኝ እንደከፈልከኝ እቆጥረዋለው?
ባርች
እንደዛ ከሆነማ ሁሌ በዚ ሰዓት መምጣቴ ነው በቃ!
ከኪሱ ብር አውጥቶ ከጠርሙሱ ስር ያስቀምጠዋል ።
ባርች አንደኛውን ወምበር ወደጎን ለመግፋት ስትታገል ያያትና ያግዛታል ። እጃቸው ይነካካል ፣ ይተያያሉ ። የነበረው ለስለስ ያለ ሙዚቃ አልቆ አዲስ ሙዚቃ ይከፈታል የሚኒሊክ ወስናቸው ማምቦ ሳምቦ ይከፈታል።
ባርች
ደና እደሪ?!
ብሎ ሊሄድ ሲል እመቤት ከእመቤት ብማይጠበቅ መልኩ እጁን ይዛ ታስቀረዋለች ። ጀርባዋን ሰጥቷት የቆመው ባርች ፊት ላይ የህጻን ልጅ ደስታ ብልጭ አለ ፣በደስታ እምባ ያቀረሩት አይኖቹ ቀና ብሎ አምላኩን ሲያመሰግን በክሎዝ አፕ እናያለን ።
እመቤት
ስራው ገና አላለቀም
ፊቱን ወደሷ መለስ አድርጎ ወደ አማላይ ማንነቱ ተመልሶ
ባርች
ስራው ምንድን ነው
የያዘችውን እጅ እየጨበጠ ከወገቧ ያዝ አድጎ 'ሞምቦ ሳሞቦ' በርጋታ ያስደንሳታል ፣ እመቤት በድርጊቷ የተከናነበችወን ሃፍረቷ ወደ ደስታ እየተለወጠ ።
እመቤት
እሱን ወደጓዳ ገብተን ባሳይህስ
እየደነሱ እጇን ለቋት ሲደንስ በአጨፋፈሩ (ምንም እንኳን ልክ ቢሆንም) ከት ብላ ትስቃለች ። በእጁ እንድትደንስ ያመልክታታል እሷም ፈገግ ብላ የሃበሽ ልብሷን እንዳደረገች እግሮቿን እዚና እዛ ትጥላቸዋለች ። ጠባብ የነበረችው ቤት ለጭፈራቸው ሰፋች። ነጭ ብርሃን የሚተፋው አምፖል መደብዘዙን አቁም ቦግ አለ ። ሰው የሌለውም ቤት በሁለት ሳቅና ኮቴ ተንጫጫ ።
እየጨፈሩ እጁን ይዛው ወደጓዳ ገባች ።
ወዲያው ተመልሳ ወጥታ እየሳቀችና እየሮጠች በሩን ትዘጋዋለች ፣ መብራቱም እልም ይላል ። የመንገድ መብራቶቹ በመስታወቱ በኩል ታግለው ይገባሉ በዛም እመቤቷ ራዲዮውን አጥፍታ ወደጓዳ ትገባለች ሙዚቃውም ይደበዝዛል ።
ሃና(V.O.)
10ኛን ተንጠልጥሎ ካለፈ በኋላ የባርች ስም በሃይስኩሉ ገነነ።
EXT. ት/ቤታቸው - ረፋድ የቀጠለ
በአናታቸው በኩል አሮፕላን ከባድ ጩኽት አሰምቶ ሲያልፍ ሃናና ጓደኞቿ የአውሮፕላን መስኮት ይከፈታል አይከፈትም የሚለው ጨዋታቸው ላይ ነበሩ።
ህጻን 1
አይከፈትም አልኩህ
አቢቲ
ለምንድን ነው ማይከፈተው
አሮፕላን ውስጥ አየር ያለ መሰለህ እንዴ
ህጻን 1
ቢፈርጡስ ሰዎቹ አ? አ?
ሌሎች ሕጻናት ኳስ እየጠለዙ ሲመጡ ሁሉም ወደኳሱ ሮጡ ክርክራቸውን ረስተው
ከሚጩሁትና ከሚጫወቱት ተማሪዎች አልፈን በደረጃው የሚወጣውን ልጅ ስንከተልና በኮሪደሩ ላይ መራመድ ሲጀምር ሴቶቹ ሁሉ ወደሱ እያዩ ፣ እሱ ደሞ በፈገግታው እያሽኮረመማቸው እንመለከታለን ።
ሃና(V.O.)
ከሱ ጋር ልትሆን የማትወድ ሴት የለችም
ከሱ ጋር ሊያረጋት የማይችላት ሴት የለችም ።
ሴቶችን እንደልቡ ይለዋውጣቸዋል እንል ነበር የናጠጠ ድሃ ቢሆን ኖሮ ።
CUT TO:
INT. ክላስ ውስጥ - ቀን
ያ ተማሪ ቀዩ ፣ ከአንድ ጥግ ተቀምጦ መምህሩን እያየ ተቀምጧል ሴቶቹ ሁሉ ደሞ ወደሱ እያዩ ከበውት ተቀምጠዋል ፣ አገጫቸውን እጆቻቸው ላይ ተክለው ። ወደ ዞሮ እርሳስ ወይ እስኪብርቶ ሲጠይቃት እሷ ብቻ ሳትሆን ሁሉም ሴቶች እስኪብርቶ አውጥተው እንካ ይሉታል የሚያምር ፈገግታ እያሳዩት ። እሱ ተደናግጦ ወደኋላው ጠጋ ካለ በኋላ ፈገግ እያለ ከአጠገቧ ከነበርችው ሴት ይቀበልና መጻፍ ይጀምራል . . .
CUT TO:
EXT. ኮሪደሩ ላይ - የሆነ ጊዜ
ተማሪው ከሆነች ልጅ ጋር እያወራ በኮሪደሩ ላይ እናያልን ። ልጅቱ ደሞ አንድገቷን ሰብራ በስስት እያየች የሚለውን ትሰማዋለች ። በዛ ያሉ ሴቶች ደሞ እሷን ከላይ እስከታች እየገላመጧት በቅርብ ርቀት ቆመው ይታያሉ ።
ቁል ቁል ስንሄድ ህጻናት እየተደባደቡ እነአቢቲም የድብድቡ ተካፋይ ሆነው እናያለን ፣ አስቂኝ ድብድብ። ሃና ግን አልነበረችም።
CUT TO:
EXT. መንገድ ላይ - ከትምህርት ቤት ሲውጡ የሆነ ጊዜ
እነሃናና አቢቲ ከሌሎች ልጆች ጋር ለመሽቀዳደም በሚመስል መልኩ እየተሯሯጡ መንገዱን ይባርኩታል ። የተማሪ መንጋ መንገዱን ያጥለቀልቀዋል ። መንገዱ ሲበርድና ተማሪዎች አልፎ አልፎ ብቻ መታየት ሲጀምሩ ተማሪው ሌላ ሴት አቅፎ እየተራመደ እንደለመደው፣ እንደለመደው እየለፈለፈ ፣ አብራው ያለችው ሌላ ሴት ደሞ እንደለመደችው ፈዛ እያደመጠችው ዩኒፎርማቸውን ለብሰው ይመለሳሉ ።
EXT. ሰፈራቸው ውስጥ - የሆነ ጊዜ
የሰፈር ልብሱን እንዳደረገ መንገድ ላይ አሁንም ከሌላ ሴት ጋር ሲራመድ እናያለን ፣ እንደለመደው።
ሃና(V.O.)
የትምህርት ቤቶቹን ሴቶች በማጥናት ጊዜው ተጣቦ ስለነበር ትምህርቱን ለማጥናት አልቻለም ።
በዛም ምክንያት ስንታየው እንደለመደው በከፍተኛ ውጤት ሲያልፍ ባርች እንደ አባቴ የስራውን ዓለም ለመቀላቀል ተገደደ።
INT. የእመቤት ጓዳ - ጥዋት
ባርች አልጋው ላይ እንደተኛ ፣ እመቤት የሱ ባዶ ደረት ላይ እንደተኛች ፣ እሱ አይኑን ገልጦ በሃሳብ እየነጎደ እሷ ደሞ ለጥ ብላ በህልም ዓለም እየነጎደች . . .
ሃና(V.O.)
የሱ እቅድ የታክሲ ሹፌር ለመሆን ነበር ወላፈን ያለው ስራ በመሆኑ። ነገር ግን እናቱን 12ኛ ክፍል ከመግባቱ በፊት በማጣቱ ቀረኝ የሚለው ዘመድ አልነበረውም ።
ለዛ የመንጃ ፍቃድ ፈተና ለመውሰድ የሚያስፈልገውን ገንዘብ አባቴን ተበድሮ መማር ጀመረ። --
ታዲያ አብሯቸው ከሚማራቸው ተማሪዎች የከባድ ጭነት አሽከርካሪ መሆን ያበላል የሚል ወሬ ሲሰማ የታክሲ ሹፌር መሆኑን ረስቶ የከባድ ጭነት አሽከርካሪ ሆነ ።
CUT TO:
INT. ገልባጭ ውስጥ - ቀን
ባርችና ከዚበፊት አይተነው የማናውቀው ሰው ጎንና ጎን ተቀምጠዋል ። ባርች ሹፌሩ ያኛው ደሞ ጫቱን የሚያኝክ ተሳፋሪ ይመስላሉ ። ያኛው ፊቱን በመስታወት አየት ካደረገ በኋላ ከፊት ለፊቱ አስቀመጣት አሁንም ወደመስታወቱ አየት እያረገ ። ከፊታቸው ያለው የማያልቅ የበረሃ መንገድ ፣ ከአናታቸው ያለው የማይቀዘቅዝ ንዳድ ፣ የመሬቱ መወዛወዝ አሰልችቷቸውል ፣ አድክሟቸዋል።
cut to:
EXT. ድሬ የከባድ መኪና ማቆምያ ጋር - ቀን
ከገልባጩ እንደወረደ ባርች ሽርጡን አድርጎና ከላይ ያረገውን የነጭ ሸሚዝ እጀጌ ወደ ላይ ሰብስቦ በተኮሳተረ ፊት ወዲህና ወዲያ እያለ ቤቶቹንና ሁኔታዎችን ያያል
ከውጭ ለሚያያት እሱ እያያት እንዳለው ብቸኛና ዝምተኛ ትመስላለች ከተማዋ ።
ቆም ብሎ ካያት በኋላ ከ'ፍሬማችን' ይወጣል ።
cut to:
EXT. የሰፈሩ መንገዶች ውስጥ - የሆነ ጊዜ
ወደ ውስጥ ስንዘልቅና እንደ ባርች በመንገዶቿ ላይ ስንጓዝ ከተማዋ አይን አፋር እንጂ ዝምተኛ እንዳልነበረች እናያለን ።
ከአንድ ሻይ ቤት ተቀምጦ ጫጫታና ሁከት ወደጆሮው ፣ መለዋና ቡና ወደአፉ እየላከ ባርችን እናያለን ። ሰዎቹን ወዷቸው ተግባብቷቸው ።
ቡናውን ሲጎነጭ ቡናውን የምትቀዳለት ሴት ፣ የቤቱ ባለቤት የሆነችው ራቅ ብላ ተቀምጣ 'ሃያት' እያሉ ከሚጠሯት ደምበኞቿ ጋር ሞቅ ባለ ሁኔት የምትነጋገረው ቀይ ጸጉሯን በሂጃብ የሸፈነችው ሴት ጋር በአይናቸው መነጋገር ይጀምራሉ ። ምንም እንኳን በእድሜ ከሱ በትንሹ የምትበልጥ መሆኗ ግልጽ ቢሆንም ።
cut to:
INT. የነሃያት ቤት - የሆነ ጊዜ
ባርችና በመኪናው ውስጥ አብሮት የነበረው ወጣት በክፍሉ ውስጥ የነበሩት ብቸኛ እንግዳዎች ቢሆኑም አኳኋናቸው ሁሉ አብረዋቸው እንደነበሩት እንደሌሎቹ 4 ሰዎች ነበር ። እንደነሱ ሽርጥ አገልድመዋል ፣ እግራቸውን አነባብረው መጅሊሱ ላይ ተቀምጠዋል ፣ ጫቱን ጎረድ ቆረጥ እያረጉ ያኝካሉ። ሃያት ከባርች አጠገብ ተቀምጣለች እንደነሱ እያረገች ። ባርች ወደ ጆሮዋ ተጠግቶ የሆነ ነገር ማውራት ይጀምራል ።
cut to:
INT. የሃያት ቤት - የሆነ ጊዜ
ሃና(V.O.)
እዛ በሚሄድበት ወቅት አንዴም እንኳን ሆቴልም ሌላ ቦታ አርፎ አያቅም ከሃያት ቤት በቀር . . .
በተመሳሳይ ክፍል ውስጥ ባርች መጅሊሱ ላይ ተኝቷል ፣ ሃያት በሂና ያጌጡትን የእግሮቿን ጣቶች ቀይ ቀለም ትቀባቸዋለች ፣ አየት እያረገች ። ለብቻዋ የጣደችው ቡና ይንሰረሰራል ። እሱን ሳታስተውል በድንገት ስልኩ ይጠራል ፣ የባርች ስልክ ።
ስልኩ የነበረው ዳርና ዳር ላሉት ለሁለት መሃላቸው ከነበረ መጅሊስ ላይ ነው ።
FLASHBACK:
ባርች ጫቱን እየቃመ ሰውነቱ በምርቃና ጡዘት ግሎ እያላበው ስልኩን ከሽርጡ ላይ አስቀምጦ ስልኩ በቀስታ ወርዶ ከመጅሊሱ ሲያርፍ አላስተዋለውም ጮክ ባለ ሳቅ ተውጦ ስለነበር ።
INT. የሃያት ቤት - የቀጠለ
ሃያት ስልኩን በቶሎ ታነሳዋለች ፣ ከእንቅልፉ እንዳይነሳ ። ቡናው ይፈላል ።
ወደ ጆሮዋ እንዳስጠጋች ፣ የገጠር ዘዬ ያላት አንዲት ሴት ማውራት ትጀምራለች ።
ሴቲቱ(V.O.)
ምነው ጠፋህ የኔ አለም?
ቡናውን አውርዳ ተናገራዋ ሴት መሆኗን ስታውቅ ወደ ውጭ ትወጣለች ። በመጠራጠር ።
EXT. የሃያት ደጅ ላይ - የቀጠለ
ሃያት
(በድሬ ቅላጼ)
ማን ልበል?
ሴቲቱ(V.O.)
ተሳስቼ ነው መሰል . . . የጆዎሲ ስልክ አደለም እንዴ
ሃያት
አው ነው አንቺ ማነሽ የኔ አለም ምናምን ምትይው ?
ሴቲቱ(V.O.)
አንቺ ራስሽ ማነሽ? ጆዎሲ እኮ እጮኛዬ ነው . . .
ሃያት
ያላህ?! ምንድን ነው ምታዪው ሴትዬ በጥዋቱ መርቅነሽ ስልክ ተሳስተሽ ነው ሚሆነው ?
ሴቲቱ(V.O.)
የለም ? አልተሳሳትኩም ? የደወልኩት ጆሲን ብዬ ነው?
አንቺ እህቱ ነሽ? ሄሎ ? ሄሎ?
(ሁለቱም ገባቸው)
አወይ እኔ?!
ሃያት ስልኩን ከጆሮዋ አርቃ እንደያዘች እየሮጠች ወደውስጥ ትገባለች . . .
INT. የሃያት ቤት - የቀጠለ
ወደውስጥ ስትገባና ስትራመድ እንከተላለን ፣ ካሜራችን ይንቀጠቀጣል ፣ እሷ ከመሃል ከነበረው መጅሊስ ላይ ትወጣና ከሱ ከፍ ብሎ ከተሰቀሉት ግድግዳውን ከሚያስውቡት እድሜ ጠገብ እቃዎች ውስጥ ሻሞላውን ትመዛለች ፣ ወደተኛው ባርች ታመራና እላይ ላይ ወጥታ ከእግሮቹ መሃል ጨምድዳ ትይዘዋለች ፣ ባርች ከእንቅልፉ ይነሳል
ባርች
አ . . .?
ሃያት
አንተ እንደ ውሻ በሄድክበት ትዳራለህና እኔ ሃያት ያንተ ቅምጥ መሆን አለብኝ ?!
(ጨምድዳው)
ባርች
እሱን ነገር ዞር አርጊል አ . . .ሴትዬ እጅሽን አንሽልኝ . . . አ!
(እምባው ይመጣል)
ሃያት
ያላህ ?! በእኔ ላይ ነው አንተ?! እሰልብልሃለው ?!
ባርች
በስማም ወልደ መንፈስ ቅዱስ?!
(የሰነዘረችውን እጇን ይይዘዋል)
(ሃያት ትተፋበታልች)
ሃያት
እገልሃለው ያኢብኒ . . .ቱ ቱ ቱ ሃክ ቱ
ባርች
በስማም ወልደ መንፈስ ቅዱስ?
በስማም ወልደ መንፈስ ቅዱስ?!
ባርች በሌላኛው እጁ በጥፊ ይላታል ፣ ትታገላለች ፣ ይደግማታል በሃይለኛው ። ወደጎን ትወድቃለች ። ሻሞላውን አልጥልም ብላ እየታገለችው ነው በተራው እላዩዋ ላይ ወጥቶ ሻሞላውን ሊያስጥላት ይሞክራል ።
ሃያት ትታፋለች ፣ ወዲያው ሻሞላዋን ነጥቆ ይነሳል ፣
ሃያት
አንተ የውሻ ልጅ?!
(እንደ ውሻ እግሩን ትነክሰዋለች)
ባርች ይጮህና በነከሰችው እግሩ ገፋ ሲያረጋት ሽርጡ ይገፈፋል ፣ እስከ ጉልበቱ የታጠፈ ጅንስ ሱሪው ይታያል ። ሲገፋት ሃያት ከሚፈላው ቡና ፣ ከእሳቱ እጇ ያርፍና ጮክ ብላ ትጮሃልች ይሄኔ ባርች በመደናገጥ ይወጣል ሻምላውን ወርውሮ ፣ ሃያት ማቃሰትና መጮህ ትጀምራለች እየተንደባለለች ።
ሃና(V.0.)
በዚህ? . . .
INT. ገልባጭ ውስጥ - የቀጠለ
መኪናው ውስጥ እንዳሉ ጫቱን ከሚያኝከው ጓዴው ጋር ፣ መንገዱ አላልቅ ሙቀቱ አልወርድ ብሎ እየሰለቹ ባለበት ከፊታቸው አንድ የታጠቀ አካል በሩቅ ይመለከታሉ ። ጸጉሩን አጎፍሯል ፣ ሽርጡንም ታጥቋል ፣ መሳሪያውን በአንደኛው እጁ እንደያዘ በሌላኛ ደግሞ እንዲያቆሙ ያመለክታቸዋል
ባርች
ምንድን ነው?
ጓዴው
(ሙት እንዳየ ሰው ሆኖ)
አው! ሽፍታ ነው ?!
ባርች
እናቁመው?
ጓዴው
የምትሰጠው ብር አለህ?!
ባርች
ስንት?!
ጓዴው
5ሺህ! 10 ሺህ!
(ህን እያለ)
ባርች
ኬት አመጣለው አሁን?!
ጓዴው
ታዲያ ለምን ጠየከኝ ?! እንዳለው ሰው ?!
ባርች
እና ምን ላርግ!
(ሳያስቡት የመኪናውን ፍጥነት እየጨመሩት ነበር)
ጓዴው
ምን ታረጋለህ መሰለባችን ነው ? በቃ?
(እምባው ወጥቶ)
ባርች
ምን?!
ጓዴው
ይሰልበናል ?! አይሰማህም ይሰልበናል?! ቤቱ ውስዶ ግድግዳው ላይ ያንጠለጥለዋል ?! እንደ ጌጥ ?!
ባርች
ታዲያ ምን ላርግ? ምን ላርግ?!
ጓዴው
እኔ ምን አውቃለው ?! አውቃለው?
ባርች
ልጆች እንኳን ሳልወልድ
(ሽፍታው መሳሪይዋን ከትከሻው ያወርደዋል)
ጓዴው
ዝም ብለህ ንዳው?! እንዳታቆም?!
ባርች
ተኩሶ ቢገለን ይሻላል ?! አንሰለበም?!
ጓዴው
(ሲፎክር)
አንሰለብም! አንሰለብም!
(ሲያለቅስ)
ይገለናል በቃ?!
ሲኖው ይነጉዳል ፣ ሽፍታው ak-47ኑን አውጥቶ ይደግነዋል ፣ እስኪመቸው እየጠበቀ።
ሲቀርቡት ጊዜ ጓዴው ፊቱን ሲያይባት የነበረችውን መስታወት ከቦታዋ ያነሳና ፊቱ ላይ ያንጸባርቅበታል ፣ ሽፍታው ብልጭ ሲልበት ጥይቱን ብልጭ ያደርገዋል ። ሲኖውን ተጠግቶ በመቆሙ ወደኋላው በመደናገጥ ወደቀ ፣ የህጻናት ሸርታቴ የምታክል ዳገት ። በድጋሜ ተነስቶ እየሮጠ ከጀርባ ሊተክስ ቢምበረከክም አይኑ አብለጨለጨበት ። አንዴ ቢተኩስም ወደ የትም ነበር የተኮሰው ወደ ሲኖው ገላ።
ወደ መኪናው ስንመለስ
የመጀምሪያው ተክሱ የፊት መስታውቱን ሰንጥቆ በመግባቱ ጓዴው ክፉኛ ተመቶ ነበር ፣ ደሙ እዛና እዚ ተረጭቶ ከደረቱ ዝቅ ብሎ እየወረደ ነበር ፣ ደሙ እየወረደ ! እያቃሰተ !
ባርች
አይንህን እንዳጨፍን ?! አንተ?! እየሰማኸኝ ነው?
ጓዴው
ሆስፒታል አናገኝም
ባርች
እንደርሳለን ?! በርታ በርታ?!
ጓዴው
ቢያንስ አልተሰለብኩም
ባርች ጓዴውን ለማንቃት እየታገል መንገዱን ይቀጥላሉ
ባርች
መንደር መኖሩ አይቀርም በቅርቡ?! እ? አተ? አይንህን እንዳጨፍን?
ይትረፍ አይትረፍ ላናውቅ ገልባጩ ባለው ፍጥነት ሁሉ ሲገሰግስ እናያለን
ሃና(V.O.)
እና በዚ ምክንያት የከባድ ሹፌር አሽከርካሪነቱን ስራ እርግፍ አድርጎ ተወ።
INT. የሃያት ቤት - የሆነ ጊዜ
ብቻዋን በተቀመጠችበት በተጠቀለለው እጇ ስልኳን ወደጆሮዋ ደግና እስኪነሳ ትጠባበቃለች ።
ሲነሳ በዛኛው ወገን የነበረው ባርች እንደሆን እንሰማለን
ባርች(V.O.)
ሄሎ?
(መልስ አልነበረም - ከተደበቀ ለቅሶ በቀር)
የውልሽ ጥሩ ሰው እንዳልሆንኩ ይገባኛል? እና ይቅርታ ልልሽ እንኳን አይገባኝም . . . (ታቋርጠዋልች)
ሃያት
አርግዣለው?!
EXT. ሰፈራቸው - የቀጠለ
ባርች ይህን ሲሰማ ደንጋጦ ቀረ
ሃያት(V.O.)
ሄሎ? እኔ ብቻዬን ልጅ ማሳደግ አልችልም
ባርች
እመጣለው ?!
ሃና(V.O.)
ውሸት
ባርች
ብቻሽን አታሳድጊውም
ሃና(V.O.)
ሌላ ውሸት
ሃያት(V.O.)
በጣም ይቅርታ . . . ? ልጁን ግን ብቻዬን አልችልም! ያረቢ !
ከዚ ወዲያ ያለውን ለቅሷዋን በዝምታ ከሰማ በኋላ ስልኳን ስትዘጋው ጊዜ ራሶቹን ይዞ ቆመ ።
INT. የእመቤት ጓዳ - የቀጠለ
ባርች በቀስታ ይነሳል የተኛችውን እመቤትን ላለመቀስቀስ በሚል ፣ ሲሪውንና ሸሚዙን ካጠለቀ በኋላ ጃኬቱን እየደረበ ይወጣል
INT. መጠጥ ቤቱ - የቀጠለ
ልብሱን ለብሶ ሊወጣ ወደ በሩ ሲያመራ ክእይታችን ይሰወራል ፣ መልሶ ኮቴው ይቀርበናል ። ተመልሶ በእይታችን ይገባል ። ከመጠጡ ስር ያስቀመጠውን ገንዘብ 'ለቅሞ' ተመልሶ ከእይታችን ይወጣል ።
INT. የነጃምቦ ቤት - ጠዋት
መጠጥ አልነካም ብሎ የማለው ጃምቦ እቤቱ ይዟቸው በመጣቸው መነኩሴ ፊቱን ጸበል ይረጫል ፣ ሃናን ወደኋላ ስትሸሽ ከትከሻዋ ይይዛትና ከስሩ አስቁሞ ያስረጫታል። መረጨት አልፈለገችም ነበር ፣ የመነክሴውን ባዶ እግር እያየች በድንገት ቸብ ያረጓታል። ጣይቱ ከበሩ ቆማ የረጠበው ፊቷን እያበሰች ነው ።
በየክስርትና ስማቸው እየጠሯቸው ከረጯቸው ወዲያ ቤቱን መርጨት ጀመሩ . . . ሃና ፊቷን ልትጠርገው ስትል ፣ እናቷ በአይኗ ተይ ትላታለች ኣባቷም እጇን ይመልሰዋል።
int. ቤተ ክርስቲያን ጸበል ቦታ - ጠዋት
ከአንዱ መጸበያ ክፍል ውስጥ አንድ ህጻን ልጅ እየተጸበለ እናያለን ፣ ከጎኑ ከነበረው የመጸበያ ክፍል ደሞ አዋቂ የሚባል ሰው እያቃሰተ በእምብርክኩ ይጸበላል ።
EXT. ቤተ ክርስቲያን ጸበል ቦታ - የቀጠለ
ወደ ውስጥ ከሚገባው ምዕመን ፣ ከውጭ በጸበል የተሞሉትን ኩባያዎች ለማንሳት ከሚሞክረው ነጭ የለበሱ ምዕመናን መሃከል ቦቸራና ባርች ነጭ ያልሆነ ልብሳቸው እንግዳ አርጓቸዋል ። ኩባያቸውን አንስተው ወድ አንድ ጥግ ከሄዱ ወድያ ባርች ወዲያው ጠጥቶት የተቀረውን ፊቱ ላይ ሲያብስ ጃምቦ ገና አባታችን ሆይ ብሎ ጨርሶ አማትቦ መጠጣት እየጀመረ ነበር ።
INT. መስሪያ ቤት - ቀን ፣ አንድ ቀን
ስንታየው ደህና ለብሶ እንደሱ ደህና ለብሰው ከተቀመጡት ወጣቶች ጋር ከአንዱ ጥግ ተቀምጦ ከምሃላቸው ብቸኛ መስሎ ሹክሹክታቸን ይሰማል ፣ አንዳንድ ሰራተኞች ወዲህና ወዲያ ሲሉ ኮቴያቸው ያስተጋባል ።
ወጣቶቹ
8 ሺ ምናምን ሰው ነበር የተፈተነው ሲሉ ሰምቻለው . . . አሁን ሶስት መቶ ምናምን ሰው ነው የቀረው መሰለኝ . . . ስንት ሰው ነው ሚፈልጉት አልተነገረማ? . . . አረ ብዙ ነው ሚሆነው ይሄን ሁሉ ሰው አምጥተውማ ? . . .
ብቸኛ ብቻ አልነበረም ስንታየው የሚመስለው ተስፋ የቀረጠም ይመስላል ። አልጓጓም ።
በድንገት ያ ፈታኝ ሰውዬ ከአንድ ክፍል ይወጣና ተኮልኩለው ከነበሩት አመልካቾች መሓል እስኪቆም ይራመዳል ። በእጁ ስም ዝርዝር ያለበት ወረቀት ይዟል ። አመልካቹ ሁሉ የሚያስተጋባውን ኬቴውን ለማድመጥ ጆሯቸውን ፣ የአፉን እንቅስቃሴ ለማየት አይናቸውን ወደ ሰውየው መለሱ ።
ከምሃከላቸው ቆሞ
ሰዉየው
ስንታየው ደስታዬ?!
ወደ ምንም እያየ የነበረው ስንታየው አልሰማም
ሰዉየው
ስንታየው ደስታዬ?! የለም?!
ስንታየው ከሃሳቡ እየባነነ ፣ ነገር ግን ሳይደናገጥ ተነሳ ።
ሰውየው
አለሁ አትልም?!
ስንታየው አልሞቀውም አልበረደውም ።
የሰውየውን መራመድ ተከትሎ ከጀርባው ኮቴው እያስተጋባ ይከተልና ከአንድ ክፍል እንደገባ ሰውየው በሩን ከኋላው ይዘጋበታል
int. ቢሮው ውስጥ - የቀጠለ
ስንታየው ቆሞ ጎን ለጎን የተቀመጡትን ጠያቂዎች ሲያያቸው እንዲቀመጥ ያመለክቱታል ። አሁንም ከሃሳብ እንደመንቃት እያለ ከፊታቸው ይቀመጣል ። መጠየቃቸውን ይጀምራሉ ፣ ፋይሉን ዝቅ ብለው እያዩ።
INT. የስንታየው ቤት - የቀጠለ
ስንታየው ብቻውን ሶፋው ላይ ተኝቶ ጣሪያ ጣሪያውን እያየ ይቆዝማል ።
በድንገት ክፍት ከሆነው በር በኩል እንግዶች ይገባሉ
እንግዶች
ቤቶች?
ስንታየው ቀና ብሎ ያያል ወደ ኋላው ፣ እንግዶቹ ጃምቦና ባርች ነበሩ ። በእጃቸው ሙዝና ዳቦ እና ጁስ ይዘዋል ፣ ቆሎም ። ከተኛበት ስንታየው ሲነሳ
ጃምቦ
በግዜር በጊዜር አይገባም
(ጃምቦና ባርች ይስቃሉ - ስንታየው በትንሹ ፈገግ ይላል)
እንግዶቹ ሶፋቸው ላይ እየተሰየሙ
ባርች
ማዘር አሉ እንዴ?
ስንታየው
የለችም ወጥታለች ?
ምንድን ነው እሱ? ስጦታ ነው?
ባርች
ሰው ቤት ሲኬድ ባዶ እጅ አይመጣም ብለን ወደ ቤታችን ይዘነው ምንመለስ ነገር ይዘን መጣን
ስንታየው
ይዛቹት ልትመለሱ?
ባርች
(እጁን ልጆ ሙዝ እየመረጠ)
አው
ሁሉም ጸጥ ብለው ይቆያሉ ፣ እየተያዩ ። ባርችና ጃምቦ በደምብ እየተያዩ ። የሆነ ነገር እያቀዱ ነበር።
ባርች
(ከጃምቦ የማይሆን አስተያየት ስለደረሰው)
እና . . . ሰሞኑን እኮ ጠፋህ ፣ ሰፈርም ውስጥ አትታይም . . . እነ ብስሬ ሰፈር እንደለቀቁ ሰምተሃል?
(ስንታየው ቅንድቡን ይሰቅልና ከሙዙ መምረጥ ይጀምራል ከዳቦውም)
ኮንዶሚኒየም ደርሷቸው እንደነበር ታቃለህ? ስራው አለቀና ባለፈው ሳምንት ገቡ?
ጃምቦ
ሶስት መኝታ ቤት
ባርች
አው ሶስት መኝታ ቤት
ስንታየው
ቢያከራዩት ይሻል ነበር
(ዳቦውን አንስቶ ካየው በኋላ ሙዙን ብቻ እየበላው)
ባርች
አው ያው ዋናው ጉዳይ እሱ ሳይሆን - እነሱ ቤት አዲስ ሰዎች ገብተዋል ፣ ሴቶች ፣ ላጤዎች። እና ወንዱ ሁሉ አይኑን ጥሎባቸዋል።
ስንታየው
አንተስ?
(ጃምቦና ስንታየው ይስቃሉ)
ጃምቦ
አረ ለሱማ ልጆች ናቸው እነሱ!
(ሳቅ)
ባርች
ወደ ቁም ነገሩ እንመለስና . . . እሺ . . . አው ወደ ዋናው ጉዳይ እንመለስና ። 2ተኛዋ ልጅ ፣ ጠይሟ
ጃምቦ
የምታምረው
ባርች
አው የምታምረ ላንት የምትሆን ናት ። የተረጋጋችና ወጣ ወጣ ማትል ናት እንደ . . . አንት እንደ ምትወደው።
ስንታየው
ወጥ አረጋት እኮ
ጃምቦ
የምራችንን ነው? ምንም አያንስህም? እውቀት አለህ? ተምረሃል? ስ . . . እ ቁመናም አለህ? ሌላ ምን ያስፈልጋል?
ባርች
ምንም
ጃምቦ
ወደ 11 ሰዓት አካባቢ ነው ከስራ የምትመለስው
ባርች
11:30
ጃምቦ
በዛ ሰዓት ሰፈር ውስጥ ደህና ለብሰህ ወጣ ብትል ታያታለህ
ስንታየው
ትንሿስ?
ባርች
ትንሿ።
ስናታየው
15 ዓመት እኮ ነው አብረን የቆየነው በ3 ሳምንት ብቻ እንዴት እረሳታለው . . . በወጣሁ በገባሁ ቁጥር ደሞ በበራቸው ስር ነው ማልፈው?
ጃምቦ
ይኸውልኽ ወደድክም ጠላህም እውነታውን መቀበል አለብህ ። ከዛ ወዲህ አንዴ እንኳን አላናገረችህም? ፣ ምክንያቷንም አልነገረችህም? ስለዚህ ምን ትጠብቃልህ?
ባርች
ይሄ ማለት እኮ አልፈልግህም ተወኝ ማለት ነው
ስንታየው
ለምን?
ለምን በድንገት ተንሰታ እንዴት እንደዛ ትላለች?
በአንድ ሌሊት እን---?
ከበሩ በኩል አንድ ሰው ይገባል ፣ የስንታየው እናት ነበሩ
ባርች
(ከመቀምጭው ተነስቶ)
ደና ዋሉ እማማ እንዴት ኖት
ጃምቦ
እንዴት ነው?
እናትየው
(ቸኩለው ነበር)
ውይ ?! እናንተ ምን እግር ጣላቹ ዛሬ ?!
የሆነ ነገር ሆኗል አደል ይሄ ልጅ . . . የሆነ ነገር ካልዞረበት አትመጡ ።
ትንሿም ጠፋች?
ባርች
እረ እንዲሁ ነው እንጠይቀው ብለን ነው
ጃምቦ
ምን ይሆናል እሱ
እናትየው
አይ የሱ ነገር? የሆነ ስራ ተወዳድሮ ነበር አልሆንልህ ካለህ አትዘን እያልኩት ነበር
ስንታየው
ገና ውጤት አልወጣም እማ?
(ብዙ ጊዜ ነግሯቸው ነበር የተቀበሉት ባይመስልም)
እናትየው
በል እሺ ተነስና ምግብ አቀርብላቸው
ባርች
ያቀርባል ያቀርባል
እናትየው
(ወደ ጓዳ እየገቡ)
ለቅሶ ቤት ልሄድ ብዬ ነጠላዬን ረስቼ የኔ ነገር
ባርችና ጃምቦ ይቀመጣሉ ።
እናትየው ወዲያው ተመልሰው ይመጡና ክፍሉ ለቀው እየወጡ
እናትየው
በሉ ተጫወቱ
ጃምቦ
እንጫወታለን እሺ?
ባርች
የምን ስራ ነው?
(ከወጡ በሁዋላ)
ስንታየው
ዝም ብሎ ነው ባክህ ? ቤት ውስጥ ከምቀመጥ ብዬ ነው የሞከርኩት ?
ድጋሜ ወደ ዝምታው
ጃምቦ
የድምበሯን ልጅ አወከው
(ወደ ባርች ዞሮ)
ባርች
ራሱን ያጠፋው?
ስንታየው
ራሱን ያጠፋው ለምን እንደሆነ ታቃለህ?
እናቱ ይገለኛል ብለው ፈርተው ውርሳቸውን ለቤተ ክርስቲያን ሲያስረክቡ . . .
(በእጁ እያመለከተ)
ጃምቦ
ማነው ያለው?
ስንታየው
ሳሚ ደላላው?
ጃምቦ
አሁን የደላላ ወሬ አምነህ ነው? ይሄኔ ስራ ፈልግልኝ ብለኸው ነው እንደዛ ያለህ?
ለምን መስለህ ራሱን ያጠፋው? አበሩን አውቃት?
ባርች
የዳሳሽ ልጅ?
ጃምቦ
አው እሷ ፣ እሷ ለካ ፍቅረኛው ነበረች ።
ባርች
አግብታ የለ እንዴ?
ጃምቦ
ከትዳሩ በፊት?! . . . ከሱ ጋር ፍቅረኛሞች ነበሩ። ለ4 ዓመት ምናምን አብረው ነበር የቆዩት ከዛ አልፈልግህም አለችው ድንገት ተነስታ
ባርች
ለምን?
ጃምቦ
ማን ያውቃል? እሷ ብቻ ነች ምታውቀው። ዝም ብላ አልፈልግህም አለችው ከዛ. . .
(በእጁ እያመለከታቸው)
ስንታየው
የ21 ዓመት ልዩነት ነው ያለን . . . ከእድሜው ወዲ ማን ትቀርበዋለች ፣ እንዳትቀርበው እንኳን ብር የለውም አበሩን ደሞ ምን አይነት ሰው እንደነበረች ቀድሞ ማወቅ ነበረበት ፣ ሩት ግን የኔ ሁኔታ ሌላ ጉዳይ ነው ። አብረን ነው . . . ስንት ጊዜ ነው የቆየነው?
ባርች
አስራ ስንት ነው? . . .
ጃምቦ
ጥ! ለማለት የፈለኩት ቀለል አርገህ ካላየኸው . . . እ . . .
የስንታየው ስልክ ይጠራል ። ያነሳዋል ባያውቀውም ።
ጃምቦነ ባርች እርስ በእርስ ማውራት ይጀምራሉ። ደምጻቸውን ቀንሰው ።
ባርች
ቁማር ተበልቶ መስሎኝ የሞተው
ጃምቦ
ጥ! ጥ! የሰዉ ወሬ ነው እሱ
ስንታየው
ሄሎ?!
ሲትየዋ
ጤና ይስጥልኝ ስንታየው ድስትዬ ኖት
ስንታየው
አው ማን ልበል
ሴትየዋ
እንኳን ደስ አሎት ስራውን አግኝተዋል
(ጸጥታ)
ቀጣይ ሳምንት መጀምር ይችላሉ ።
ስንኩን ዘግቶ ወደነ ባርች ይመለከታል ።
ስንታየው
ስራ አገኘሁ?
(ምንም አልመሰለውም)
የሰይፉ ይሆንስ ኤቦ ላላ የሚለው ሙዚቃ ይጀምራል
int. መጠጥ ቤት - የዛኑ እለት
ሙዚቃው በመጠጥ ቤት ውስጥ ጮክ ብሎ ይሰማል ፣ ስራ መያዙን አስመልክቶ ሊያከብሩ ከመጠጥ ቤት መሃል ላይ ተሰይመዋል ፣ የነጩ አምፖል ብርሃ ከት ብለው የሚስቁትን እነ ባርችና ስንታየውና ጃምቦን ያሳየናል ። ከበሩ ስር የሚቀመጡት ቀጮዎች ዛሬ የሉም ቢሆንም ከሁሉም ጥግ የሚመጣው ወሬና ክርክር ከሙዚቃው ጋር ተደምሮ በደምብ እንዳይሰማ ያረጋል።
ስንታየውና ባርች መጠጥ ይዘዋል ጃምቦ ታቅቧል።
እመቤቲቱ ባርችን አየት ታረገዋለ አሁንም አሁንም ። እየተሽኮረመመች ።
ባርች
አየህ? አየህ አደል? ሊነጋ ሲል ይጨልማል ሚባለው ለምክንያት ነው እ?
ስንታየው
ምን ጥቅም አለው? እሷ ከሄደ. . .
ጃምቦ
አ . . . ለዛሬ በቃ እርሳት ተመስገን በል ተደሰት ማንም የማያገኘውን እድል ነው ያገኘኸው !!
(እየወዘወዘው)
ባርች
ያች ደላላ ግን ለኔም ለምንድ ነው የማትፈልግልኝ ?
ጃምቦ
በምን? ጥበቃነት ነው?
(ከት ብሎ ይስቃል - ቦቸራም ፈገግ ይላል)
ባርች
ስራ አይናቅም? ለነገሩ ከዚ ሰፈር ወጥተህ አታውቅ ምን ታውቃልህ ስለ ህይወት?
ጃምቦ
ተበሳጩ እንዴ ጋሼ . . . እረ አያኩሩፉ ግድ የሎቱም
ባርች
የምሬን እኮ ነው አንድ ደህና ታክሲ ያለው ሰው አያገኝም
ጃምቦ
ለምን ራስህ አጠይቀውም?
ከበሩ በኩል የሚገባውን ቀጠንና ጎበጥ ያለ መሃከለኛ ቁመት ይለውን 'ሳሚ ደላላውን' ለመቀበል ከተቀመጠበት እየተነሳ ። ሲቀርባቸው ሞቅ ያለ ሰላምታ ተሰጣጡ ።
ሳሚ
ቦቼ እንኳን ደስ አለህ?
(እየተቀመጥ)
ምን ያህል ሰው ነው የተፈተነው የነበረው? 600 ምናምን ነው አደል? ከ600ው ሰው አንድ ቦቼ ብቻ አለፈ ቢባል ማን ያምናል? ወንድ ልጅ ስወልድ ስንታየው ነው ምለው?
(ጊዜ ሳያጠፋ ወደ ወሬው)
ስንታየው
እ?
ጃምቦ
600?
(ወደ ቦቸራ ያያሉ በመገረም)
ሳሚ
እኔስ እሱ አደል እንዴ የገረመኝ
ስናታየው
ብዙ ሰው ነበር ግን 600 አይሆኑም?
ከሆኑ የሆነ ያረከው ነገር አለ እኔ ማላውቀው እንጂ ከ600
ሳሚ
የውልህ እጄ ቢረዝም ቢረዝም ያን ያሃል አይረዝምም ከ600 ሰው ለይቶ አነተን ለማውጣት
ባርች
ቢሆንም አንተ ባታስታውሰው ማን ያስታውሰዋል ፣ በነካ እጅህ እንዳው ለኔም የሆነ ታክሲ ነገር ምናምን አታገኝም?
ሳሚ
እፈልጋለው እስቲ ?
ባርች
ያልሰራሁበት በረሃ የለም . . .
አስተናጋጁ መጥቶ ዝም ብሎ ሲገተር ጊዜ ያቋርጠዋል ፣
ባርች
ጠጣ ጠጣ መጀመሪያ በባዶ ሆድህ አላድክምህ?
(ሲጀነጅነው)
ሳሚ
ቀዝቃዛ ቢራ አምጣልኝ
CUT TO:
INT. ፍሪጅ ውስጥ - የቀጠለ
ቀዝቀዝ ያለው ቢራ ላቡን በጠርሙሱ ላይ እያንጠፈጠፈ እያንጸባረቀ እንመለከታለን። ከፍሪጁ ውጭ በርቀት እነጃምቦ ከተቀመጡበት ደብዘዘው ይታያሉ።
INT. መጠጥ ቤት - የቀጠለ
ጃምቦ ምራቁን ሲውጥ ፣ ጉሮሮው ከላይ ወደታች ይመላላሳል ።
አስተናጋጁ ወደመጣበት ይመለሳል ። ከጀርባ ወደ ፍሪጁ ሲያመራ እንመለከታለን ። ጃምቦ እነ ስታየው በጃቸው የያዙትን መጠጥ በመጎምጀት እያየ የሚሉት ነገር አይሰማውም ፣ ጆሮው ላይ ያልጎመጉሙበታል ።
አስተናጋጁ ተመልሶ ምጥቶ ቀዘቅዝ ያለውን ቢራ ቀደም ሲል ያያነውን አውጥቶ ከሳሚ ደላላው ፊት ያስቀምጠዋል ፣ ሲያስቀምጠው የጃምቦ ሰመመን ይበናል ። ድምጻቸውም ድጋሜ ሊሰማን ይጀምራል ።
ሳሚ
(ከቢራው ጥሙን ካራሰ ወዲያ)
ቦቼ አንድ ነገር እጠይቅሃለው እያልኩ?
ስንታየው
ብድር እንዳይሆን እንጂ
(ይስቃሉ)
ጠይቀኝ?
ሳሚ
ከሩት ጋር ተለያያቹ እንዴ?
(መጠየቅ አልፈለገም ነበር)
ስንታየው
ማን ነው ያለው?
(ባርችና ጃምቦ ይተያያሉ ውሸት በመሆኑ)
ሳሚ
አይ ማን ይላል እንዳው ለነገሩ ብዬ ነው?
ስንታየው
መኮራረፍ ምናምን ያለ ነገር ነው - ቀለል ያለ ነገር ነው
(ባርችና ጃምቦ ድጋሜ ይተያያሉ ቅንድባቸውን እየሰቀሉ)
ሳሚ
አይ . . . (ሊናገረው ነው) . . . ዲቡ ደስታዬ (ሊተወው ነው) . . .ዲቡ ደስታዬ . . . (መናገር አለበት). . . ሊያገባ ብሎ ሽማግሌ አሰባስብልኝ አለኝ . . . (ይቅር) . . . ሰውዬው የናጠጠ ሃብታም ነው ሶስት ሽማግሌ አይበቃውም
ባርች
እረ? ዲቡ ደስታዬም ሊያገባ ነው? ራሱ ሽማግሌ አደል እንዴ
(ይሳሳቃሉ)
ራሱ አይሄድም ፣ ለምን ሰው ያደክማል
ሳሚ
አው እድሜውማ ሄዷል . . . እኔ ራሴ ለዘመድ ነው ብዬ ነበር ፣ ሰውዬው ህ? የዋዛ አደለም!
(ይቅር)
(እየጠበቁት ነው)
(ይውጣለት)
አይ . . . ሽማግሌዎቹ የሚላኩት እነ ሩት ቤት ነው ብዬ ነው
ሙዚቃው ጡዘቱ ላይ ሲደርስ ጸጥ ይላል ፣ ዱብ እዳ። 'eyeye' የሚለውን የምድረክ ላይ ስራ በድጋሜ መስማት እንጀምራለን ። ሌላው ሁሉ ድምጽ ይሰክናል ።
ስንታየው ተነስቶ ሊወጣ ይላላ ፣ እነ ባርችና ጃምቦ ያረጋጉታል ፣ ይመክሩታል ። ስንታየው የሆነውን ማመን ስላቃተው ይከራከራቸዋል።
EXT. ሰፈራቸው መንገድ ላይ - በማግስቱ
አንድ ፍሬም ስንታየው ቆሞ የሆነ ነገር በመጠባበቅ ላይ ነው በጥዋቱ ። የስራ ልብሱ ለብሶ ወዲህና ወዲያ እያለ ይጠባበቃል ። በድንገት ከጀርባው ወደ እይታችን ትገባለች ። ስትመጣ ጊዜ ስንታየው በችኮላ እየተከተለ ሊያስረዳት ይሞክራል ፣ መራመዷን ስላላቆመች። ከእይታችን ይወጣሉ ። ተመልሰው ይገባሉ ሌላ ልብስ ለብሰው እንዲሁ እየጨቀጨቃት ፊቷንም ዞር ሳታረግለት ታስከትለዋለች። ድጋሜ ይገባሉ ሌላ ልብስ አድርገው በተመሳሳይ መንገድ ይራመዳሉ።
አንድ ምሽት ግን ወድ እይታችን ተመልሰው ሲገቡ ስንታየው እጇን ይዞ ያስቆማታል
ስንታየው
እንዴት ነው እሱን ምታገቢው ሰውዬው እኮ አባትሽ ይሆናል? እኔ ምን አጎደልኩብሽ?
ሩት
እጄን ልቀቀኝ እያሳመምከኝ ነው?!
ስንታየው
መልሽልኝ ምን ሆነሽ ነው ምን አረኩሽ? ምን አስቀየምኹሽ? ስራ ራሱ አግኝቻለው እሱ ከነበረ ያሳሰበሽ?
ሩት
እንኳን ደስ አለህ? አሁን እየመጣህ አታስቸግረኝ! እጮኛ ያላትን ሴት እንዲህ ማናገር ብልግና ነው? ልቀቀኝ ልሂድበት?
ስንታየው
(ግራ ይገባዋል)
ራስሽን አደለሽም ? እንዲህ አይነት ሰው አደለሽም?
ሩት
አታቀኝም ነበር ማለት ነው?
ስንታየው
የሆነ ነገር ሆነሻል? በባዶ ሜዳ እንዴት እንዲህ ? ቆይ ምንድን ነው ይሆንሽው? ሰዉስ ምን ይልሻል ኣባትሽን ስታገቢ? ብር ባይኖረው ኖሮ እኮ አንቱ ምትዪው ሰው ነው ?
ሩት
ባይገርምህ 51 ዓመቱ ነው ገና?
ስንታየው
ገና ? (በረጅሙ ይተነፍሳል) ራስሽን አትዋሺ? ሰውዬውን አትወጅውም?
ሩት
እወደዋለው ?! አፈቅረዋለው ?! ቀሪውን ሕይወቴን ከሱ ጋር ነው ማሳልፈው ?! ምን ታረጋለህ ?! ከ1 ወር በኋላ ልንጋባ ነው ። አዝዬው እዞራለው ምን ትሆን?!
እጁን ነጥቃ ከእይታው ትወጣለች ።
ስንታየው ደርቆ ሲያያት ከቆየ ቧኋላ
ስናታየው
መጦሩንም እንዳትረሺ?! . . . ዳይፐርም ቀይሪለት?!
ሩት(O.S.)
ለሰርጌ መምጣቱን እንዳትረሳው?!
ከአንዳንድ ቤቶች በኩል አንዳንዳ እናቶች ነገሩን በትዝብት እያዩ እንደነበር ሲያስተውል መንገዱን ይጀምራል በተቃራኒው ።
እኛ ደሞ ከታዛቢዎቹ ጋር እንቀራለን
INT. የታዛቢዋ ቤት - የሆነ ወቅት
ሃና(V.O.)
ጉዳዩ በሰፈራችን ትልቅ መነጋገሪያ ሆነ። ከዛም በላይ ቤተ ክርስቲያስ ሳይስሙ የማያድሩት እናቷ እንዴት ፈቀዱላት የሚለው ጉዳይ እብዙ ቤት የቡና ቁርስ ሆኖ ቀረበ
እድሜ የጠገቡና ያልጠገቡ ሴቶች ተሰብስበው ቡናቸውን ክበው ተቀምጠዋል ። አንደኛው የሰርጉን የመጥሪያ ካርድ ይዛ
የመጥሪያ ካርዱ የደስታዬ ውብአለም እና የሩት ዋለልኝ ሰርግ ይላላ።
የመጥሪያ ካርዱን ይዛ አየት ካረገችው በኋላ ወደ ወደ ወምበሩ አስቀመጠችውና ቡናዋን ተቀብላ መናገር ጀመረች እያማሰለች ። ሁሉም ፊታቸውን ወደሷ መልሰው መስማት ጀመሩ ። ተረት እንደሚሰሙ ሕጻናት ።
ሴትዬዋ አፏ ይንቀሳቀሳል ድምጿ ባይሰማም
ሃና(V.O.)
አንዳንዶች
INT. የሩት ቤት - ማታ
እናቷ
በአጥንቴ ላይ ተራምደሽ ካልሆነ እኔ በቁሜ እያለሁ እንዲህ አታረጊም ? ህ? ምንስ ቢሆን ያለውን ፍቀን በልተን እናድራለን እንጂ ገላሽን እንድትሸጪ እተውሻለው እንዴ? እግዜሩስ ምን ይላል? ሰዉስ ምን ይላል?
እናቷ ተቀምጠው እሷ ደሞ ካረጀው ሶፋ ጀርባ ቆማ ቁልቁል እያየቻቸው
ሩት
ስለዚ?
እናቷ
ምን ስለዚ አለው? አይሆንም በቃ ሰውየውን አታገቢውም
ሩት
ምን ታረጊኛለሽ?
(በሴራ እያየቻት)
እናቷ
አስሬሽ ጸበል ለጸበል ይዤሽ እዞራለው? ምን አረጋለው?
ሩት
ነው
እናቷ
አይ አታስፈራሪኝ? ነገርኩሽ በቃ?
ሩት
ነው እንዴ?!
(ወደ ጓዳ እየገባች)
እናትየው ቁጭ ብለው ራሳቸውን እየነቀነቁ በመገረም ባሉበት ትንሽ ቆይቶ ከጓዳ ጩኸት ይሰማል። እቃዎች ሲሰበሩና ሲወድቁ ። እናትየው ወደጓዳ ይሮጣሉ
INT. የነሩት ጉዳ - የቀጠለ
ሩት በእጇ ቢላዋ ይዛ ወደ እጇ ወደ መዳፏ አስጠግታ ቆማለች እቃዎቹ ሁሉ መሬት ላይ ተሰባብረው ወድቀዋል ። ከሌላኛው የእጇ መዳፍ ደም ይንጠባጠባል
ሩት
ራሴን ስገልልሽ ታርፊዋለሽ?
እናትየው
እረ ልጄ ተይ ? አረ የሰው ያለ?
(ሳይጮሁ)
ሩት
እንዳትጮሂ ? ሰው እንዳትጠሪብኝ?
እናትየው
(ማልቀስ ከጀመሩ ቆይተዋል)
እሺ! እናቴ? የፈለግሽውን አድርጊ እንደፈለግሽ?
ሩት
አገባዋለው!
እናትየው
እሺ ታገቢዋለሽ? ቢላውን ጣይውማ
ሩት
መርቂኝ . . . ውለዱ ክበዱ በይኝ
እናትየው
'ውለዱ ክበዱ'?
ሩት
ከልብሽ በዪኝ!!
እናትየው
ውለዱ! ፣ ክበዱ ፣ ለወግ ማረግ ያብቃቹ ፣ የሰው እጅ አያሳያቹ ፣ መንገዱ ቀና ሃገሩን አማን ያርግልን!
ሩት ቢላውን ትጥላለች ። ደሟን እያንጠባጠበች ወደሚያለቅሱት እናቷ ታያለች ፣ ስሜት በሌለው አስተያየት።
INT. የታዛቢዋ ቤት - የቀጠለ
ታዛቢዋ ቡናዋን ትመልሳለች ሁሉም ሲኒውን በአይናቸው ይከተላሉ። ምንም እንኳን የራሳቸውን ሲኒ ይዘው ቢሆንም ።
ሃና(V.O.)
አንዳንዶች እንዲህ ሲሉ
ሌላኛዋ ሴት ደሞ ቡናቸውን ልክ እንደቀደመችው ጎንጨት ጋረገች ወዲያ ከንፈሯን ማንቀሳቀስ ጀመረች። ሁሉም እንደቅድሙ ፊታቸውን ወደሷ መለሱ።
INT. የነስንታየው ቤት - የሆነ ወቅት
ጠረጴዛውን በክንዳቸው ተደግፈው አፍ ለአፍ ገጥመው ያወራሉ።
ስንታየው
እሺ እቅዱ ምንድን ነው? -- እንጣላለን።
ሩት
ለምን?
ስንታየው
ሁለታችንም ስራ የለንም - ጊዜው ደሞ በጣም ከፍቷል ምን እንበላለን
ሩት
ፍቅር ካለን ችግር የለውም
ስንታየው
ፍቅር የሚባል ምግብ አለ?
ሩት
እና ልትተወኝ ነው?
ስንታየው
አስጨርሽኝ
እንጣላለን . . . ከዛ አንቺ ዲቡ ደስታዬን ትጠብሽዋለሽ?
ሩት
እህ? ለምን?
ስንታየው
አስጨርሽኝ
ትጠብሺዋልሽ ። ቆንጆ ስለሆንሽ እድሉ ሊያመልጠው አይፈልግም ። ከዛ እንድታገቢው ይጠይቅሻል ።
ሩት
አህም? አህም?
(እየገባት ስለመጣ ራሷን ትነቀንቃለች)
ገባኝ ከዛ አርጅቶ ነው ብለን . . .
(በእጇ እናርደዋለን ትለዋለች)
(ስናታየው ራሱን ይነቀንቃል)
በጣም ብልጥ ነህ
ስናትየው
በጣም ቆንጆ ነሽ
እጅ ለእጅ ተያይዘው በግምባራቸው እየተያዩ ፈገግ ይባባላሉ ።
ሃና(V.O.)
ሌሎች ደሞ እንዲህ ነው ይላሉ ።
INT. የነጃምቦ ቤት - ማታ
ሲኒውን አስቀምጦ በሌላኛው እጁ የያዘውን የሰርግ መጥሪያ ካርድ እያየ ከቆየ በኋላ ወደ ሶፋው ወረወረው ።
ጃምቦ
ያሳዝናል!
ህጻን ሃና ካርዱን ከሶፋው አንስታ አየት ካረገችው በኋላ እሷም ጣል ታረገዋለች ።
ጣይቱ
(ቴሌቪዥኗን እያየች)
እረ ደግ አረገች? ስታክ ትኑር እንዴ ደሞ?
ጃምቦ
ምንም ቢሆን እኮ እድሜውን አቃጥላበታለች
ጣይቱ በእጇና በፊቷ 'አረ ኤይዳ' ትላላች ። ሊወድቅ የነበረውን ጀበና ትደግፈዋለች ።
ጣይቱ
የሰርጓ እለት ባየኋት
ጃምቦ
ምን እንደሚያበሳጫት ታውቂያለሽ?
(መልስ አልነበረም)
የሰርጓ ቀን ቦቸራ ሱፉን አድርጎ ከሌላ ሴት ጋር ጥሪውን አክብሮ ቢመጣ
ጣይቱ
እንደዛ ሊያረግ ነው? የሰው ህይወት ማበላሸቱን ያቅበት የለ?
ጃምቦ
ምንድን ነው ችግርሽ? ምን አርግ ነው ምትዪው?!
ጣይቱ
ምን አልኩኝ? ልጅቷን የሆነ ነገር ባያረጋት እንደዛ አትሆንም ነበር ብዬ ነው?
ጃምቦ
ምክንያቷን ማንም አያውቅም ለራሱም አልነገረችውም
ጣይቱ
ብትነግረው እንኳን ምን ብሎ ይነግርሃል?
(በመገረም ያያታል)
እና እንደዛ ነው የሚያረገው?
ጃምቦ
እኛማ እንደዛ ብለን ነበረ የመከርነው ግን እሱ 'አይኗን አላየውም' አለ. . . ቀረን።
ጣይቱ
'ቀረን'? ቀረ ለማለት ነው?
ጃምቦ
ቀረን እንጂ? አንሄድም።
ጣይቱ
አብረን የምንሄድ መስሎኝ?
ጃምቦ
ነውር አደል እንዴ? ለምን ብዬ ነው ምሄደው?
ጣይቱ
ነው እንዴ?! እንደዛ ነው? ከኔና ከሱ ማን እንደሚያዋጣህ እናያለን? አልበዛም እንዴ ?! . . .
ሃና ከቲቪው ትይዩ ከነሱ መሃል ብትቀመጥም ወሬያቸው ሃሳቧን አልሰረቀውም።
INT. የእመቤት ጓዳ - ማታ
እመቤት በለሊት ልብሷ መስታወቱ ፊት ጸግሯን እያስተካከለች ነበር። ያላትን ነገር ስትሰማ ፊቷን መልሰችና ተጋድሞ ወደሷ እያየ የነብረውን ባርችን እያየች
እመቤት
'ቀረን'?
ባርች
አው
እመቤት
እሺ እሱ ይቅር አንተ ለምንድን ነው ምትቀረው
(መልስ አልነበረም)
ከኔ ጋር መታየት አሳፍሮህ ነው እንጂ?
(ወደ አልጋው እየገባች)
ባርች
አላልኩም። ለምን ብዬ አፍራለው።
(ሊያቅፋት ሲጠጋ ፊት ትነሳዋለች)
እመቤት
መውለድ የማትችል 'አሮጊት!' ጋር ምን ልትሰራ ትታያለህ . . . ስንት ሰው ሲለምነኝ እምቢ ብዬ ነው ባይገርምህ
ባርች
ስለሰው ምን አስጨነቀሽ
ጀርባዋን ሰጥታው ትኝታ እንዳልሰማ ዝም ትለዋለች ለራሱ እያወራች ። ባርች ድጋሜ ሊጠጋት ብሎ አሁንም ፊት ስትነሳው ወደ ቦታው ይመለስና ግምባሩን ማሸት ይጀምራል
1 ወ ር ይ ቆ ጠ ራ ል
INT. የነስንታየው ቤት - ማለዳ
ጸሃዩ በመስኮቱ በኩል እየገባች ግድግዳዎቹ ላይ ከማረፏና ቤቱን ሁል ከማድመቋ በፊት በሳሎን ውስጥ ከቆመው ረጅም መስታወት ፊት የቆመው የስንታየውን ፊት ወርቃማ ታረገዋለች ። ራሱን እያስተካከለ ነበር ።
እናቱ ከአንደኛው ሶፋ ተቀምጠው ወደሱ እያዩ ቆዩና ራሳቸውን እየነቀነቁ ከንፈራቸውን መጠጡ
እናቱ
እንዳው ቢቀርብህ ምን አለ?
ስናታየው
ምኑ?
(በርጋታ)
እናቷ
ወዴት ልትሄድ ነው እንዲህ ምትሆነው ያለኸው
ስንታየው
ቀጠሮ አለኝ
እናቷ
ከማ ጋ?
ስንታየው
አታቂያትም
እናቷ
ሴት ናት?
ስንታየው
አዎ. . .
ዝም ብለው ይቆዩና የከነከናቸውን ነገር በመጨረሻም ይዘረግፉታል
እናቷ
ወደ ሰርጉ ነው ምትሄደው አደል?! ሳትዋሽ ንገረኝ?!
ስንታየው
እነሱ ንቀው ቢጠሩኝም ለራሴ ያለኝ ክብር እንዳልሄድ ያግደኛል?
እናቷ
አታልላታለው ብለህ ነው?! ነው እንጂ። አረጀች ብለህ
ስንታየው
ብታረጂ ብታረጂ ከዲቡ ደስታዬ አትበልጭም
እናቱ
መች አጣሁትና ቀድሞውኑም ፣ ሃሳብህ ሁሉ እዛ ነው
ስንታየው
ምን ልሰራ ነው ምሄደው?
(pause)
ሰው ስለተጠራ ብቻ ሰርግ ነው ማለት ተገቢ አደለም . . . ወደ መቃብሩ ሊሸኙት . . . ለመጨረሻ ጊዜ ሊሰናበቱት ሊሆን ይችላል የታደሙት
(ለርሱ ለመስታወቱ)
እናቱ ለራሱ የተናገረውን ስለሰሙ ደንግጠው ዝም ብለው ቀሩ ፣ መስታወቱ ፊት ቆሞ ራሱን እያየ የሚናገረውን ስንታየውን እያዩ
ስንታየው
ከ1 ከ2 ውር በኋላ መሞቱ ስለማይቀር ቀድመው ሊያለቅሱለት ይሆናል?
እናቱ
እንደፈራሁት! እንደፈራሁት! እባክህ ልጄ ምንም ነገር እንዳታረጋቸው? ከእግዜር ያገኙታል ተዋቸው
ስንታየው
(ከመስታወቱ ርቆ ወደ እናቱ እያየ)
እገለዋለው እኮ አላልኩም ይሞታል ነው ያልኩት ?
ትገለዋለች.
እናቱ
ማ? ሩት? ለምን ብላ?
ስንታየው
ለገንዘብ ሌላ ለምን ይሆናል?!
(pause)
እንዲህ አምሮብኝ ለቅሶ ቤት እንዴት እሄዳለው ስታስቢው . . . (አምሮበታል) . . . እንዴት ነው?
እጁን ዘርግቶ ከፊቷ ይቆማል።
እናቱ
ቱ! ቱ! ቱ!
(ወደ ውጭ እየወጣ ነበር)
ቀረባት!
EXT. የሰፈራቸው መንገድ - የቀጠለ
አንዳንድ ሴቶች ሰፈርተኞቹ በቆድሞ ፍቅረኛው የሰርግ እለት እንዲህ አምሮበት የሚወጣውን ስንታየውን ሲመለከቱ ከንፈራቸውን ማጣመማቸው አልቀረም ። ስንታየው ሳያያቸው ይጓዛል ። ብዙም ሳይርቅ ግን የኮቱን እና የሱሪውን ኪስ ይደባብሳል የሆነ ነገር ፍልጋ ፣ የሆነ ነገሩ የለም። የሆነ ነገሩን ለማምጣት በመጣበት መንገድ ይመለሳል ።
INT. የነስንታየው ቤት - የቀጠለ
እናቱ በሳሎኑ ላይ ወዲህና ወዲያ እያሉ ስንታየው ከጀርባቸው ያልፋል ።
እናቱ
ምነው? ምን ረሳህ?
ስንታየው
የሆን ነገር
(ውደ ጓዳ እየገባ)
INT. ጓዳ ውስጥ - የቀጠለ
ስንታየው ከአላጋው ራስጌ የነበረውን ትራስ ብድግ አድርጎ ይፈልጋል ፣ የለም ። ከአልጋው ስር ይፈልጋል ፣ የለም ። ከቁምሳጥኑ ላይ ይፈልጋል ፣ የለም ።ወደ ሳሎን ይመለሳል ።
INT. ሳሎኑ - የቀጠለ
አንድ ነገር በማሳናዳት ላይ የነበሩት እናቱን ያልፍና እየተጣደፈ ወደ ሚተኛበት ሶፋ ያመራል ። ትራሶቹን ሳያነሳ በእጁ ሰርስሮ ፈለገ ፣ 'የሆነ ነገር' አገኘ ። አውጣው
እናቱ
ምንድን ነው?
ስንታየው የሰርጉ መጥሪያ ካርድን ነበር ያገኘው። ነገር ግን ለእናቱ ሳያሳያት እንደመጣው እየተጣደፈ ይወጣል ።
ስንታየው
ምንም አደልም?
EXT. ሰፈር ውስጥ - የቀጠለ
ስንታየው በመጣበት መንገድ ሲመለስ ያዩት ፣ አሁንም መልሰው ያዩት የመንደሩ ሴቶች ትንሽ እንደሱው ዘንጠው መንገድ ጀምረዋል ። አንዷ የአንዷን ልብስ እያስተካከለች ፣ አንዷ የአንዷን ውበት እያሞገሰች ፣ ወጣ ገባ የበዛው የሰፍራቸው መንገድ ያደረጉትን ታኮ ጫማ አለቅም ብሎ እንዳይደፋቸው እየተጠነቀቁ ፣ ያረጉት ነጭ የሃበሻ ቀሚስ አጭሩም ይሁን ረጅም በእጆቻቸው አንጠልጠለው ይዘው ይጓዛሉ ። ከየቤቱ እየወጡ ወደ ሰርጉ።
INT. አዳራሽ ውስጥ - ቀን
አዳራሹ ሰፊና የተንጣለለ ነው ። ወለሉ የሚያንጸባርቅ ጣውላ ፣ ጣሪያው ከፍ ያለና ብርሃን የሚያስገቡ ናቸው ፣ የናጠጠ ሃብታም ሊከራየው ወይም ሊገዛው የሚችል አዳራሽ።
ሃና(V.O.)
ምንም እንኳ ዲቡ ደስታዬ እንዲህ ያለ አዳራሽ ለመከራየት አቅሙ ያለው ባለሃብት ቢሆንም ከወደደው ቦታ የወደደውን እያረገ ለመኖር የሚችል ቢሆንም እድገቱና ኑሮ ከአንድ ከሰፈራችን ርቆ አያውቅም -
ያ የሆነበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለማንም ግልጽ አደለም ። አንዳንዶች እንደሚባለው ባለሃብት አደልም ፣ ጥሩ ብቻ ስለሚለብስ ነው ይላሉ። ሌሎች ደሞ ደግ ሆኖ በዙሪያው ያሉትን ሊረዳ ስለሚፈልግ ነው ጻድቅ ስልሆነ ይላሉ ።
በአዳራሹ ጸጥታ ሰፍኗል ፣ ታዳሚው ሁሉ ቆሞ ተንጋሎ ወደ ተከፈተው በር እየተመለከተ ነው ። ሰው በመብዛቱ ከሩቅ መለየት ባንችልም ቀረብ ቀረብ እያልን ስንመለከታቸው የሚያማምሩ አዳዲስ ሱፍ ያደረጉት ያልተተኮሰና አሮጌ ካረጉት ወንዶች እንዲሁም ጠባብና አጭር ፣ ቦርቀቅ ያለና የተቀዳደደ ቀሚስ ያደረጉት ልክክ ያለባቸውን የሃበሻ ቀሚስ ካደረጉት ሴቶች መሃከል ለመለየት እንችላለን ፣ የሙሽራውና የሙሽሪት ወገን። ልዩነታቸው በልብስ ብቻ አልነበረም በእድሜም ጭምር ነው አንዳንዶቹ ።
ጸጥታው እንደ ሰፈነ ነው ። ከአንዱ ጥግ አንድ ዲጄ ሁለት ትላልቅ ሞንታርቦዎች ደግኖ በመጠባበቅ ላይ ነው እንደሰዉ ። ከጎኑ ያሸበረቀ ባዶ መድረክ አለ ፣ አፋቸውን የከፈቱ የሙዚቃ መሳሪያዎች ያሉበት ።
ሃና(V.O.)
አንዳንዶች ደሞ እንደጀምበር እየጠለቀ ያለው እድሜው ሳያግደው እንደ ጥዋት ወጋገን እየፈካ ያለውን የሩትን ወጣትነት በቀላሉ የራሱ ለማድረግ ሲል ነው ከዚ ሰፈር ቀደሞውንም ያልወጣው ባይ ናቸው ከሰሞኑ ። ግን ማን ያውቃል? ጊዜ ካልሆነ?
ከታዳሚዎቹ መሃከል ሰርጎ ገቦችን እንመለከታለን ሁለት ጸጉረ ልውጦች ለቦታው ። ባርችና ጃምቦ ከእመቤትና ጣይቱ ጋር ሕጻን ሃናን ከፊታቸው አሰልፈው ። ወንዶቹ ሱፍ አድርገዋል የጃምቦ ትንሽ ቢሰፋውም ሁለቱም ግን አምሮባቸዋል ። ሴቶቹ ደሞ የሃበሻ ልብሳቸውን አድርገው አምሮባቸዋል ። የመጀምሪያዎቹ በመገኘታቸው ደስትኛ አይመስሉም ሴቶቹ ደግሞ ጓጉተዋል ፣ ወደበሩ እየተንጠራሩ ያያሉ ።
ባርች ራሱን በአሉታ ይነቀንቃል ። ሙዚቃው በትልቁ ይለቀቃል ፣ 'ጉርምርሜ ና ጉርምርሜ'
እይታችን ከበሩ ላይ ብቻ ይሆናል ፣ ብዙም ሳይቆይ ሚዜዎቹ ጥንድ ጥንድ እይሆኑ ይገባሉ ። 'ያሆበሌ ያሆበሌ' እያሉ እየተቀበሉ ። ሰዉ ያጨበጭባል ።
በሚዜዎቹ መሃል ግልጽ የእድሜ ልዩነት ነበር።
ጃምቦ
ሚዜዎቹ ራሱ እኩዮቹ ናቸው ።
እያንዳንዱን የወንድ ሚዜ በፍጥነት እንመለከታለን ፣ አንዳቸው ጸጉራቸው ገብቷል ፣ አንዳቸው መነጽር አርገዋል ፣ አንዳቸው ኩልኩልቲያቸው ወጥቷል አንዳንዶች እግራቸው ሰሏል ።
ባርች
ተከራይቷቸው ነው ሚሆነው
(ጣይቱ ገልመጥ ታረጋቸዋለች)
(ጸጥ ብለው ይቆዩና)
ጃምቦ
ስታስበው ወጣቶች መከራየት ያቅተዋል ።
ባርች
አንተ ብር ቢኖርህ እንደሱ ሃብታም ብትሆን እንደሱ ብታረጅና ሚዜዎች ብትቀጥር የወለድካቸው ልጆችህ የሚመስሉ ወጣቶችን ነው ምትከራየው ወይስ አብሮ አደግ ናቸው የሚባሉ ሽማግሌዎች? 'ስታስበው'?
ጃምቦ ሲያስበው ባርች ልክ ነበር ። ልክ በመሆኑ እየተገረመ ራሱን ይነቀንቅለታል። ስንታየው ጭንቅላቱ ይነካል በጣቶቹ ። አዋቂ ስለሆነ ።
ሚዜዎች እያለከለኩ ሲውረገረጉ ቆዩና ቦታቦታቸውን ይዘው ዳርና ዳር ቆሙ ።
በድጋሜ ሰዉ ወደ በሩ መመልከት ይጀምራል ፣ እኛም እናያለን ።
ሙሽራዬ የሚለው ሰፈን ይጀምራል ።
ከበሩ በኩል ወፍራሙ ሙሽራ ጸጉሩን እንዳረገው ሱፍ ያለ ጥቁር ቀለም ተቀብቶ ፣ ሰፊና ወፍራም ቆዳ ያለውን የቀይዳማ የሆነውን ፊቱን ተላጭቶ በረሃ አድርጎ ፣ ሳቁ ከዚኛው ጆሮ ወደዛው በሰፊው እየቀደደ ፣ የተሰደሩ ጥርሶቹን ብልጭ እያረገ ትልቁን ቦርጩን አስቀድሞ ፣ ሙሽሪት ደግሞ በአጭሩ ልዕልት መስላ ብቅ ይላሉ ። አስቂኝ ወይም አሳዛኝ ምስል ከሁለቱ አንዱ ።
በአንዱ እጁ አበባዋን በሌላኛው የዲቡ ደስታዬን እጅ አጥብቃ ይዛ ፣ ረጅሙን ቬሎ እየጎተተች በቀዩ ምንጣፍ ላይ ዳርና ዳራቸው ላይ እንደ እንጨት አጥር ከፍና ዝቅ ብለው የተሰደሩትን ሰዎች እየሰነጠቁ ያልፋሉ ። ሁለትም እጅጉን ተደስተዋል ።
ሰዉ በመገረም ወይም የጭፈራ ሰዓት ባለመሆኑ ዝም ብላል።
ስንታየው
ያሳዝናል
ባርች
ያገጣል እኮ ደሞ
ስንታየው
እሱስ ያግጥጥ እሷ ለምንድን ነው ምትስቀው
እመቤት
ሽ!!!!
ባርች
ደስ ብሏት ነዋ ፣ ከዚ ወዲ ራበኝ ጠማኝ የለም ።
እኔ ራሱ ባገባው ደስ ይለኛል ።
(ይስቃሉ)
ጣይቱ
ጥ!
ባርች
አስመሳዮች!!
ሙሽሮቹ በሰዉ ታጅበው ከሚዜዎቹ መሃል እንደቆሙ ትንሽ ቆይቶ ዲጄው በማይኩ
ዲጄው
እስቲ ለሙሽሮቹ አንድ ጊዜ
(ሙዚቃውን እየለቀቀው)
የኛማ ሙሽራ የተሰኘውን ሙዚቃ ለቀቀው ። ሙሽሮቹ እስክስታቸውን መምታት ጀመሩ ፣ ሚዜዎቹ ከበዋቸው እየዞሩ እስክስታውን ይመታሉ ሰዉ ከዙሪያቸው እንደሰፈፈ ።
ሃና(V.O.)
ለአብዛኛው የሰፈራችን ሰው እንዲህ ያለ አዳራሽ መግባት፣ እንዲህ ያለ ረጅም ቬሎ ማየት ከስንት አንዴ የሚያጋጥሙት ነገሮች ቢሆኑም ያሳደጓት ልጃቸው ካሳደጉት አባታቸው ጋር ሲጨፍር ማየት ከዛ በላይ እጃቸውን ከአፋቸው እንዲጭኑ የሚያደርግ ነበር ።
ጃምቦ ሊቀመጥ ሲል እመቤት በእጇ ታነሳዋለች ፣ እየቆነጠጠችው ያለ ይመስል እያመመው ወዲያው ተነሳ ። በመገረም ያያታል ።
ሃና(V.O.)
በአይነቱ ለየት ያለ ሰርግ ነበር ፣ የአዳራሹ ስፋት የምግቡ አይነት የሚታወቀውም የማይታወቀውም ብዛት ፣ የሚቀዳው መጠጥ
ከጊዜ በኋላ ሰዉ ብፌ ሊያነሳ ተሰልፏል ፣ ብፌው ከባህል ምግብ አንስቶ ምንነታቸው ወደማይታወቁ ምግቦች ተመድበዋል ። ባርችና ጃምቦ ወደ አንዱ አስቂኝ መልክ ያለው ምግብ እየተጠቋቆሙ ቆመዋል ። 'ምንድን ነው?' እየተባባሉ ይመስላሉ ። ወደወምበራቸው ተመልሰው እየተመገቡ ጃምቦ ከፊቱ የነበረውን መጠጥ በአይኑ ያባብለዋል ፣ ባርች አንስቶ ወደ ብርጭቆው ያንቆረቁረዋል
ባርች
የጥፋተኝነት ስሜት እየተሰማኝ ነው
ጃምቦ
ወድጄ አደለም የመጣሁት
ወደ ሴቶቻቸው ያያሉ በንዴት ።
INT. ባንክ ውስጥ - ቀን
ስንታየው ከአስተናጋጁ መስኮት በኩል ተጥግቶ ከሰራተኛዋ ጋር እየተነጋገረ ነበር ።
ሴትየዋ
ሁሉንም ነው?
ስንታየው
አው?
ሴትየው
እሺ
ስንታየው
(ሲያስብ ከቆየ በኋላ)
ግማሹን 50 50 አርጊው እንዳውም
ሴትየዋ
አውጥቼዋለው እኮ
ስንታየው
እባክሽ
int. አዳራሽ ውስጥ - የቀጠለ
ሃና(V.O.)
ከታደመው ሰው ጉራማይሌነት አንስቶ እስከ ተጋባዥ ካህናትና ሙዚቀኞች
ከዲጄው አጠገብ ጥቁር በነጭ የለበሱ ወንዶችና የሃበሻ ልብስ ያረጉ ሶስት ሴቶች ወደመድረኩ ይወጣሉ ፣ ዲጄው ፊቱን በአንድም በሌላም ምክንያት ይለጥጣል ።
ምግቡ ተበልቶና ተጠጥቶ ሙዚቃው እየደራ ቆይቶ ሰዉም ግማሹ ሲጨፍር ግማሹ እየተቀመጠ ከመንበሩ የተሰየመውን የዲቡ ደስትዬን ፈገግታ እንደ ምርቃት እየተቀበሉ ቆዩ ። ሳሚ ደላላው ወደነ ባርች ሄዶ ሰላም አላቸው ባርች ስለስራው ሊያናግረ ፈልጎ ነበር ደላላው ግን ፈጥኖ ሸሸ።
ባርች
እና የስራውን ጉዳይ ምን አረክልኝ?
ደላላው
እስቲ እናወራለን
ባርች
ያን ልጅ አስታወስከው?
ጃምቦ
የቱን
(ከታደሙት ሰዎች ውስጥ እየፈለገ)
ባርች
ያ ባንዱ ውስጥ ያለው?
የፊት አውራሪ ልጅ ነው
(ባንዱ እየተዘጋጁ ነበር ቦታ ቦታቸው እየያዙ)
የመሳሪያ ተጫዋቾቹ በመሉ ከአንዲት ሴት ድራመር በቀር ሁሉም ወንዶች ነበሩ ፣ ሁሉም ጥቁር ሱፍ ነጭ ሸሚዝ ጥቁር ከረባት አድርገው 'ኩል' ነበሩ ። ድምጻዊዎቹ ሶስት ሴቶች ነበሩ ። ሁለቱ አጃቢዎች ሲሆኑ አንዷ ደሞ ዋና ዘፋኝ ናት ። ሶስቱም የሃበሻ ልብስ አርገው ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል ።
ጃምቦ
ምንተስኖት ፊትአውራሪ?
ባርች
አው የሳቸው? ቀዩ?
ጃዝ ይጫወታል
ጃምቦ
ዘፋኝ ነው?
ባርች
ሙዚቀኛ
አይዘፍንም
ጃዝ ነው ሚጮተው ፣ ከአባቱ ጋር በጃዝ ምክንያት ተኳርፈው ነው ያረፉት? አሪፍ ውጤት አምጥቶ አዲስ አባ ዩኒቨርስቲ ደርሶት ምን መማር ትፈልጋለህ ሲሉት ሙዚቃ አላቸው ። ይህን ሲሰሙ ፊታውራሪ 'አዛምሪ በዘራችን የለም' ብለው እግሩን በዱላ ሰብረው ሰብረው ለቀቁት ፣ አሁንም ካስተዋልከው ትንሽ ያነክሳል? በጣም ትንሽ?
ጃምቦ
ምንድን ነው እሱ? ጃዝ?
ባርች
የዘፈን አይነት ነው ፣ ልክ እንደ ሬጌ ፣ ራፕ ምናምን
ጃምቦ
ገባኝ? የዘፈን አይነት ነው ? ግን ምኑ ነው ሚለየው ማለቴ ነው?
ባርች
እንዴት አድርጌ ላስረዳህ ዝም ብለህ ስማው ዝም ብለህ ስማው
ባንዱ ወደ የተባለውን ልጅ ሳክስፎን ይዞ የቆመውን ከተመለከቱ በኋላ ይጀምራሉ ፣ የሙላቱ አስጣጥቄን ኩሉን ማን ኳለሽ 7:48 ሙዚቃ ።
EXT. የሰርጉ አዳራሽ በር አካባቢ - የቀጠለ
ከጀርባ ሙዚቃው ይቀጥላል ። የአንድ ሰው ኮቴ ይታየናል ፣ ደረጃውን እየወጣ ነበር ።
INT. አዳራሽ ውስጥ - የቀጠለ
ታዳሚው ከየቦታቸው እየተነሱ መውረግረግ ጀምረዋል ፣ አብዛኞቹ ኩራት ያለው እስክስታ ነው ሚወርዱት ፣ ከሙዚቃው ምት ጋር ።
በበሩ በኩል ያ ኮቴ ይታያል ፣ እየጨፈረ ይመስላል ፣ አንዳንዶች ማጉረምረም ጀመሩ። የኮቴው ባለቤት ስንታየው ነው ። በበሩ በኩል በቀዩ ምንጣፍ አንድ ወዲህ አንድ ወዲያ እያለ ቀለል ያለ እስክስታ እየመታ ወደ መሃል ፈገግ እያለ በኩራት ይገባል ።
ጣይቱ
መጣላቹ ሰውያቹ?
ባርችና ጃምቦ በባንዱ ተመስጠው ነበር ። እየጨፈረ ወደውስጥ እየዘለቀ ያለውን ስንታየውን ሲመለከቱ ፊታቸውን ሸፍነው ጀርባቸውን ሰጡት። ቀድሞም አላያቸውም ።
እመቤት
ምንድን ነው? አረ አበዛቹት?
ስናታየው ወደመሃል ሰርስሮ ገባ ፣ ያዝ እንግዲህ ፣ ትከሻ ማለካካት ጀመረ ። ሴቷ ትዘፍናለች . . . ሰዉ ይቀበላሉ 'እኽ' 'እሸት የወይና እሸት የቡንኝ' . . . ስንታየውን እያጫፈሩት
ብዙም ሳይቆይ ስንታየው ብር ከኪሱ እያወጣ ወደ ላይ መበተን ጀመረ ።
ባርች
(ለሃና)
ወይኔ . . . ሂጂና ብሩን አንሺ ከመሬት ልቀሚው
ጣይቱ
እረ ተዋት
ጃምቦ
እረ ትልቀመው?
ሃና እየሮጠች ትሄዳለች ፣ ሌሎች ህጻናት ግን ቀድመዋት እየሮጡ ነበር ። በሰዉ እግር እየሾለኩ የሚዘበውን ብር መልቀም ጀመሩ ።
ብሩ ይዘንባል ፣ ወደ ላይ ይበተናል ። ይህን ድርጊት ሙሽሮች ሳያዩ ማለፍ አልቻሉም ። ሩት ስንታየው መሆኑን ስታይ ስሜቷ ተረበሸ ። እምባዋ ቀረሩ ። ዲቢ ደስታዬ በጎረነነ ድምጹ ።
ዲቢ ደስታዬ
እሱ ነው እንዴ?
ሩት ራሷን ትነቀንቃለች ።
አብረው ሲጨፍሩ የነበሩት ስናታየው መሆኑን ሲያስተውሉ ሙት እንዳየ ሰው ዝም ብለው ቆሙ።
ዲቡ ደስትዬ አንድ ሰው በእጁ አመልክቶ ያስጠራል ። ሰውየው ጆሮውን ወደ ዲቡ አስጠግቶ አጎነበሰ ። ወደ ስንታየው ዞሮ ተመለከተ ፣ ስንታየው እያያቸው አልነበረም ። ሰውየው ወረደና ከሌሎች ወጠምሾች ጋር ወደ ጭፈራው መሃል ገቡ ፣ የሚጨፍረውን ስንታየውን በክንዱ ሲይዙት ሳይታገል በጭፈራ አድርጎ አስለቀቃቸው ። ይህን ሲያዩ ባርችና ጃምቦ ከመቀመጫቸው ተነሱ
ጣይቱ
ምን ልትሆ . . .
አልሰማትም ፣ በርጋታ ግር ግር ላለመፍጠር ወደ ጭፈራው መሃል ገብተው ። ክንዱን ይዘው ሊያስወጡት ከነበሩት ሰዎች መሃል ገቡና ገላገሉ ። ሳሚ ደላላውም በቅርብ ርቀት ነበር ። ሰዉ ጭፈራውን አቋረጠ ፣ ባንዱም ሙዚቃውን አቋርጦ ተመለከተ ።
ስንታየው
'እሸት የወይና እሸት የቡንኝ'? ጨፍሩ ። እሰይ! እሰይ!
cut to:
EXT. አዳራሹ በር - የቀጠለ
ባርችና ጃምቦ ይዘውት ወጡ ።
ወጠምሻዎቹ የተወሰነ ተከትለዋቸው ነበር ። ለመመልሰ እንዳላሰቡ ሲያዩ ወጠምሾቹ ተመልሰው ወደውስጥ ይገባሉ ።
ባርች
ምንድን ነው!? ምንማረግህ ነው!?
ስንታየው
(ይስቃል)
እናንተን ልጠይቃቹ ምን እያረጋቹ ነው?
እንደምትመጡ አላወኩም ነበር?
ጃምቦ
(አልተደማመጡም)
ሰው በመጀመሪያ ደሞዙ ስንት ነገር ያረጋል? አስራት በኩራት ያወጣል ፣ ለእናቱ አስፔዛ ይገዛል ስንት ነገር ያረጋል አንተ ዝም ብለህ አየር ላይ ትበትነዋለህ? ለምንም? ለምንም?
ስንታየው
'ለምንም'? ጆሮዬ ነው መሰለኝ ለ'ምንም' ነው ያለከው? ልክ ነህ የኔ ህልም የኔ ህይወት 'ምንም' ነው።
ጃምቦ
እንደዛ አላልኩም?
ባርች
ቦቸራ ራስህን አረጋጋ ማን እንደዛ ያለ የለም?
ስንታየው
(እንደ እብድ እየፈገገ አይኑ እምባ አቅርሮ)
አይ አይ አይ ልክ ናቹ 'ምንም' ነው። ማን ህይወት እንዳለው ታቃለህ? ማን ባለህልም እንደሆነ ልንገርህ? ዲቡ ደስትዬ? ለምን መሰለህ ? ገንዘብ ፈለገ ገንዘብ አገኘ ፣ ቤት ፈለግ ቤት አገኘ ፣ ሚስት ፈለገ የምትንከባከበው ሚስት ይኸው ዛሬ ሚስት አገኘ። ሚስቱ ፍቅረኛ እንደነብራት ያውቃል?
ይጠብቃል።
ባርች
ቦቼ?
ስንታየው
በደምብ ነው ሚያውቀው እንዴት አያውቅም?!
ጃምቦ
እርሳ. . .
ስንታየው
የሰው ፍቅረኛ እጮኛ መንጠቅ ነውር እንደሆነ አያቅም?
(መልስ የለም)
ያቃል።
ግድ ይሰጠዋል?
አይሰጠውም። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? የዛ የውዳቂ ፍቅረኛዋ ህልም 'ምንም ስለሆነ! ግን እናንተ እየበላቹ እየጨፈራቹ ስለነበር ምን ታውቃላቹ!
ይሄኔ ሃና እየሮጠች ከጀርባቸው ትመጣለች። ያፈሰችውን ገንዘብ በሙሉ በሁለቱም እጆቿ ይዛ።
ሁሉም ዝቅ ብለው ያያቷል ወደ ስንታየው የተዘረጋውን እጆቿን እንደሰቀለች ።
ስንታየው ሲመለከታት ራሱን በሃዘን ይነቀንቃል ፣ በደረጃው ጀርባውን ሰጥቷቸው ይወርዳል ።
ስንታየው
'ማንም' . . . 'ምንም'
ከደረጃው መውጫ ጋር የቆመውን ነጭ የሙሽሮችና የሚዜዎች መኪና ጋር ሲደርስ እቃ እንደጥለ ሰው ዝቅ አለ ። ከቅርብ ርቀት ቆመው የነበሩት የመኪናው ሹፌው ወይም ጥበቃ ያዩትና
ጥበቃው
አንተ!? ምን እያረክ ነው?!
ያዘው ያዘው !?
ጎማውን አየር እንዲሰርቅ እያረገው ነበር ። እንደተነቃበት ሲያውቅ እየሮጠ ያመልጣል ሰውየው ይከተሉታል ። ይሄንን ትእይንት ከደረጃው መውረጃ ጋር ቆመው የሚመለከቱ ጃምቦና ቦቸራ ይቀራሉ ። ሃናም አብራቸው ።
INT. አዳራሹ - የቀጠለ
ከተፈጠረው ነገር ጀርባ የድርጊቱንም ከዋኝ ማንነት በማወቃቸው አብዛኛ ሰዉ ተደናግጦ ነበር ። ታዛቢዎቹ እንደለመዱት እጃቸውን አፋቸው ላይ ጭረው በነጠላው ሸፍነው ማንሾካሾክ ከጀምሩ ቆይተዋል ።
ዲቡ ደስትዬ ከመንበሩ ተሰይሞ ከተሰደሩት ጥርሶች መሃከል አንደኛውን የወርቁን ብልጭ አድርጎ
ወፍራም እጁን እንደጃንሆይ ከፍ አድርጎ ከፍ አድርጎ ስርዓቱ እንዲቀጥል ያመለክታል ፣ ባንዱ ይቀጥላል ።
ሃና(V.O.)
በተፈጠረው ነገር ላይ ከነበረው እውነታ በተጨማሪ ሰዎች ተረታቸውን እስጨምሩ እስከምሽት ብቻ መጠበቅ ነበር የነበረባቸው ።
INT. አንዷ ታዳሚ/ታዛቢ ቤት - ማታ
የሃበሻ ልብሷን እንዳደረገች ፣ ከቤተሰቧ ጋር ተቀምጣ ራት እየተቋደሰች ስለተፈጠረው ነገር ትናገራለች ፣ ድምጿ ባይሰማንም ። አንድ ወንድ ጎረምሳ ልጅ እና እህቷ ትሁን ልጇ ማትለይ ሴት።
INT.አዳራሽ - የቀጠለ
ስንታየው ብሩን ከበተነ በኋላ እያለቀሰ ፣ ደረቱን እየደቃ ለቅሶ ላይ እንዳለ ሰው ሆኖ እናየዋለን። ሰዉ ሁሉ ዙሪያውን ከቦ አፉን ይዞ ማየት ከጀምረ ቆይቶ ።
ሃና(V.O.)
አንዷ 'ስንታየው ድንኳን ሰብሮ ብሩን ዘርቶ እምባውን በሰዉ ሁሉ ፊት እናቱ እንደሞተችበት ዱብ ዱብ አደረገው' በሚል ተረት ጀመረችው። ገረምሳው ልጇ የላም በረት ብሎ ሲቀበላት
EXT. አንድ ቤት ስር - ጥዋት
ያ ጎረምሳ ከሌላ ጎረምሳ ጋር አንድ ላይ ቁጭ ብለው እያውሩ ነው ፣ የመጀመሪያው እየተረከ ሌላኛው እያደመጠ ።
INT. አዳራሹ - የቀጠለ
ስንታየው ብሩን ከበተነ ካለቀሰ በኋላ ልብሱን እንዳበደ ሰው መቀዳደ ይጀምራል ፣ ተምበርክኮ እየጮሐ ፣ ጩኸቱ ጆሯችንን ያደማዋል ።
ሃና(V.O.)
መልሶ ተረቱ ላይ የራሱን ተረቶች ጨምሮ ለጓደኛው ሲተርከው ይህን የመሰለ ቅርጽ ያዘ ።
ext. ድድ ማስጫው - አመሻሽ
ያኛው ልጅ ደሞ ከታሪኩ ባለቤት ጋር በመሆን አብረዋቸው ድድ ለሚያሰጡ ልጆች ይተርካሉ ።
INT. አዳራሹ - የቀጠለ
ስንታየው ብሩን ከበተነ ካለቀሰ ልብሱን ከቀደደ በኋላ ወደ ዲቡ ደስታዬ ታስሮ እንደተፈታ አውሬ ይንደረደራል ፣ ግብ ግብ ። ከዲቡ ደስታዬ ጋር እጅ ለእጅ ይያያዛሉ ፣ ዲቡ ደስታዬ በወፍራም እጁ በጥፊ በጥፊ በጥፊ ይለጣጥፈዋል ።
ሃና(V.O.)
በመጨረሻም በጎረምሶቹ መሃል የሚነገረው ታሪክ ይሄ ሆነ ፣ ልክ እንደአዋቂዎቹ ሁሉ ።
EXT. መንገድ ላይ - አመሻሽ
በአንድ ፍሬም ስንታየው ሩትን አስቁሞ ካናገረበት ቦታ አንገቱን አቀርቅሮ ያልፋል ።
ሃና(V.O.)
ታዲያ ከዛ ጊዜ ወዲያ በሰፈራችን ውስጥ ስንታየውን አእምሮውን እንደሳተ እንጂ በሙሉ ጤናው ላይ እንዳለ አድርጎ የሚያየው ሰው ጠፋ ። እሱ 'ከሁሉት ከሶስት ወር በኋላ ይሞታል' እንዳለው የዲቡ ደስታዬን ሞት ሲጠባበቅ ፣ ሰዉ ደሞ ስንታየው በረኪና ጠጥቶ መሞቱ አይቀርም ይሉ ጀመር ።
ተመልሶ ይመጣል ጥዋቱን ። አንዳንድ መንገዳቸው የገጠመ እናቶች ፣ ዘምቢላቸውን ይዘው ከጀርባው እየተንሾኳሸኩበት ይከተሉታል።
ሃና(V.O.)
የሰፈራችንም የሙዚቃ ባንድ ከድድ ማስጫቸው ተቀምጠው በወጣ በገባ ቁጥር ለህይወቱ የሚሆኑ የማጀምቢያ ሙዚቃዎችን ይጭወቱለት ጀመር ።
ስንታየው በፍሬሙ ድጋሜ ይገባል ። አሁን የትየሌለ እናቶችና ሰዎች እየተንሾካሾኩ ይከተሉታል ፣ መንገዳቸው ገጥሞ እንዳልሆነ ግልጽ ነው ። እሱ አንገቱን ቀና ሳያደርግ ሳያስተውላቸው ይጓዛል።
ext. የድድ ማስጫው ጋር - ጥዋት
የሰፈሩ የሙዝቃ ባንድ ከቦታቸው ተሰይመዋል ። ከጎናቸው ከነበረው መንገድ መሃል ቆሞ ወደነበረ ጓደኛቸው አይናቸው ተተክሏል ሁሉም ። ልጁ ደሞ ከመንገዱ ላይ ። ትንሽ
ጎረምሳ 1
(እያንሾካሾከ)
መጣ?
ጎረምሳ 2
(በእጁ ጠጠር እየወረወረበት)
አተ!?
ጠባቂው
እ?
ብዙም ሳይቆይ ጠባቂው እየሮጠ ተመለሰ ወደልጆቹ ፣ ከጎናቸው ቆመ ።
ጎረምሶቹ
መጣ? መጣ? መጥቶ ነው?
ጠባቂው
አው አው አው ጀምሩ ጀምሩ
ከመንገዱ ስንታየው እየመጣ ነው ።
ባንዱ ዘፈኑን ይጀምራል። የሰይፉ ዮሃንስ 'ኤቦ ላላ' ግጥሙ እንደተለመደው ከራሳቸው ነው።
ጎረምሶቹ
ላላ ኤቦ ላላ ኤቦ ላ
ላላ ኤቦ ላላ ኤቦ ላ
ላላ ኤቦ ላላ ኤቦ ላ
ላላ ኤቦ ላላ ኤቦ ላ
ኤባ
አይሆነኝም ብላ
ስለሌለው መላ
ስላገኘች ሌላ
መቅሰስ የሚያበላ
የሚያጠጣ ጠላ
ማያነሳ ዱላ
ሄደች ሃገር ጥላ
ጎረምሶቹ
እሂኢ . . . አሂኢ . . . እሪሪ
ያዝ . . . ሰይ! ኤቦ ላ!
ጉራገኛውን ሲያስነኩት ስንታየው በአጠገባቸው እንደለመደው ዞርም ብሎ ሳያያቸው መንገዱን ያቀናል ። መጨፈራቸውን መዝፈናቸውን ይቀጥላሉ ።
INT. መስራቤት የነስንታየው ቢሮ - የቀጠለ
ስንታየው ከመግባቱ ቦርሳውን ከወምበሩ ላይ እንዳስቀመጠ ፣ ከደስኩ ላይ ወረቀቶች ያገኛል ።
አንስቶ ያያቸዋል ። የህንጻ ካርታዎች ሰነዶች ነበሩ ። እየገለጠ ፊቱን አኮማትሮ ከተመለከታቸው በኋላ ከጎኑ ከነበረው ዴስክ ከተቀመጠችው ጠይም ልጅ አቀና ወረቀቶቹን እንደያዘ ። ልጅቷ የባንክ ደምብ በመሆኑ ሙሉ ሱፍ አድርጋለች ያለከረባት ፣ ከላፕቶፗ ላይ ኢር ፎኑን ሰክታ ታደምጣለች።
ስንታየው
ይቅርታ . . . እንዴት አደርሽ
ልጅቷ
ሰላም ነው ?
ስናታየው
እነዚህ ያንቺ ናቸው መሰለኝ?
ልጅቷ
እስቲ
ከዴስኩ አልፎ ወረቀቱን ሰጥቷት ሲመለስ ።
ልጅቷ
አይ የኔ አደልም ፣ የመጨረሻው ፔጅ ላይ ስምህ አለበት ካላየኸው ?
ግራ በመጋባት ወደ ልጅቷ ተጉዞ የዘረጋችውን ወረቀት ይቀበላታል ፣ በድጋሜ እያገላበጠ ተመልክቶት
ስንታየው
የህንጻ ካርታ ምን ላረገው ነው?
ልጅቷ
ግምት
INT. ቢሮ ውስጥ - የቀጠለ
ሰፋ ካለው ቢሮ ፣ ሰፋ ካለው መስታወት ስር ፣ ሰፋ ካለው ዴስክ ላይ ፣ከትከሻው ሰፋና ሾል ያለ ኮት ያደረገችው ማናጀር ተቀምጣላች ። በሯ ይንኳኳል ።
ማናጀሯ
ይግቡ
ስንታየው ወደውስጥ ገባ ይልና
ስንታየው
ላናግርሽ ፈልጌ ነበር
ማናጀሯ
ግባ ግባ ስ . . . ስንታየው?
ወደውስጥ ገብቶ ፣ ወደሷ አቅንቶ
ስንታየው
አው
ማናጀሯ
ተቀመጥ ተቀመጥ?
ስንትየው
ችግር የለውም
ማናጀሯ
ግድ የለም ተቀመጥ
ስንታየው የግዱን ሆኖበት ይቀመጣል ።
ማናጀሯ
እንኳን ደስ አለህ?
ስንታየው
ለምኑ?
ማናጀሯ
ከዛ ሁሉ ሰው ተወዳድሮ አንድ ብቻ ሆኖ መውጣት ቀላል ነገር ነው መሰለኝ ላንተ
ስናታየው
እ . . . አይ ትንሽ ቆየት ስላለ ነው።
ማናጀሯ
እሺ ምን ልርዳህ?
ስንታየው ወረቀቱን ያቀብላታል። ከመቀመጫው ብድግ ብሎ ።
ስንታየው
ለኔ የተሰጠኝ ስራ ነው መሰለኝ?
ማናጀሯ መጽሯን ወሸቅ ወሸቅ እያረገች ወረቀቶቹን እያገላበጠች ትመለከታለች ። ስታበቃ መነጽሯን ዝቅ አድርጋ ፣ ወረቀቱን በሌላኛው እጇ እንደያዘች
ማናጀሯ
ምን ሆነ?
ስንታየው
የቤት ካርታዎች ናቸው።
ማናጀሯ
አየኋቸው ።
ስንታየው
ምን እንደማረጋቸው አልገባኝም?
ማናጀሯ
(ወረቀቶቹን ከድና)
ትገምታቸዋለኽ ። ቦታው ላይ ትሄድና ህንጻዎቹ ወይም አንተ እንዳልከው ቤቶቹ በምን አይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ ታጠናለኽ ፣ ያን ካደረክ በኋላ ስንት ሊሸጡ እንደሚችሉ ትገምታለህ ፣ ቀላል ነው።
ስንታየው
ግን ገማች አደለሁም
ማናጀሯ
ሲቪህን አይተነዋል ፣ በጣም የሚያስደንቅ ውጤት ነው ያለህ ይሄን 'ሲሊ' ነገር መማር ይከብድሃል ብዬ አላስብም።
ስንታየው
ያ ሳይሆን እኔ ኢንጅነሪንግ ነው የተማርኩት
ማናጀሯ
ሲቪል አደል?
ስንታየው
ኤሌክትሮ መካኒካል
ማናጀሯ
አው ኤሌክትሮ ፣ ሰሞኑን ስራ በዝቶብኛል ።
ዝም ።
ስንታየው
እና . . . ስለህንጻዎች የማውቀው ነገር የለም?
ማናጀሯ
ይገባኛል ፣ ስራው እንደምታስበው የተወሳሰበ አደለም ነገሮችን እስክትለምዳቸው ድረስ ከነ ስዩም ጋር ትሰራለህ እነሱ ያለማምዱሃል
ስንትየው
አው ያ ብቻ ሳይሆን ግን . . . ስራውን ብዙም የምወደው አይመስለኝም
ማናጀሯ
ምን ጠብቀህ ነበር ሮቦት እሰራለው ብለህ ነበር ? የተቀጠርከው ባንክ ውስጥ ነው ፣ ቢበዛ ባንተ ፊልድ ሊሆን የሚችል ስራ ያለው የተበላሸ ኤቴኤም ማስተካከል ነው ፣ ያን ማረግ ደሞ አንችልም ። ቦታ የለም ። ሁሉ ቦታ ለጊዜው በታታሪ ሰራተኞች ተይዟል ። ክፍት ቦታ እስክናገኝ ድረስ የምናገኝ ባይመስለኝም የተሰጠህን ስራ እንድትሰራ እመክርሃለው ።
ዝም ።
ማናጀሯ
ይቅርታ እንደሱ ለምንድን ነው ምታየኝ?
ስንታየው
እንዴት?
ማናጀሯ
የውልኽ የኔ ወንድም ስራውን ማትፈልገው ከሆነ በፈልከው ሰዓት መልቀቅ ትችላለህ ፣ እንዳየኸው ብዙ ሰው አንተ ያገኘኸውን እድል ማግኘት ይመኛል ። ግን የ'ወደድከውን' ነገር ለመስራት ከፈልክ ናሳ ወይም አፕል አፕላይ ብታረግ ጥሩ ነው ፣ ያን እስክታደርግ ድረስ ግን የተሰጠኽን ስራ ሳትታክት ተወጣ።
ወረቀቱን መልሳ ዘረጋችለት ። ስንታየው አማራጭ የለውም ተቀበላትና እያዘገመ ከቢሮው መውጣት ጀመረ ። የማናጀሯ የቢሮ ስልክ ይጠራል ፣ ታነሳዋለች ።
ማናጀሯ
መሲ? . . . በጣም ጥሩ እ የሰውየውን ቀጠሮ ሰርዥው ፣ ወይ ከሰዓት በዪው ። ጥሩ ፣ በጣም ጥሩ
እና ደሞ ስዩምን ከስንታየው ጋር ሳይት እንዲሄድ ንገሪው፣ አዲሱ ልጅ . . .
ስንታየው ክፍሉን ለቆ ወጣ ።
INT. የነስንታየው ቢሮ - የቀጠለ
ስንታየው እያዘገመ ወደወምበሩ አቅንቶ ከወምበሩ ተቀምጦ ወረቀቱን እያገላበጠ ባለበት ፣ ወዲያው ከአንዱ ጥግ አንድ 'ጉልቤ' የሚመስል ወጣት ቆዳ ጫማውን እያማታ ወደሱ መጣን ከፊቱ ቆመ
ስዩም
ስንታየው?
ስንታየው
አው
ስዩም
ስዩም እባላለው . . . እንኳን ደስ አለህ ለማለት እድሉን አላገኘሁም ነበር እንኳን ደስ አለህ?
ስንታየው
አመሰግናለው
ስዩም
ያለውን ሁኔታ እንዳሳይህ ታዝዤ ነበር . . . ልቀበልህ
ወደ ወረቀቱ እየጠቆመ። ወረቀቱን ገረፍ ገረፍ ካደረገ ወዲያ
ስዩም
እንንቀሳቀስ
(መንገዱን ብቻውን እየጀመረ)
ስናታየው ከጀርባው ጥሎት የሚሄደውን ስዩምን እየተከተለ ።
INT. መኪና ውስጥ - የቀጠለ
መኪናው ነጭ ለአንድ ኩሩ ዘር ናት ፣ የመስሪያ ቤት መኪና ። ከውስጥ 4 ሰዎች አሉ ። ስንታየውና ስዩም ከጀርባ አንዲት ሴት እና ሹፌሩ ከፊት ተቀምጠው ይታያሉ ።
ወጣቷና ሹፌሩ ሞቅ ያለ ወሬ ይዘዋል ። ስንታየው ወረቀቱን እያጠናው ነው ።
ስንታየው
በአንድ ወለል 4 ቤቶች አሉ ?
አንዱ ቤት 7 ክፍል አለው ?
ባለ 5 ፎቅ ህንጻ ነው ?
ስዩም
8 አንድ ረስተሃል
እዚ ጋ ። እንደመጀምሪያ ግን በጣም አሪፍ ነው ። ሰዎች ልጁ አስተማሪ አያስፈልገውም ዝም ብለን ነው ምንደክመው ? አተ ፣ ማንን እንደጫንክ ታውቀዋልህ
ሹፌሩ
ማን ልበል ወንድሜ
ስንታየው
ስንታየው
ሹፌሩ
ስንታየውን ነው የጫንኩት
ስዩም
ስራውን ከስንት ሰው እጅ እንደፈልቀቀ ብታውቅ ተነስተህ እጁን ትስም ነበር ።
ሹፌሩ
እጆቹ ንጹህ ከሆኑ ብቻ ነው ምስማቸው እ? ብር የቆጠረ እጅ አይሳምም። ስንታየው?
ዝም
ሹፌሩ
አንተን ማለቴ አደለም? ያው ያለንበትን ሁኔታ ታውቀዋልህ ስራ ማግኘት እንዴት ከባድ እንደሆነ እና ከዛ ሁሉ ሰው አንድ ብቻ ሰው ወጣ ሲባል ያጠራጥራል
ዝም ። ለመመለስ አልጨነቀውም ፣ ያሰበውን ያስብ ።
ስዩም
አሁን ዋናው ነገር እሱ አደለም ማነህ ጓድ ሹፌር ቁም ነገር ልንነጋገር ስለሆነ ድምጽህን ቀንስ ።
ሹፌሩ
የሚነዳ ሰው ማስከፋት ጥሩ ነው ትላለህ?
ስዩም
ሽ!!!!!!!!
እሺ ፣ አሁን ህንጻው ምን ያለ እንደሆነ በምናብህ ሳለው 5 ፎቅ ህንጻ ባዶ ህንጻ
CUT TO:
INT. ህንጻው ውስጥ - የቀጠለ
እነ ስንታየው ስዩምና ልጅቷ በባዶው ህንጻ እየተዘዋወሩ ይገመግማሉ ። ስንታየው ምኑን ማየት እንዳለበት ስላላወቀ እዚህም እዢያም አይኑን ያንከራትታል።
ስዩም(V.O.)
በየወለሉ 7 ቤት አለው ። በየቤቱ ደሞ 8 ክፍል አለው።
ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ብለን እናስብና። ስንት ያወጣል ብለህ ታስባለህ?
ስንታየው ወደ ባልኮኒው ወጥቶ ቁልቁል እየተመለከተ ፣ እየተመኘ ስዩም ወደሱ ይመጣል ።
ስዩም
ስንት አልከው?
ስንታየው
7 ሚሊየን?
ስዩም ፈገግ ብሎ እጁን ከፍ ያደርገዋል ።
ስንታየው
10 ሚሊየን
ከፍ
ስንታየው
20?
ራሱን ይነቀንቃል ምናልባት በሚል።
ስንታየው
27?
ዝቅ
ስንትየው
25?
24?
24.5?
ስዩም በእጁ ልክነቱን ያመለክተዋል።
INT. መኪና ውስጥ - የቀጠለ
ስንታየው ላይ ይስቁበታል ፣ ስንታየው ፈገግ ብሎ ፊቱን ወደ መስኮቱ ይመልስና ወደ ሃሳቡ ይመለሳል ።
ስዩም(O.S.)
ከዚ ሁሉ የኛ ደሞዝ እንደ ሳንቲም ነው
ሹፌሩ(O.S.)
ነው እንዴ?
EXT. ሰፈራቸው ውስጥ - አመሻሽ
ሰንታየው ቦርሳውን እንዳነገተ ከአንድ የሃብታም ቤተ ፊት ለፊት በቅርብ ርቀት ቆሞ ወደ ሰገነቱ ሽቅብ ይመለከታል ። አንደ ነገር በመጠባበቀ ላይ ያለ ይመሰል ።
ቤቱ በዙሪያው ከነበሩት ሌሎች ደንክ ቆርቆሮዎች እና ጭቃዎች ከከተሙት ለቅሶ በመለየት ወዙና ነጭ ቅቡን እንደተቀባ ሰርገኛ መስሏል።
ሰረገኛ ከሚመስለው ቤት ሰገነት ሰረገኛዋ ሩት ብቅ ትላለች። ከሰገነቱዋ ላይ ቆማ የንጉሱን ገዛት እነደምታይ ልዕልት ነጭ ቀሚስ ለብሳ ቁልቁል ግዛቱዋን ትቃኛለች። በኩራት በሰላም ። ከግዛቷ አንድ እረኛ አንገቱን ስቅሎ በተማጽኖና በምኞት ይመለከታታል ። ሰንታየው።
ልዕልቲቱ እረኛውን ስታይ ፊቷ ላይ የነበረው ደስታ ይደበዝዛል ትኮሳተራለች። ሰላሟ ወደ ብስጭት ይለወጣል ። ብዙም ሳትቆይ ፣ ወደ ቤቷ ተመልሳ ትገባለች ፣ የሰገነቱን መጋረጃ ገልጣ።
ብቸኛው እረኛ ብቸኛውን ቤት ሲያይ ቆይቶ እሱም እንዳዘነ ይሄዳል።
ሃና(V.O.)
አንዳንድ ሰዎች ነጻ ፈቃድ የሚባል ነገር የለም ብለው ያምናሉ ። ሰው የተጻፈለትን እድሜ ይቆጥራል እንጂ ከራሱ ፣ ለራሱ ፣ በራሱ ፈቃድ የሚጨምረው ነገር የለም ይላሉ ። ስንታየውም ባጋጠሙት አሳዛኝ የህወት አጋጢሚዎች በመነሳት እንዲዛ ያለ ድምድሜ ላይ ሊደርስ እያኮበከበ ስለሆነ ለጊዜው ስንታየውን እዚጋር እንተወውና ባርችን እንከተል ። ምክንያቱም ተስፋ የቆረጠን ሰው መከተል ጥሩ ስላልሆነ።
ስንታየው አቀርቅሮ በሚሄድበት መንገድ ላይ ስንከተለው ቆይተን በድንገት ወደ ጎን እንጥጠፋለን። ወደ መጠጥ ቤቱ ።
INT. መጠጥ ቤቱ - የቀጠለ
ባርችና ሳሚ ደላላው እንዲሁም አንድ እንግዳ እድሜ የጠገቡ ሽማግሌ ከወትሮውም በተለየ መልኩ ጩኸትና ካካታ በበዛበት ቤት ውስጥ ከአንድ ጥግ ተቀምጠዋል ። ባርችና ሳሚ ደላላው ከአንድ ወገን ሽማግሌው ከሌላ ወገን ። ሽማግሌው ኮስተር ብለው ባርችን ይመለከታሉ፣ የተቀደደ ቅንድባቸውን አኮሳትረው ። ዝም ።
ሽማግሌው ትስሽ ቆይተው ከኪሳቸው የመኪና ቁልፍ ያወጡና ከፊቱ ያንጠለጥሉታል ። ባርች እጁን ዘርግቶ ሊቀበላቸው ይላል። እሳቸው ግን አይሰጡትም ።
ሽማግሌው
አልማዝ ምንህ ናት?!
ከሽማግሌው ጀርባ የነበረችው እመቤት ፣ አልማዝ ።
ባርች
ምን?
ሽማግሌው
የምሰማው ነገር ምንድን ነው?
ባርች
(የዘረጋውን እጁን እየመለሰ)
ምን ሰሙ ጋሼ?
ሽማግሌው
(ሽማግሌው ቁልፉን ከወምበሩ አስቀምጠው ቀጠሉ)
እዚ ጋር ያለው ሰውዬ (ወደ ሳሚ ደላላው እየጠቆሙ)
የወንድሜ ልጅ የከንፈር ወዳጅ ስራ እንደሚፈልግና ሹፌር እንደሆነ ነገረኝ
ባርች
እንደኔ፣ እኔም ሹፌር ነኝ።
ሽማግሌው
አዳምጥ . . . የወንድሜ ልጅ አልማዝ ፣ የዚህ ቤት ባለቤት ጓደኛ እንደያዘች ሳትነግረኝ ከማላውቀው ሰው ያን ስሰማ ውስጤ ቢያዝንም እድሜዋም እየሄደ ስለሆነ እንደዚ አይነት ዜና በመስማቴ እጅግ ደስተኛ ሆኜ እንደነበር አልዋሽም ። ይገባቿል እኔና ወንድሜ ለቤታችን ብቸኛ ልጆች ነን እንደእድል ሆኖ እኔ ምንም ልጆች የሉኝም ፣ ወንድሜ ደሞ ከወለደ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ህይወቱ አለፈ ነፍሱን ይማረውና ?
(ነፍሱን ይማር)
እና አልማዜን እንደአባት ሆኜ ያሳደኳት እኔ ነኝ? ምንም እንኳ እሷ ነገሮችን ለመንገር ባትቀርበኝም ።
ባርች ወደ ባልኮኒው ይመልከታል ፣ እመቤቷ(አልማዝ) ወደነሱ እያየች ነበር ። እመቤት በእጆቿ ትስመዋለች ። ባርች ፈገግ ብሎ ይመለሳል ወደ አጎቱ ።
ሽማግሌው
ዜናውን ስሰማ ደስተኛ ነበርኩ ፣ የኔን ቤተሰብ ስታስተዳድር የቆየችውን ታክሲ ለልጄ ጓደኛ ለመስጠት ምንም አልሳሳም ፣ ነገር ግን ለእንዳንተ አይነት ሰው ነው የምሰጠው ብዬ አላሰብኩም ነበር ።
ባርች
አልገባኝም?
ሽማግሌው
ምኑ ነው ያልገባህ?
ባርች
'እንዳንተ ያለ ሰው' ሲሉ አልገባኝም?
ሽማግሌው
'እንዳንተ ያለ ሰው' ስልማ ፣ እናቶቹ ሊሆኑ ከሚችሉ ሴቶች ጋር እየተዳራ ገንዘብ የሚቀበልን ሴሰኛ ፣ መንደርተኛው ሁሉ ጅብ እያለ የሚጠራውን ክብረ ቢስ ሰው አልጠበኩም ማለቴ ነው?
አሁንስ ገባህ?
ባርች
አልማዝ አሮጊት አደልችም
ሽማግሌው
ላትሆን ትችላለች ፣ ግን ደግም እኩያህም አደለችም ።
ባርች
በ3ት ባራት አመት ብንለያየ ነው ጋሼ? ሰው ስለሚያወራው ተረት ደግሞ የለመድኩት ነገር ነው
ሽማግሌው
ስለተላመድከው እንኳን ደስ አለህ። ውዳቂ!
ዝም።
ሽማግሌው
በዚህ ጠርሙስ አናትህን የማልልህ ቆራቢ ስለሆንኩ ነው።
እና በግልጽ አማርኛ እነግርሃለው ከልጄ ራቅ . . . ያው እኔ ምንም አላረግህም ፣ ከላይ ያለው ግን ይፋረድሃል።
ቁልፉን እያቃጨለ ይነሳና ፣ ቀበቶውን እያስተካከለ ወደ አልማዝ ዞሮ 'ቀዝቃዛ ሰላምታ' ሰጥቷት ይወጣል ።
ባርች ፊቱን ያብስና ወደ ሳሚ አዙሮ ፣
ባርች
ካልጠፋ ሰው እንዴት እሳቸውን ታመጣለህ?
ሳሚ እጁን ግራ በመጋባር አንስቶ ያየዋል።
ሳሚ
እንዲህ አይነት ሰው እንደሆነ በምን አውቃለው? ቆራቢ እንደሆነ ነው ማውቀው ?
ምን አይነት ሰው ናቸው?
ወደ እመቤት ተመለከት ፣ አሁንም እያየችው ነበር ። በጭንቀት ሲያያት ጊዜ ፣ እጇን 'ተወው ባክህ?' በሚል አንስታ ጣለችው ። ባርች ፈገግ አለ።
ዝም ።
ባርች
ሰዉ ጅብ ነው እንዴ ሚለኝ?
ሳሚ
አሁን እሱ አደለም ዋናው ነገር ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ የምትገባበትን መንገድ ነው ምንፈልገው . . .
ሳሚ ርዕሱን ቀይሮ ሲያወራ ድምጹ በዝግታ እየደበዘዘ ይመጣል።
ሳሚ(O.S.)
ወደነ ቾምቤ ሰፈር አይጠፋም ታክሲ . . . እንጠይቃለን
እይታችንም በበሩ በኩል ወዳለው መንገድ ይወሰናል ። ቤቱ ባዶ ይሆናል ይነጋል ።
CUT TO:
ext. አንድ መንደር - ቀን
ሃና(V.O.)
ከሁለት ሳምንት በኋላ ሳሚ ደላላው ቃል በገባለት መሰረት ለባርች የተባለውን ታክሲ ለባርች አስረከበው ።
ባርችና ሳሚ ከአንድ ሽማግሌ የሚኪና ቁልፍ ይቀበላሉ ። ሽማግሌው ገሸሽ ይሉና ከጀርባ የነበረውን ታክሲ ያሳዩዋቸዋል።
ሃና(V.O.)
ስራ አጥነት በነገሰበት ከተማ ባርች የሚያገኘው ትርፍ ከረዳቱ ጋርና ከመኪናው ባለቤት ጋር ለመካፈል የነበረበትን ቅድመ ሁኔታ በደስታ ነበር የተቀበለው ።
CUT TO:
INT. መኪናው ውስጥ - ቀን
በየቦታው እየቆመና የሚገባውን እያስገባ የሚወርደውን እያስወረደ መንገዱን ይቀጥላል ።
ሃና(V.O.)
ቢሆንም ግን ከእያንዳዱ ግድግዳ ጀርባ ከያናንዱ ጣራ ስር የቡና ቁርስ ሆኖ 'ጅቡ' እየተባለ እንደሚጠራ ከማሰብና በዛም ከማዘን ራሱን ሊገታ አልቻለም ።
CUT TO:
INT. የአልማዝ ቤት ሳሎን - ምሽት
ባርችና እመቤት ከአንድ ሶፋ ተቀምጠው ከአንድ ሰሃን ራታቸውን እየተመገቡ ፣ እናያለን ። ባርች ያዘነላት ይመስል አየት ያረጋታል ፣ ደስተኛ ባልሆነው ፊቱ ። እሷ ደሞ ጠቅለል አድርጋ ታጎርሰዋለች ።
ልብሱን ከሶፋው አንስታ ወደ መዘፍዘፊያው ስትጨምረው እናያለን ልታጥበው ።
ሃና(V.O.)
ምንም እንኳ ያ ባህሪው የተደበቀ ባይሆንም አልማዝ ለባርች የነበራትን ፍቅር እንዲቀንስ የሚያደርገው አልነበረም።
ይልቁንም ባርች ጓዙን ጠቅልሎ እንዲመጣና አብሯት እንዲኖር አብዝታ ትጠይቀው ነበር ። ፍቃደኛ ባይሆንም ።
ባርች
አሁንስ ምን ሆን? እንደዝሁ ብንኖር ምን ችግር አለው።
እመቤት
ምን ችግር አለው።
ባርች
ችግር ይኖረዋል ሳይሆን . . .
እመቤት
ታድያ ምንድን ነው?
ባርች
ሰው ምን ይለናል?
ከተዋወቅን አመት እንኳን አይሞላንም?
ምን እንደሚሉኝ ደሞ አስቢው ።
እመቤት
ምን ይሉሃል?
ደሞ ስለሰው ምን ገዶህ ነው? የፈለጉትን ይበሉ?
(ራሱን ይነቀንቃል)
አፍረህ ነው እንጂ ሌላ አደለም። ያን ያህል ትልቅ ነኝ እንዴ?
ከፊቱ ተቀምጣ ከነበረችበት አልጋ ላይ ተነስታ ወደ መስታወቱ ትሄድና ትቆማለች ። ቆመናዋን ታያለች ።
እመቤት
ምኔ ነው ያስረጀኝ?
ባርች
አላረጀሽም።
(አላረጀችም)
እመቤት
አስቀያሚ ሆኜብህ ነው ታድያ
(አልነበረችም)
ባርች
እመቤት ነው ምትመስይው
እመቤት
እና አብረን ብንኖር ምን ችግር አለው?
ሃና(V.O.)
አልማዝ ተማጽኖዋን ለ2 ሳምንት በኋላ በትጋት ቀጠለች። በመጨረሻም አብሯት ለመኖር ተስማማ
ባርችና እመቤት በዚሁ ጉዳይ በተለያየ ጊዜ ሲነታረኩ እናያለን ። በመጨረሻም ባርች በሌሊት ታክሲውን ከመጠጥ ቤቱ ፊት ለፊት አቁሞ ሻንጣውን ይዞ ይወርዳል እመቤት ከበሩ ቆማ ትጠብቀዋለች በደስታ ሆና ።
CUT TO:
int. የነጃምቦ ቤት - ጥዋት
ሃና(V.O.)
ወደ አባቴ እንመለስ
አባቷ ሶፋው ላይ ተኝቶ እንቅልፍ ውስዶታል ። በቤት ውስጥ ማንም ባይኖርም ከውጭ ጫጫታ ይሰማል የህጻናትና አዋቂዎች ንግግር ። ከውጭ ሃና ትገባና ወደ ቆጡ እየሮጠች ትወጣለች ፣ ሌሎችም ህጻናት ተከትለዋት ይሮጣሉ በሽክሹክታ ።
ሃና(V.O.)
ላለፉት ሶስት ወራት የተፈጠረ አዲስ ነገር አልነበረም ።
ትወርዳለች ። ህጻናቱ ተከትለዋት ይወርዳሉ ። ወደ ውጭ ይወጣሉ ። በዚ ሁሉ ነገር አባቷ ለጥ ብሎ በመተኛቱ እንደለመደው ጠጥቶ ራሱን ስቶ ነው ወይ ብለን መገመታችን አይቀርም ።
ሃና(O.S.)
እንደሱ አደለም
አቢት(o.s)
እና እንዴት ነው?!
እኔ አቅበታለው!
ሃና(O.S.)
ቆይ መጣሁ?
ሃና ተመልሳ ወደ ውስጥ ትገባለች ። ልጆቹ በር ላይ ቆመው የተኛውን አባቷን የታሰረ አምበሳ እንደሚያይ ሰው ከሩቁ ያዩታል ። ሃና ወደ አባቷ ተጠግታ ያለብርድ ልብስ ተጠቆሎ የተኛውን አባቷን ነካ ነካ ታረገዋለች ። ከዚህ በፊት ቁርስ ስትበላ እንዳደረገችው ። እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ አይነሳም ። ድጋሜ ወጋ ወጋ ታረገዋለች ። አይነሳም ። ሶስተኛ ስትወጋው ግን ይባንናል ። በላብ የሚያንጸባርቁት ልጁና ህጻናት ሁሉም ወደሱ እያዩ እናያለን ።
ሃና
የጓሮውን ቁልፍ ስጠኝ አባ?
መሰላሉን አውጥተን ኳስ ልናወርድ ነው ጣሪያ ላይ ስለሆነ።
ሃና(V.O.)
በሶስት ወር ውስጥ እንዳለው አባቴ ምንም አይነት መጠጥ አልነካም ። መጠጥ ቤት በሚባል ቦታም አላለፈም ።
ከደህና እንቅልፉ በድንገት የተነሳው ጃምቦ ኳስ ለማውረድ ቢቀሰቀስም ልጆቹን ሊቆጣቸው አልፈለገም ። በረጅሙ እየተነፈሰ ይነሳል ።
CUT TO:
EXT. ቆሎ ቤት ደጅ ላይ - ቀን
ጃምቦ በረንዳው ላይ ቆሞ ከባሪያው ጋር እየተነጋገር እንመለከታለን ሂሳብ እያወራረዱ።
ጃምቦ
የውልህ ስማኝ ባለፈው ስንት ነው የወሰድከው?
10 ማዳበሪያ ያስገባህ ጊዜ?
ባሪያው
320?
ጃምቦ
አየህ ከሱ ስንት ብር ጨመርኩልህ ማለት ነው?
50 ብር ጨመርኩልህ አደል?
ባሪያው
ዎ ሰውየ ያማ ባለፈው ነው?
ጃምቦ
የውልህ አድምጠኝ?
አሁን ባለፈው የሰጠሁህ 50 ብር ላይ 100 ስጨምር ቻለ አደለ?
ሃና(V.O.)
ከተለመደው ስራ ውጭ ከተለመደው የሂሳብ ጭቅጭቅ ፣
በመሃል ስልክ ተደውሎለት ሲነጋገር እናያለን ጭቅጭቅ በሚመስል መልኩ
ሃና(V.O.)
ከተለመደው ደምበኛን የማባበል የሽንገላ ቃላት በቀር
ስልኩን ይዞ ወደውስጥ ይገባላ ።
INT. ቆሎ ቤቱ - የቀጠለ
አይኑን ገለባ እየከደነው ጆሮውን የብረት ምጣድ ለቅሶ እያከከው ከማዳበሪያዎቹ ክምር አጠገብ ሄዶ ይቆምና ስልኩን ከጆሮው አርቆ ይነጋገራል ።
ጃምቦ
ይኸው አሁንም እኮ እዛው ቆሜ እያሰራሁኝ ነው
ደምበኛው
ትናንትና አልነበር መድረስ የነበረበት አሁን እኮ እጄ ላይ ምንም የለም?
ጃምቦ
ትናንትና ቆይዋ ለቅሶ ነበራት ሄሎ?
(ደምበኛው የባክ ግራውንዱን ጩኸት እንድትሰማው ወደ ቆሊታዋ ሄዶ ስልኩን እያስጠጋው)
ሃና(V.O.)
ምንም አዲስ ነገር አልነበረም።
CUT TO:
EXT. ቤተክርስቲያን በር - አመሻሽ
ጉባኤውን ለመሳተፍ ከመጡት ሰዎቹ ጃምቦ የቤተክርስቲያኑን ግምብ ሲሳለም እናያለን። ከኪሱ መቶ ብር አውጦ ሙዳየ ምጽዋት ውስጥ ሲከተው ። ተሳልሞ ሲወጣ ።
INT. የጃምቦ ቤት - ማለዳ
ጃምቦ በሳሎናቸው ውስጥ ከነበረ ስዕለ አድህኖ ስር ቆሞ መዝገበ ጸሎቱን ይዞ እየጸለይ እናያለን እየተማጸነ ። ከጀርባው ከአልጋው ጣይቱ ጀርባዋንን ሰጥታው ተኝታለች። ከልብ ያለ ጸሎት።
ሃና(V.O.)
ነገር ግን በታህሳስ ወር ከወሩ በአንደአኛው ቀን የአንድ ደምበኛውን ዝክር መድረስ ነበረበት ። ለዛም -- ሄደ።
EXT. የደምበኛው ቤት ደጅ - ቀን
ጃምቦ ዝክሩን ለማድረስ ከመጡ ሌሎች ሰዎች ጋር ሌላ ሰው ሆኖ ተቀላቅሎና ለብቻው ተነጥሎ ተቀምጧል ። ጃምቦ ከተቀመጠበት ተነስቶ ብፌውን ይዞ ተመልሶ ተቀምጦ እየበላ 'ብቻውን' በሚባል መልኩ ። የደጋሽ ዘመድ የሆነችው አንዷ ወዲህ ወዲያ እያለች ሰዉን እያስተናገደች ፣ ጃምቦ ምንም መጠጥ ሳይዝ አይኑ ወዲህ ወዲያ እያለ በሚጠጡት ምራቁን እየዋጠ ትመለከታለች ።
ሴትየዋ
ጠላ ልቅዳልህ አደል?
በድንገት ዙርያው ሁሉ ብርሃኑ ደብዘዝ ይልና ሰዉ ሁሉ እሱን ያያል። መልሱን በመጠበቅ ።
ሃና(V.O.)
ለሶስት ወር ምንም መጠጥ አልነካም።
ሴትየዋ እንገዳ ተቀባይ የነብረው ፈገግታዋ ፣ ወደ ሚያስፈራና ተንኮል ወዳዘለ አሳሳቅ ተቀየረ ። ሰዎቹም 'ብቻውን' አልተዉትም ። ምን ይበል?
ጃምቦ ራሱን ነቀነቀ ፣ እርግጠኛ ሳይሆን ። ወዲያ ሁሉ ነገር እንደነበር ይመለሳል ሰዉም ወደ ጉዳዩ ይገባል ፣ ሴትየዋል ካገነበሰችበት ቀና ትልና ወደ ቤት ውስጥ ትገባለች ።
ሃና(V.O.)
ነገር ግን ከዛ ሁሉ ሰው ፊት 'አልጠጣም' ብሎ ማለት አሳፈረው።
ሴትየዋ ተመልሳ ትመጣች ፣ ጠላ የሞላ ጆግና ብርጭቆ ይዛ ። ብርጭቆውን ከፊቱ ታስቀምጥና ታንቆረቁርለታለች ። ጃምቦ ምራቁን ይውጣል ።
ሴትየዋ
እስኪ ጠጣ ምንም አይል
ብላ ወደ ውስጥ ተመለሰች ።
ጃምቦ መጠጡን እዛው እንዳለ ትቶ ለመውጣት ስለፈለገ ምግቡን መብላቱን ቀጠለ ። ሰዉ ግን አሁንም አሁንም ወደ እሱና ወዳልነካው መጠጥ ማየት አዘወተሩ ። 'ብቻውን' አልተው አሉት።
እንደቀደሙ ዙሪያው ጨለመ ሁሉም ወደሱ እያዩ እንደሆነ ሲያየ እየፈራና እየተባ ብርጭቆውን አነሳው ወደ ፣ ወደ አፉ አስጥጋው ፣ ሁሉም እያዩት ነው ፣ ከንፈሮቹና ብርጭቆው ተነካካ ፣ ፉት ፣ ፉት ፣ ፉት ፣ ልግት ።
EXT. የዲቡ ቤት ግቢ - እኩለ ሌሊት አካባቢ
ጨለማ ከተንጣለለው ግቢ ላይ ነግሶበታል ። በከባዱ ይተነፍሳል ። በመስኮቱ በኩል ከዘመናዊው ቤት ውስጥ ሰው እንዳልነበር እናያለን ።
ሃና(V.O.)
ያን እለት ማታ ታዲያ ስንታየው . . . ሁለተኛውን ጥፋት ለመስራት ወሰኖ ነበር።
ከአጥሩ ቁጢጥ ብሎ ቆሞ ። ወደውስጥ ይመለከታል ሰው አልነበረም። ትንሽ ጠብቆ ወደውስጥ ይዘላል ። እንደወረደ ፣ ከቤቱ ውስጥ አንዲት ቡችላ መጮህ ትጀምራለች። የላይኛው ወለል መብራት ይበልራል ። ስንታየው ምሽግ ፍለጋ ይሮጣል ። ዲቡ ደስታዬ በመስኮቱ በኩል ቁልቁል ይመለከታል ። ሙታንታውንና ፓከውቱን አድርጎ የሚያስጮኸው ነገር ምን እንደሆነ ለማውቅ ።
ስንታየው የለበሰው ጥቁር ልብስና በአይኖቹ ልክ የቀደዳቸው ክፍተቶች ያሉበት ኮፍያው ከህንጻው ስር ሲደበቅ እንዳይታይ አድርጎታል ። ዲቡ ደስታየ በመስኮቱ ቆሞ ጥቂት ካሰሰ በኋላ ወዳለመታየቱ ይመለሳል ። መብራቱን አጥፍቶ።
መብራቱ መጥፋቱን ሲያስተውል ወደ አንዱ ጥግ የቤቱን ዙሪያ ያስሳል ስናትየው ። ውሻው ይጮሃል ። ወደውስጥ መግቢያ መንገድ እንደሌለው ሲያቅ ፣ በመጣበት መንገድ ሲመለስ አንዳንድ እቃዎች ይወድቃሉ በመንገዱ ላይ የተኮለሉ። ስንታየው ጩኸቱ እስኪያልቅ በትግስት ይጠብቃል ። እንዳለቀ ወደፊትለፊቱ በር ይሮጣል። በድጋሜ ይሞክራል። አይከፈትም።
አሁንም በሌላኛው ጓሮ በኩል ይሄዳል ፣ ነገር ግን በዚህ በኩል ምንም የሚያንቀሳቅስ ጠባብ መንገድ እንደሆነ ሲረዳ መግቢያ እንደሌለው አውቆ ወደ መኪናው ይሄዳል። ጎማውን ሊያተነፍስ ይሞክራል ። 3 ጎማዎችን አተንፍሶ ወደ4ተኛው እያመራ ፣ ዋናው በር ይከፈታል ።
ዲቡ
ቁም እንዳትበላሽ!?
ብችላዋ ከዲቡ ጀርባ ሾልካ ትወጣና ወደ ስንታየው ትሮጣለች ።
ስንታየው የዲቡን ዛቻ ሳይሰማ ይሮጣል ።
introው ላይ የሰማነውን ሙዚቃ በድጋሜ እናደምጣለን ።
ስንታየው በሩን ከፍቶ ሊወጣ ሲል ዲቡ በእጁ ይዞት የነበረው ብረት ነገር ይወረውርበታል ። ስንታየው ሽል ይላል ፣ በሩ ሲመታ ይጮሃል ።
ዲቡ
ቁም ብዬሃለው ሌባ! ዘረ ቢስ ሌባ! ቁም ብዬሃለው!
ስንታየው ግን አልቆመም በሩጫ ከአጥሩ ይወጣና ወደዛኛው መንገድ ይወድቃል ።
EXT. መንገድ ላይ - የቀጠለ
ስንታየው ይሮጣል ፣ ጭምብሉን ከፍ አድርጎ ፣ ከጀርባው የሚታይ ሰው አልነበረም ። ከጀርባው ማንም እንደሌለ ሲረዳ ፣ ወደሰፈሩም እንደደረሰ ሲያውቅ ተረጋግቶ ትንፋሹን ሊሰበስብ ይሞክራል።
ወደ ፊት በአዝጋሚ እርምጃዎች ሲራመድ የአንድ ሰው ድምጽ ከሩቁ እየለፈፈ እንሰማለን ። ስንቀርብ ፣ ስንጠጋ ለፋፊው ጃምቦ እንደነበር እናያለን።
ያን ሲያይ ጊዜ ስንታየው ሃዘን ፊቱን ይገባዋል ። ራሱን ይነቀንቃል ።
ስንታየው ወደ ጃምቦ ሄዶ ይደግፈዋል።
ጃምቦ
ማ? . . . ሌባ!?
ጃምቦ
እ? . . . ቦቼ?! የተረገሙ ሰዎች?!
አንድ ጠጣ ብለው አጠጡኝ!!
ተሸነፍኩ!
INT. የነጃምቦ ቤት - የቀጠለ
ሃና ቴቪውን እያየች እንቅልፍ ወስዷታል እናቷ በር በሩን እያየች በሃሳብ ትነጉዳለች ። በእክለ ሌሊት ባሏ ከቦታው ባለመኖሩ ።
እንዲህ ባለ ሁኔታ ትንሽ ቆይታ በመጨረሻ በድንገት ግን ከውጭ የሰከረው ባሏን ድምጽ ትሰማለች ።
ስንታየው(O.S.)
ቀስ?
ጃምቦ(O.S.)
ቀስ አትበለኝ!?
(ጩኸቱ ሃናን ይቀሰቅሳታል)
ጣይቱ
ተነሽ ግቢና ተኚ!?
ቶሎ በይ?!
ሃና በመደናገጥ ወደላይ ትወጣለች
ጃምቦ(O.S.)
አልሰከርኩም!!
(ድምጹ እየቀረበ)
እናቷ ወደ በሩ ስታመራ በሩ በሃይለኛው ይከፈታል። ሃና ደረጃምውን መውጣት አቁማ ወደ በሩ ፊቷን ታዞራለች
ጣይቱ
ብለህ በለህ ሌሊት ይዘኸው መምጣት ጀመርክ
ጃምቦ
አልሰከርኩም እንዴ?!
ስንታየው ምንም ሳይል ወደ ውስጥ ይገባና ሶፋው ላይ ያስተኛዋል። ይሄኔ የጃምቦ ጩኸት ከትልቁ ሰፈራቸው ውስጥ የነበረውን መንደር ይቀሰቅሳል ፣ ሰዎቹም ከበራቸው እየወጡ ብቅ እያሉ ማየት ይጀምራሉ ። ስንታየው አስተኝቶት ሊወጣ ሲል
ጣይቱ
ሌላ ማንም ሰው እንዲህ አያደርገውም ሊዚህ ሰውዬ ጠንቁ አንተ ነህ አው!? ይሄ ሰውዬ አንድ ነገር ቢሆን ካንተ ራስ አልወርድም
ዝም ብሏት ይወጣል
ጃማቦ
ቦቼ!!!! ወንድሜ!!!!
ጣይቱ
እያናገርኩህ ንቀት ነው ማትመልስልኝ? ገና ለገና ስራ አገኘሁ ብለህ? የተማርክ ስለሆንክ?
ጃምቦ
አንቺ ሴትዬ ተይው እኮ ነው ምልሽ!?
ጃምቦ ከተቀመጠበት ለመነሳት ሲሞክር የቡናውን ረከቦት በእጆቹ ተጭኖ ይደፈጥጣቸዋል እሱም ይወድቃል። ትርምስ። ስንታየው የወደቀውን ጃምቦን ሊያነሳው ዝቅ ይላል። ሃና ታለቅሳልች ፣ አቢቲና እናቱ ወደ በሩ ጠጋ ይላሉ
ጣይቱ
ገና ለገና ፍቅረኛው ጥላው ሄደችና የኔ ቤት መታመስ አለበት እንዴ?
(ወደ እማሹ ዞራ)
እማሹ በእጁ ዝም እንድትል እና እንድትተወው ታመለክታታለች ። ነገር ግን ጣይቱ ፊቱ ግሎ አይኗም ርሶ ሳግ እየተናነቃት ነበር ምትናገረው ።
ጣይቱ
አደለማ?! ሰው ስንቴ ዝም ትይዋለሽ አንዴ ሁለቴ ትታገሻለሽ! ዘላለሜን ዘላለሜን ከሱ ጋር ከተገናኘ-ቤቴ ይበጠበጣል። እኔ አብሮ አደጉ ነው ብዬ ይከፋዋል ብዬ እንጂ አፌን ይዤ የከረምኩ?
ስንታየው ሊወጣ ቢፈልግም ነገሩን ለማጣራት በሩ ላይ ተኮልኩለው የነበሩት ሰዎች ማለፊያ እንደማይሰጡት ሲያውቅ ነገሩን ለማብረድ
ስንታየው
ከመንገድ ላይ ነው ያገኘሁት?
ለምን ክፉ ትናገሪያለሽ?
ልጅቷንም አታስለቅሻት?
ወደ ሃና ዞሮ
እማሹ
ነይ ሚጣ ነይ?
ጣይቱ
ጭራሽ ልትመክረኝ? ቤቴን እንዴት መምራት እንዳለበኝ?
ወደ አደለም ለካ ያቺ ሩት አንቺ የሸሸችው ምኑ አይናውጣ ነው።
የግርምቱን እየሳቀ ወደውጪ በሰዎቹ መሃል ሰርስሮ ሊያልፍ ሲል።
ጣይቱ
እንዳልቀስክ ኑር መድሃኔዓለም አዬ?
ስንታየው
እንዳውም አንድ ነገር ልንገርሽ?! አጠጥቼውም ከሆነ ደግ አረኩ?! ደግ አረኩ?! ደም አንባ አልቅሺ?!
ሊያልፋቸው የነበሩት ሰዎች ታዲያ ይህን ሲሰሙ (ጎልማሶቹ) ያጉረመርማሉ
ጎልማሶቹ
ማነኝ ነው ምትለው ቋይ?
ምንድን ነው ሚለው?
ና እስቲ ወዲህ?
ቀጫጫውን ስናታየውን በአንገቱ ይዘው ያወጡታል።
ሴቶቹ
አረ ተዉ ቆይ ተዉ እንጂ?
ሊወቁት ይጀምራሉ ስንታየውም እጆቹን ይሰነዝራል።እልህ ። ውጭ የነበረው እቃ ይተረማመሳል
ጃምቦ
ቦቼ!!!! ቦቼ!!!!
ጃምቦ በድጋሜ ሊነሳ ሲልና ወደመሩ ሲያመራ በድጋሜ ይወድቃል። ሲጸልይበት ከነብረው ሰዕለ አድህኖ ፊት። ወጪ ድብደባው ይቀጥላል ። ሴቶቹ ለማገላገል ይጥራሉ ፣ ጣይቱ በሩ ስር ተቀምጣ የተደፋውን ባሏን እያየች ታነባለች ።
ሃና ወዳባቱ ትሮጥና ለማንሳት ትጥራለች ።
CUT TO:
INT.የነጃምቦ ቤት - የቀጠለ
ጃምቦ እንደለመደው ተኝቷል ፣ በቤቱ ውስጥ ሃናና አቢቲ ብቻ ቴሊቪዥን እያዩ ተቀምጠዋል ፣ አቢቱ ሰርቅ እያረገ ወደ አባቷ ያያል ። አባቷ ቆይቶ እየተንፏቀቀ ይነሳል ። ሲነሳ ጊዜ ሃናና አቢቲ እየሮጡ ይወጣሉ
ጃምቦ
(ስካሩ ሳይለቀው)
እናንተ?
ሃና(O.S.)
መጣን አባ
ጃምቦ ከተኛበት እየተነሳና ፊቱን እየደባበሰ እኩለ ቀን እንዳለፈ ሲረዳ እንደለመደው በቤቱ ውስጥ ሃይላንድ መፈልግ ይጀምራል ።
EXT. መንገድ ላይ - የቀጠለ
ሃና እየሮጠች አቢቲን ትቀድመዋለች ፣ ወደ አንድ የሴቶች ጸጉር ቤት ከሚመስል ቤት ትገባለች እኛ አንገባም ።
ከውስጥ የሴቶች ድምጽ ይሰማል ፣ የተርጋጋ ጨዋታ
ሃና(O.S.)
(በሽኩሹክታ)
እማ? ተነስቷል?
ጣይቱ(O.S.)
እሺ መጣሁ ጠብቂኝ ውጭ?
መጣሁ እሺ! እቺን እንደሱ ያዣት በጣም ይቅርታ?
አቢት ቀስ ብሎ ሲደርስ እናትና ልጅ ተያይዘው ከቤቱ ውስጥ ይወጣሉ ።
አሁንም ከኋላቸው እየተከተለ በመጡበት መንገድ ይመለሳሉ ።
INT. የነጃምቦ ቤት - የቀጠለ
ጃምቦ በየጉራንጉሩ ሃይላንድ ይፈልጋል ። ሶፋ ስር ፣ ከአልጋው ጀርባ ፣ ከብፌው ውስጥ ፣ ቆጥ ላይ ደረጃውን ውጥቶ ። ሃይላንድ የሚባል ነገር አልነበለም ። ከቆጡ ሲወርድ እንደናወዘና እንደጀዘበ ሆኖ ጣይቱ ከበሩ ትደርስና ደረጃምው ላይ የተቀመጠውን ጃምቦን
ጣይቱ
እ? ነቃህ? ተመልሰህ ተኛ እስኪለቅህ?
ጃምቦ
ሃይላንዱ የታል?
ጣይቱ
ህ! አንተ ሰውዬ ጤነኛ አደለህም እንዴ? ምን ሊያረግልህ ነው ሃይላንድ?
ጃምቦ
ዝም ብለሽ አምጭ?
ጣይቱ
የለም? ሃይላንድ ሚባል በቤቱ የለም? አህው!
አውጥቼ ቆሻሻ መጣያ ጥዬዋለው ? መጠጣት ከፈልክ ከዛ ከገንዳው ቆፍርና አውጣ?!
ጃምቦ
(በሚተረክክ ድምጹ በሰከረ አንደበቱ)
እህ?! አንቺ ሴትዮ ያምሻል እንዴ?!
ጣይቱ
ከአንተ ጋር እየኖርኩ ጤነኛ እሆናለው ብለህ ነው?
ጃምቦ
እህ? ምን ፈልገሽ ነው።
EXT. የነጃምቦ በረንዳ ላይ - የቀጠለ
አቢቲ የነጃምቦን ጩኸት ላለመስማት ስልፈለገ ተመስጣና ተጨንቃ የነበረችውን ሃናን ጎንተል አድርጎ ከግቢ ወጥተው እንዲጮቱ ይጠይቃታል ። ተያይዘው ከግቢ ይወጣሉ ።
ጃምቦ(O.S.)
በቃ ዞር በይልኝ?!
ጣይቱ(O.S.)
ጭራሽ?!
ልጆቹን ተከትለን እንወጣልን ፣ ከለመዱት ቦታ ብያቸውን መጫወት ይጀምራሉ። ትንሽ ቆይተው?
ሃና
ስንታየውን አልወደውም ፣ በጣም ነው ሚያስጠላው
አቢቲ
ቦቸራን ነው?
ሃና
አው አባቴን እያሰከረብኝ
የግቢያቸው በር በሃይለኛው እንደተከፈተ ሁለቱም ወደ በሩ ፊታቸውን ይመልሳሉ ። ጅምቦ ሃይላንዱ አግኝቶ በጁ አጥብቆ እንደያዘ መንገዱን ከአጠገባቸው ይደርሳል።
ጃምቦ
እናትዬ የኔ እናት
ጉንጯን ስሟት ያልፋል ከንፈሩ ስለሸተታት ፊቷን ትቋጥረዋለች ። ከኪሱ 100 ብር አውጦ
ጃምቦ
እኑ ብስኩት ብሉ ግዙ ብስኩት!
የተሰጣቸውን ብር ሃና ደስ ሳይላት ተቀብላ ርቆ እየሄደ ያለውን አባቷን ትመለከትዋለች ትክ ብላ ፣ አቢቲ ደሞ የብስኩት ብሩን።
INT. መስራያ ቤት - ቀን
ስንታየው ወረቀት ላይ የሚሞላ ነገር ሲሞላ ቆይቶ ቀና ሲል አንድ አይኑ ጠቁሮ እንመለከታለን። ከአጠገቡ ዴስክ የነበረችውን ልጅ ሲመለከታት እንደሱ አልደበራትም ጆሮዋ ላይ ኢር ፎን ሰክታ ከኮምፑተሯ ምታየውን እያየች ፈገግ እያለች ነበር ። በረጅም ይተነሳል።
EXT. ሰፈራቸው ውስጥ - አመሻሽ
ከስራ ከወጣ በኋላ ስንታየው በሰፈራቸው መንገድ እየተራመደ እንመለከተዋለን እንደለመደው አቀርቅሮ ። በመጠጥ ቤቷ በኩል ሲያልፍ ሰዓቱን ተመለከተና ወደመጠጥ ቤቱ ሊገባ አለ ። ነገር ግን በሩቁ ጃምቦን ከመጠጥ ቤቱ ሲወጣ ተመለከተውና እንዳያየው በፍጥነት እየተራመደ ወደ ሰፈሩ መሿለኪያ ሊገባ ገሰገሰ ። ጃምቦ ግን መመልከቱ አልቀረም።
ጃምቦ
ቦቼ!! ቦቼ!!!!
ስንታየው እንዳልሰማ ሆኖ ኮቴውን አፍጥኖ ይራመዳል።
INT. የነስንታየው ቤት - የቀጠለ
ቦቼ እያለከለከ ወደ ቤቱ ይገባል ከጀርባ የተከተለው ሰው አለመኖሩን ቼክ እያረገ ።